ስብከተ ወንጌልና የጥምቀት በዓል
1. የቃላት ትርጒም
“ስብከተ ወንጌልና የጥምቀት በዓል” በሚለው ርእስ ውስጥ በጋራና በተናጠል ትርጒም የሚሹ አራት ቃላት ይገኛሉ፤ እነዚህም ወንጌል፥ ስብከት፥ ጥምቀትና በዓል ናቸው፤ ስብከትና ወንጌል በአንድነት ተጣምረው “ስብከተ ወንጌል” የሚል ሐረግን ይፈጥራሉ፤ ይህ ሐረግም የራሱ ትርጒም ያስልገዋል፤ በተመሳሳይ መልኩ በዓልና ጥምቀት የሚሉት ቃላትም በአንድነት የሚሰጡት ትርጒም ተያይዞ ቀርቧል፡፡
1.1 ወንጌልናስብከተ ወንጌል
ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው? ስብከት ማለትስ? ወንጌልና ስብከት የሚሉት ቃላት በአንድነት ተጣምረው ሲነበቡ “ስብከተ ወንጌል” የሚለው ሐረግ ምን ትርጒም ይሰጠዋል?
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወንጌል የሚለውን ቃል ሲተረጒሙ ወንጌል (ወንጌላት ሲበዛ፥ በጽርዕ/ግሪክ “ዮአንጌሊዎን”፥ በዐረብ ኢንጂል ካሉ በኋላ) “በቁሙ ወንጌል፥ ብሥራት፥ ምሥራች፥ ሐዲስ ዜና፥ መልካም ወሬ፥ ደስ የሚያሰኝ ስብከት፥ አምላካዊ ቃል፥ ሰማያዊ ነገር፥ ምሥጢረ ሥላሴ፥ ምሥጢረ ሥጋዌ” ሲሉ ተርጕመውታል፤ በመጽሐፍነቱ ሲፈቱም፦ “መጽሐፍ፥ የመጽሐፍ ስም፥ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ፥ እንደ ነገሥት አራት ክፍል ያለው፥ አራት ሰዎች የጻፉት” ይሉና “ፍቺው ብሥራት ማለት ነው” ይሉታል፡፡ ደስታ ተክለ ወልድ በበኩላቸው፦ “ወንጌል-የመጽሐፍ ስም፥ አራት ሰዎች የጻፉት፥ የክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ መጽሐፍ፥ ትርጓሜው የምሥራች ማለት ነው” ይላሉ፡፡
የክርስቲያን እምነትና ጸሎትም በወንጌል እውነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ሃይማኖቱ “ሃይማኖት ወንጌላዊት”፥ ጸሎቱም “ጸሎት ወንጌላዊት” ተብሎ ተገልጧል ሃይማኖቱን በተመለከተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ “ከእናንተ መካከል ማንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጸጋ የታጣ (የጠፋ፥ የራቀ) አይሁን፤ ይኸውም የምትመጣዋ ደስታ እና ወንጌላዊት ሃይማኖት ናት” ይላል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው መዛግብተ ቃላትና የሊቃውንት አባቶች ትርጒሞች እንደሚያስረዱን በግእዝና በአማርኛ ወንጌል የምንለው ቃል “ዮአንጌሊዎን” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ትርጒሙም “የምሥራች ቃል” ማለት ነው፡፡ መቅድመ ወንጌልም ቃሉን ሲተረጕም “ወንጌል ብሂል በልሳነ ጽርዕ ወትርጓሜሁ ስብከት” ይላል፤ ትርጒሙም “ወንጌል የሚለው ቃል በጽርዕ/በግሪክ ቋንቋ ነው፤ትርጓሜውም የምሥራች ማለት ነው” ይላል፡፡
ወንጌል ማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን፥ መወለድ፥ ማደግ፥ መጠመቅ፥ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ተአምራት፥ ሞትና ትንሣኤውን፥ ዳግም ምጽአቱን በአጠቃላይ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ያደረገውን የማዳን ሥራ የሚያስተምር ትምህርት ነው፤ ስለዚህ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሰውን ለማዳን ነው በማለት የሚታመን እምነትና የሚታወጅ እውነት ነው፤ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣበት ምክንያት ነው፤ ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ነው፤ ወንጌል ራሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ወንጌልን መስበክም ክርስቶስን መስበክ ነው፡፡
