የበዓሉ ፕሮግራም ከሚሴ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን 8:00 መነሻውን አድርጎ በደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤትና በካህናት ዝማሬ በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ 9:30 ደርሷል
መርሀ ግብሩ በአባቶች የጸሎት ፕሮግራም እስከ ጸሎተ ወንጌል ደርሶ በእለቱ የስብከተ ወንጌል መ/ር አምደ ብርሀን በመስቀሉ አስታግብአነ/በመስቀሉ አንድ አደረገን :-የሚለውን የቅዱስ ያሬድ ሃይለ ቃል መነሻ አድርገው ነገረ መስቀሉንና የመስቀሉን ታሪክ አስተምረዋል።
ከእለቱ ትምህርተ ወንጌል ቀጥሎ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መስቀል አብርሀ በከዋክብት አሰርገወ ሰማየ :እምኩሉሰ ፀሀየ አርአየ እግዚአብሔር /መስቀል አበራ ሰማይን በከዋክብት አስጌጠ ከሁሉም ይልቅ ፀሀይን አሳየ የሚለውን ወረብ አቅርበዋል።
ከሊቃውንቱ የወረብ ዝማሬ ቀጥሎ የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እጅግ መንፈሳዊ ሀሴትን በሚሰጥ አቀራረብ ደመ ወማየ አውሀዘ ለነ ደመ ወማየ /ዮም ንዜኑ ዘመስቀል እበየ የሚለውን ወረብ /ዝማሬ አቅርበዋል
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ደጀን ተስፋዬ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አቅርበው እግዚአብሔር ይህንን ታላቅ በዓል በሰላም እንድናከብር ስለፈቀደ እናመስግነዋለን ለቀጣይም አምላካችን በሰላም እንዲያደርሰንና ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ ሁሉም ሰው በሰላም ወጥቶ የሚገባባት አገር እንድትሆን ሁሉም ህዝበ ክርስቲያን መጸለይ አለበት በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈው በበዓሉ በክብር እንግድነት ለተገኙት
1ኛ.የከሚሴ ከተማ ከንቲባ ክቡር ሸሪፍ ቃሲም
2ኛ.የከሚሴ ከተማ ብልጽግና ጽ/ቤት ቅርንጫፍ ኀላፊ ወ/ሮ ዘምዘም መሐመድ
3ኛ.የከሚሴ ከተማ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሳዳም ሁሴን
4ኛ. የከሚሴ ከተማ የፖለቲካ አደረጃጀት ኀላፊ መሀመድ አሊን
አመስግነው ክቡር ከንቲባው የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል።
ክቡር ከንቲባውም ለመስቀሉ በዓል ታዳሚዎች እኔ በዚህ በዓል በመገኘቴ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል መስቀል ከአካባቢ ከአገር አልፎ በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒስኮ የተመዘገበ ታላቅ በዓል ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምትጠይቀው ኢያንዳንዱ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መልስ እንሰጣለን በማለት ንግግራቸውን በምስጋና ዘግተው ከአባቶች ጋር በመሆን የደመራ መለኮስ ፕሮግራም አካሂደዋል።
መረጃው የከሚሴ ሀገረ ስብከት ህዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።