ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም
“”” “””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ
****

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ በሥሩ ባሉ የተለያዩ ኮሌጆችና በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በመደበኛ፣ በተከታታይ፣ በርቀትና በልዩ የካህናት ሥልጠና ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ፫፻፸፮ ደቀመዛሙርትን በድኅረ ምረቃ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፊኬት ማዕረግ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒው ዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳት፣ ክቡር ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በክብር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመረቀ።

ዩኒቨርሲቲው ዳግም ለቤተክርስቲያን ተመልሶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ፲፱፻፹፯ ዓ/ም ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ደቀመዛሙርት በማፍራት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊነት፣ በአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት እና በተለያዩ ከፍተኛ የክህነት እና የአስተዳደር ሥራ ኃላፊነት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ባሉ የቤተክርስቲያናችን መዋቅር በትጋትና በታማኝነት እያገለገሉ ያሉ አባቶችና መምህራንን አፍርቷል።

ምንም እንኳ ሥራውን የጀመረው በአንድ የትምህርት ክፍል ቢሆንም በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ መዋቅሩን በማሳደግ ፫ የትምህርት ዘርፎችና ፲፪ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት በርካታ ደቀመዛሙርትን እያስተማረ እንደሚገኝ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል። የዚህን ዓመት የምርቃት ሥነ ሥርዓት ልዩ የሚያደርገው ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀት የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ተመራቂዎች መኖራቸው መሆኑ በትምህርት ዘርፍ ኃላፊው ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው ከተጠቀሱት የትምህርት ክፍሎች በተጨማሪ መደበኛ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የአብነት ትምህርቶችን እየሰጠ ከመሆኑም ባሻገር በጥናትና ምርምር ክፍሉ የተለያዩ ቤተክርስቲያንና ሀገርን የሚጠቅሙ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ይፋ ከማድረግ ባሻገር ወርሐዊ የጥናትና ውይይት መድረክ በማዘጋጀት ለሀገርና ለቤተክርስቲያን እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ተመራቂዎች በዩኒቨርስቲው የተዘጋጀላቸውን ልዩ ልዩ ሽልማቶች በዕለቱ ከተገኙ ብፁዓን አበው እጅ ተቀብለዋል።