ወንጌልን ከጥንቱ ከመሠረቱ ከብሉይ ኪዳን ታሪክና ትምህርት አንጻር ስናየው በታሪክ፥ በሕግ፥ በትንቢት፥ በመዝሙር፥ በቅኔ፥ በምሳሌና በጥበብ መልኩ ሲሰበክ የኖረ ትምህርት ነው፤ በተለይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ ዐይቶ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” በማለት በብሉይ ኪዳን ተሠውሮ ያለውን የወንጌል መልእክት ያሳያል (ገላ. 3÷8) ፤ ክርስቶስም “አብርሃም አቡክሙ ተመነየ ይርአይ ዕለትየ ርእየሂ ወተፈሥሐ” ማለት “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ/ፈለገ፤ አየም፤ ደስም አለው” (ዮሐ. 8÷56) በማለቱ ነቢያት በዐይነ መንፈስ ዐይተው፥ በመንፈሰ ትንቢት አምነውትና ሰብከውት፥ በእርሱ ተደስተው ያለፉ መሆኑን ተናግሯል፤ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ወንጌል ሥረ መሠረቱ ጥንት መሆኑን ነው፡፡
ሆኖም ግን ትንቢቱና ተስፋው ተፈጽሞ አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ በወንጌል መጻሕፍት ለመጀመሪያ ጊዜ “ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ” (ማር. 1÷14-15) ተብሎ እንደተጻፈው “ወንጌል” ክርስቶስ፥ ወንጌል ተስፋ መንግሥተ ሰማያት፥ ወንጌል የዘለዓለም ሕይወት እንደሆነ የሰበከው ክርስቶስ ነው፤ ከክርስቶስ የተማሩትን ደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ጸንተው እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ አዳራሱት፤ ይህም ወንጌል እስከ ዛሬ ድረስ እየተሰበከ ከእኛ ዘመን ደርሷል፡፡
1.2. ስብከትና ስብከተ ወንጌል
ስብከት የሚለውን ቃል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ሰቢክ፥ ሰቢኮት” በሚለው ንኡስ አንቀጽ ሲፈቱት “መስበክ፥ ማብሠር፥ ማስተማር፥ በታላቅ ቃል መጮኽ፥ ማሰማት፥ መልፈፍ፥ መለፍለፍ፥ ዐዋጅ መንገር፥ ማዜም፥ መዘመር፥ ማውራት፥ መመስከር” ይሉታል (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፥ ገጽ 845)፤ ወንጌል የሚለውን ቃል ስንተረጒም ወንጌል ማለት ስብከት ማለት ነው ብለን ከመቅድመ ወንጌል ማስረጃ ዐይተናል፤ በዚህም መሠረት ስብከት ማለት ወንጌል፥ ወንጌል ማለትም ስብከት ማለት እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡
ወንጌል የክርስቶስ የማዳን ሥራ፥ ወንጌል ራሱ ክርስቶስ ስለ ሆነ “ስብከተ ወንጌል” የክርስቶስን የማዳን ሥራ መስበክ፥ ማወጅ፥ ማስተማር፥ መመስከር ይሆናል፤ ይህም ማለት ክርስቶስን ክርስቶስን መስበክ ፥ ማወጅ፥ ማስተማር፥ መመስከር ነው፡፡
የጥምቀት በዓላችን የክርስቶስን የማዳን ሥራ የምንሰብክበት፥ የምናውጅበት፥ የምናስተምርበት ሃይማኖታዊ ሥርዐታችን፥ ክርስቶስን የምንሰብክበት ወንጌላችን ነው፤ ስብከተ ወንጌልና የጥምቀት በዓል በሚለው በዚህ አጭር ጽሑፍ ለማሳየት የተፈለገውም ይህን ነጥብ ነው፡፡
1.3. ወንጌልን የመስበክ ኀላፊነት የማነው?
ስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን እንደ እልቅና፥ እንደ ጸሓፊነት ወይም እንደ ሒሳብ ሹምነት/ ሠራተኛነትና እንደ ቁጥጥር ወዘተ አንድ የሥራ ዘርፍ አይደልም፤ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ሁሉ መሠረትና የሁሉም ምእመናን ኀላፊነት ነው፤በተለያየ መንገድ ሁላችንም ሰባክያነ ወንጌል ነን፤ ስብከተ ወንጌል እምነትንና እውቀትን እንጂ ሹመትን አይጠይቅም፤ ክርስቶስ “ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ብሎ የተናገረው ቃል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለክርስያኖችና ወንጌልን መስበክ ለሚፈልጉ ሁሉ መመሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡
ይህ ማለት ግን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ዕውቀት ፥ እምነትና ችሎታ ሳይኖራቸው፥ ሥርዐትንና ሕግን ሳይከተሉ እንደፈለጉ መስበክ ይቻላል ማለት አይደልም፤ ወንጌልን የመስበክ ኀላፊነት ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠበቅ አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ለመናገር ነው እንጂ፤ ይህን የተረዳው ሐዋርያ “ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።” (1ቆሮ. 9÷6) ሲል የጻፈውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡
1.4. ጥምቀትና የጥምቀት በዓል
ጥምቀት፦ በዓልም፥ እምነትም ምሥጢርም ነው። በበዓልነቱ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ዓላማ የአደባባይ በዓል አድርገን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐት መሠረት እናከብረዋለን፤ በእምነትነቱ “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት” ማለትም “ለኀጢአት ሥርየት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ብለን እንመሰክራለን፤ በምሥጢርነቱ ደግሞ በካህን እጅ፥ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ይፈጸማል፤ በዚህም ተጠማቂው ከእግዚአብሔር ዳግም ይወለዳል፤ ይህ የመዳን ምሥጢር የሆነው ጥምቀት“ምሥጢረ ጥምቀት” ተብሎ ከአምስቱ አዕማደ ምሥጢር አንዱ ሆኖ ይቈጠራል፡፡
በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ትምህርት መሠረት በዓል ማለት ለመታሰቢያነት የሚደረግ አፍኣዊ እና ልማዳዊ ሥርዐት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ማዳን የምንሳተፍበት የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ነው፤ የጥምቀት በዓልም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስንማንነትና የሥላሴን ምሥጢር ያወቅንበት፥ ክርስቶስን አምነን ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበት፥ በማዳን ምሥጢሩ የምንሳተፍበት፥ የቤተ ክርስቲያን አካል የሆንንበት ምሥጢር ነው፡፡
2. የጥምቀት በዓልንና ስብከተ ወንጌልን የሚያስተሳስሩ ነገሮች ምን ምን ናቸው?
2.1. የጥምቀት በዓል የተመሠረተው በወንጌል ትምህርት ላይ ነው፡፡
አራቱም ወንጌላት ከመዘገቧቸው የወንጌል ታሪኮች አንዱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው፤ በማቴ .3÷13-17፤ ማር.1÷9-11፤ሉቃ.3÷21-22 እና ዮሐ.1÷32-34 ተመዝግቦ የምናገኘው የወንጌል ቃል ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፤ የጥምቀት በዓል የወንጌል ትምህርት የቤተ ክርስቲያንም ሕይወት መሆኑን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናንም ሆኑ ከቤተ ክርስቲያን በአፍኣ ያሉ በዓሉን የሚመለከቱ ሰዎች ሁሉ ሊረዱት ይገባል፡፡
በጥምቀቱ ሰማያት ተከፍተዋል፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ዐርፏል፤ አብ ከሰማያት “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ተናግሯል፤ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር በዚህ ተገልጧል፤ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀትን በዓል ስታከብር እምነቷንና ትምህረቷን የመሠረተችበት የወንጌል ትምህርት ይህን ነው፤ በመዝሙሮቿ፥ በቅዳሴዋና በሌሎችም የበዓሉ መገለጫ ሥርዐቶች ሁሉ የምታውጀው ይህን የወንጌል ቃል ነው፡፡
2.2. በጥምቀት በዓል የሚዘመሩ የግእዝ መዝሙሮች የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩ ናቸው፡፡
ቅዱስ ያሬድ በዜማዎቹ ሁሉ በሦስት መንገዶች ወንጌልን ሰብኳል፤ አንደኛ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል ቀጥታ በመጥቀስና በአስደናቂ ዜማ በማዜም፥ ሁለተኛ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባባት በትርጓሜ በማብራራትና ሦስተኛ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት በሕይወቱ በመኖር ናቸው፤ የጥምቀትን በዓል በሚመለከትም ቅዱሳት መጻሕፍትን ቀጥታ በመጥቀስና ምሥጢራቸውን በማብራራት ካስተማራቸው ዜማዎች በመጥቀስ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀትን በዓል ወንጌል እንደምትሰብክበት ብቻ ሳይሆን ወንጌል አድርጋ እንደምትኖረው ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡
ሀ) “ኀዳፌ ነፍስ ለጻድቃን ወተስፋ ቅቡፃን ክርስቶስ አስተርአየ ውስተ ዓለም ፤ እም ድንግል ተወልደ ክሡተ ኮነ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ ከዊኖ ሰብአ በዮርዳኖስ ተጠምቀ” (ትርጒም) “ለጻድቃን የነፍስ አሻጋሪ/መሪ/አስተማሪ (ጠባቂ)፥ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋቸው ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተገለጠ፤ ከድንግል ተወለደ፤ለዘመዶቹ እየታዘዘም በግልጥ ታየ፤ሰው ሆኖ በዮርዳኖስ ተጠመቀ” (ዋዜማ ዘጥምቀት)፡፡
ለ) “ክርስቶስ ተወልደ፤ ክርስቶስ ተጠምቀ፤ ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ፤ እሙነ ኮነ ለፀሐየ ጽድቅ አስተርእዮቱ አማን መንክር ስብሐተ ልደቱ/ጥምቀቱ፡፡” ትርጒም “ክርስቶስ ተወለደ፤ ክርስቶስ ተጠመቀ፤ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስም ዳግመኛ ወለደን፤ የጽድቅ ፀሐይ (ክርስቶስ) መገለጡ እውነት (የታመነ) ሆነ፤ በእውነት የልደቱ (የጥምቀቱ) ክብር የሚያስደንቅ ነው፡፡” (ምልጣን)
ሐ) “ነአምን በአብ ወነአምን በወልድ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ፤ እማርያም ዘተወልድ አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኀቤነ ፤ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ ከመ ይፈጽም ኵሎ ሕገ ሰብእ ፤ አስተርአየ ገሀደ፡፡” ትርጒም “በአብ እናምናለን ፤ በወልድም እናምናለን፤ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፡፡ ከማርያም የተወለደው እኛን ወድዶ ወደእኛ መጣ፤ ነቢያት የሰበኩልን እርሱ ሕግን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ ተገልጦም ታየ፡፡” (አቡን)
መ) “አስተርአየ ዘኢያስተርኢ፤ ኮነ እሙነ አስተርእዮቱ ለመድኀኒነ ክርስቶስ፤ እሙነ ኮነ አስተርእዮቱ፤ እምድንግል ተወልድ፤ እሙነ ኮነ አስተርእዮቱ፤ በሥጋ ረቂቅ እሙነ ኮነ አስተርእዮቱ፤ በሠላሳ ክረምት በዮርዳኖስ ተጠምቀ በበሕቅ ልኅቀ፡፡” ትርጒም “የማይታየው ታየ፤ መገለጡም የታመነ ሆነ፤ ከድንግል ተወለደ፤ መገለጡም የታመነ ሆነ፤ ረቂቅ የሆነው እርሱ በሥጋ ተወለደ፤ መገለጡም የታመነ ሆነ፤ በሠላሳ ዓመቱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ በየጥቂቱም አደገ፡፡”
ከላይ ያቀረበኋቸው የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች በጥምቀት በዓል ከሚዘመሩ መዝሙሮች የተወሰኑትን ለማሳያ ይሆኑ ዘንድ ነው፤ እነዚህ መዝሙሮች ሁሉም በሐዲስ ኪዳን፥ በተለይ ደግሞ በወንጌል ትምህርት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ወንጌልን ያነበበ ሁሉ በቀላሉ ይረዳቸዋል፡፡ መልእክታቸውም፡-
- የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ መገለጥ (አስተርእዮ) ይባላል፤ ቅዱስ ዮሐንስ ክርስቶስን በማየ ዮርዳኖስ ሲያጠምቀው ማንነቱን ለእስራኤል እየገለጠው/እያሳወቀ ነበር፤ በዮሐ.1÷32 “ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ” ይላል፤ በቍጥር 31 እና 33 ላይ ሁለት ጊዜ ዮሐንስ “እኔም አላውቀውም ነበር” ብሏል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ክርስቶስነቱ/መሲሕነቱ/ እና የእግዚአብሔር ልጅነቱ ተገለጠለት፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ሲያርፍበት ዐይቶና አብ የምወድደው ልጄ ይህ ነው ብሎ ሲመሰክር ሰምቶ ከዚህ በኋላ “እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬያለሁ” አለ (ዮሐ.1÷34)፡፡ መጀመሪያ ዮሐንስ ለእስራኤል ገለጠው፤ ዛሬ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀትን በማክበርና ወንጌልን በመስበክ ለዓለም ሁሉ ትገልጠዋለች፤ ያመነበትም የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፡፡
- የክርስቶስ መጠመቅ እኛን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም ለመውለድ የተደረገ የማዳን ሥራው ነው፤ “ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ” ማለትም “ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ወለደን” የሚለው የቅዱስ ያሬድ ትምህርት ይህን ያስረዳል፡፡
- የክርስቶስ ጥምቀት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት አንድ አምላክነት የተገለጠበት ምሥጢር ነው፤ በወንጌል ክርስቶስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ያረፈበት መሆኑና አብም በደመና የምወድደው ልጄ ይህ ነው ማለቱ ይታወቃል፤ ይህን የወንጌል ትምህርት መሠረት አድርጋ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ የጥምቀት በዓል “ነአምን በአብ ወነአምን በወልድ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ” እያለች ትዘምራለች፤ በዚህ መዝሙርም ወንጌልን ትሰብካለች፤ እምነቷን ለዓም ሁሉ ትመሰክራለች፡፡
- በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ የጠጠመቀው ክርስቶስ አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተሰበከውና ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ነው፤”ነቢያት የሰበኩልን እርሱ ሕግን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ” የሚለው የመዝሙሩ ሐሳብ ይህን ያረጋግጣል፡፡
እነዚህ ማሳያ አድርጌ ያቀረብኋቸው መዝሙሮች የጥምቀት በዓል የወንጌል መስበኪያ መድረክ ብቻ ሳይሆን ራሱ ወንጌል እንደሆነ ያመለክታሉ፤ እነዚህ መዝሙሮች የያዙትን ምሥጢር ሊቃውንቱ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑባቸው፥ ለራሳቸው ወንጌልን ሲማሩባቸውና ግእዝ ቋንቋን ለሚሰሙ ተማሪዎቻቸው ሲያስተምሩባቸው እንደኖሩ ሁሉ አሁን ደግሞ ሕዝብ በሚሰማው ቋንቋ በመተርጐምና ከምንጫቸው ከወንጌል ጋር በማስተሳሰር ማስተማር ይገባናል፤ ሁሉም ነገር እያለን የቤተ ክርስቲያንን ጸጋና ሀብት እንደሚገባው ባለማሳወቃችን ሌሎች ባለማወቅም ሆነ በክፉት ቤተ ክርስቲያናችንን ሲያሳንሱ መስማት እየተለመደ ስለመጣ ይህን ተገቢ ያልሆነ ነቀፋ ማራቅ ይገባል፤ ይህ የሚቻለው ደግሞ ይህን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሀብት በማስተማር ነውና ሁሉም ሊተጋ ይገባል እላለሁ፡፡
2.3. የጥምቀት በዓል ከዘጠኝ ዐበይት (ታላላቅ) የጌታ በዓላት አንዱ ነው፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን እምነትና ትምህርት ከምትጠብቅባቸውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ከምታስተላልፍባቸው መንገዶች መካከል የጥምቀትን በዓል የምታከብርበት በዓል አንዱ ነው፤ በወንጌል ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማወቅ ደግሞ ከዘጠኝ ዐበይት (ታላላቅ) የጌታ በዓላት አንዱ ጥምቀት መሆኑ አስረጅ ይሆነናል፤ እነዚህ ዐበይት በዓላትም በመጋቢት 29 ቀን የሚከበረው ትስብእት (ሰው መሆኑ)፥ ታኅሥሥ 29 (ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ 28 ቀን) የሚከበረው ልደት፥ ጥር 11 ቀን የሚከበረው ጥምቀት፥ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው ደብረ ታቦር ፥በቀመር የሚገኙት ሆሳዕና፥ ስቅለት፥ ትንሣኤ፥ ዕርገትና ጰራቅሊጦስ ናቸው። እነዚህ በዓላት ሁሉም እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን በሠራቸው ሥራዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ በዚህም ጥምቀት ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ከሠራቸው ታላላቅ የማዳን ሥራዎች አንዱ ነውና እንደ ስቅለቱና ትንሣኤው ሁሉ ከፍ አድርገን እናከብረዋለን፤ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለመስበክም ሆነ ለመኖር ከዚህ የበለጠና የከበረ የላትም፡፡
2.4. ጥምቀት በዓል ሰፊ የሆነ የስብከተ ወንጌል መድረክ ነው፡፡
የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል ከመሆን አልፎ በሀገር ውስጥም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትገኝበት ቦታ ሁሉ የምታከብረው በዓል ነው፤ ከዚህም አልፎ በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች እንኳን ቢሆኑ የእግዚአብሔርን ማዳን ሊያዩና ሊሰሙ የሚችሉበት ሰፊ መድረክ ነው፤ ለዚህም በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ ፥ የባህልና የትምህርት ድርጅት ((UNESCO) መመዝገቡ አንድ ማስረጃ ይሆናል፡፡
በበዓሉ የሚፈጸሙ ነገሮችም በምሳሌነት የሚያስተምሩት ስለ ክርስቶስ ነው፤ በየስፍራው ሁሉም ምእመናን በአንድነት ስፍራ የሚገናኙበት ታቦታትን ከመንበራቸው በማውጣትና ውኃ ባለበት ቦታ በማሳደር፥ በዚያ ቦታም ማኅሌት በመቆምና ቀድሶ በማቁረብ የምንፈጽመው ሃይማኖታዊ ሥርዐት ጌታችን ከገሊላ ዮሐንስ ያጠምቅ ወደ ነበረበት ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ የተጠመቀበትን የትሕትና ጉዞ የሚሰብክ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ምንም ነገር ስታደርግ ያለምክንያት አታደርግም፤ በሥርዐተ አምልኮትዋ ውስጥ የምትፈጽማቸው ነገሮች ሁሉ የጌታችንን የማዳን ሥራ ለመግለጥ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡
ወንጌልን ለመስበክ፥ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ ለማወጅ ከዚህ የበለጠ ታላቅ እድልና ሰፊ መድረክ ሊኖር አይችልም፤ አባቶቻችን ሰውን ከእግዚአብሔር ጋርና ሰውን ከሰው ጋር በፍቅር የሚያገናኙ እንደዚህ ዐይነት በዓላትን የሠሩት በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመሥርተው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፤ እኛም እግዚአብሔር ለአባቶቻችን የሰጠውን ጥበብ ዐውቀን፥ ይህን ሰፊ እድል እንደሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
3. ማጠቃለያ
የጥምቀት በዓል በቅዱስ ወንጌል ትምህርት ላይ የተመሠረተና ራሱም ወንጌል እንደሆነ ተመልክተናል፤ አባቶቻችን የጥምቀትን በዓል ሲሠሩ ዋና ዓላማቸው ሰዎች ሁሉ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ዐውቀውና አምነው ከእግዚአብሔር ጋር እንደኖሩ ለማስተማርና በበዓሉም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ለመሆን ነው፡፡
በዚህ ዘመን ያለን የቤተ ክርስቲያን ልጆችና አገልጋዮችም ይህን ጠንቅቀን ዐውቀን በዓለ ጥምቀትን በወንጌል ቃል እንደ ተገለጠው የክርስቶስ ትምህርት ልናከብረው ይገባል፤ በፍትሐ ነገሥት ለካህናት መስፈርት ሲቀመጥ ከተገለጡት ነገሮች አንዱ “ካህን አምላካውያት መጻሕፍትን ይልቁንም አራቱን ወንጌላት የማያውቅ ይሆን ዘንድ አይገባም” ይላል፤ “ይልቁንም ዐርባእቱ ወንጌላትን ማወቅ አለበት” የሚለው ቃል ካህን በሚሠራው ሥራ ሁሉ የወንጌልን ልዩነትና በቤተ ክርስቲያንም የተሰጣትን ልዩ ቦታ ማገልገል እንደሚገባው የሚያመለክት ነው። ከዚህ አንጻር ካህናት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በዋናነት የወንጌል ትምህርት የሚሰጥባቸው፥ ራሳቸውም በተግባር የሚታዩ ወንጌል ሥራዎች መሆናቸውን ተረድተው በበዓላት ወቅት ሌሎች ከበዓሉ ጋር የማይሄዱ ተግባራት በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ማስወገድ ይገባቸዋል፡፡
ወጣቶችም የአባቶቻቸውን መንፈሳዊ ጥበብና ክርስቲያናዊ መንገድ ተከትለው የጥምቀት በዓልን በልዩ መንፈሳዊ ሥርዐት፥ ሙሉ ትኵረታቸውን በክርስቶስ ትምህርትና ትእዛዝ ላይ አድርገው ሊያከብሩት ይገባል፤ በዚህ ዘመን ወጣቱ ከሚደነቅባቸው ነገሮች አንዱ የቤተ ክርስቲያን በዓላትን የሚያደምቅበት ልዩ ሥርዐት ነው፤ ይህ በመንፈሳዊ ትምህርትና ሥርዐት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በበዓላት ወቅት በፍቅርና በአንድነት መብላት መጠጣት የተለመደና ከጥንት ጀምሮ በእስራኤል ልማድ የሚታወቅ ነገር ቢሆንም ከበዓሉ ጋር የማይሄዱ ስካርና ጭፈራ ዐይነት ተግባራትን ምእመናን ሊርቋቸው ይገባል፤ የበዓለ ጥምቀት ዋና ጉዳይ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ማወጅ፥ ክርስቶስን ማመስገን፥ የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር ለዓለም ማሳየት ነውና በዚህ ዋና ጉዳይ ላይ ትኵረት አድርገን ጥምቀትን ልናከር ይገባል በማለት መልእክቴን በዚህ እፈጽማለሁ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያ ሀገራችንን፥ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!
መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር
በመ/ፓ/ ጠ/ቤ/ክህነት ስብከተ ወንጌልና
ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሰባኬ ወንጌል