ብሔር አይለየንም
ብሔር የሚለው ቃል ከግእዝ የተገኘ ቃል ሲሆን፤ ሲተረጐምም ብዙ ሐተታ አለው። ከአሉት ሐተታዎች መካከል ለግንዛቤ ያህል በአጭሩ፦
1ኛ) ብሔር «ቦታ» ተብሎ ሲተረጐም፥ (ኢሳ. 49፥20፤ ኢዮብ 28፥1)
2ኛ) ብሔር «ግዛት» (አውራጃ) ተብሎ ሲተረጐም፥ (ዮናስ 1፥8፤ ኤር. 1፥1-2)
3ኛ) ብሔር «ነገድ» (ወገን) ተብሎ ሲተረጐም፥ (1ኛነገ. 14፥24፤ 1ሳሙ. 14፥24)
4ኛ) ብሔር «ሰዓት» ሲሆን፥ (የሐዋ.ሥራ 2፥15)
5ኛ) ብሔር «የመጽሐፍ ክፍል» ሲሆን፥ ብሔረ ኦሪት፥ ብሔረ ነገሥት ይባላል።
6ኛ) ሰማይና ምድር በሙሉ ማለት ሰማይ ከነግሱ፥ ምድር ከነልብሱ፥ በጠቅላላ መላው ዓለም ላዩም ታቹም የአንድ አምላክ ግዛት ስለሆነ በምሳሌ «ብሔር» ተብሎአል። «ከመዝ ይቤ እግዚአ-ብሔር — የዓለም ጌታ (ፈጣሪ) እግዚአብሔር እንዲህ አለ» (ኢሳ. 66፥1)።
ከዚህ በላይ ከተራ ቍ. 1-6 ከሰፈረው በመነሣት «ብሔር» የሚለው ቃል በልዩ ልዩ መልክ ሊተረጐም እንደሚችል በግልጽ መረዳት ይቻላል።
በመሆኑም በዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ ብሔሩ አንድ ነው፤ የተለየ ብሔር የለውም፤ ምክንያቱም የአንድ እግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ። ልበ አምላክ ዳዊት እንዲህ ይላል፦ «ሰማየ ሰማያት ለእግዚአብሔር ምድርሰ ወሀበ ለዕጓለ እመሕያው — ሰባቱ ሰማያት የእግዚአብሔር ማደሪያ ሲሆኑ፤ ምድር ግን ለሰው ልጅ ሁሉ መኖሪያ ልትሆን ፈጥሮ ሰጠ» (መዝ. 113፥24)።
ይህ ከላይ የተጠቀሰው ኀይለ ቃል ዓለም (ምድር) በመላዋ ለሰው ልጅ ሁሉ ብሔር ሳይለይ የጋራ መሆንዋን ነው። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር የተሰጠን የበረከት ምድር ባለቤቶች እንደመሆናችን ተመስገን ይህን የሰጠኸን ብለን ልናመሰግንና መላዋ ቅድስት ኢትዮጵያ ሀገራችን የሁላችን፥ የጋራችን ናት ማለት አለብን።
ለምሳሌ ከዚህ በታች ያሉትን የቦታ መዳረሻዎች እንይ፦ ከሐረር እስከ ጎንደር፥ ከመቀሌ እስከ ባሌ፥ ከጎሬ እስከ ሽሬ፥ ከአኵስም እስከ ጎጃም፥ ከወሎ እስከ ደምቢዶሎ፥ ከጎዴ እስከ ጠገዴ፥ ከሲዳሞ እስከ ደብረ ዳሞ፥ ከሸዋ እስከ አድዋ፥ ከመተሐራ እስከ ሑመራ፥ ከአዲግራት እስከ ክብረ መንግሥት፥ ሌሎችም ስማቸው ያልተጠሩ በርካታ ቦታዎች በሙሉ የቦታ መጠሪያ ስምን (መለያን) እንጂ የሰው ተፈጥሮን ወይም የብሔር ልዩነትን አያመለክቱም።
ሰው በመላው አንድ ቅርጽ አንድ ባሕርይ ያለው፥ ከአንድ አባት ከአንድ እናት (አዳምና ሔዋን) የተገኘ የምድር ገዥ ነው። ቋንቋም በኋላ የመጣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሆነ የቋንቋ ልዩነት የተፈጠረው በኋላ በቅጣት መልክ ከእግዚአብሔር የተሰጠ (ዘፍ. 11፥7-10) እንጂ ልዩነቱ ቀድሞ የነበረ አይደለም። ቋንቋ የሰዎች መግባቢያ መሣሪያ እንጂ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ምክንያቱም ቋንቋ በምንም ዓይነት መመዘኛ ብሔር የለውምና ነው።
ቋንቋና ሃይማኖት
ቋንቋና ብሔር የተለየ ሃይማኖት የላቸውም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቋንቋ በብሔር፥ በዘር በጎሳ ሳትለይ ሁሉንም በአንድ ዐይን በመመልከት በእኩል ታስተምራለች። በስመ ሥላሴ አምኖ የተጠመቀ ከቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ሲቀርብ አንተ ማን ነህ? አንቺስ ማን ነሽ? ምን ቋንቋ ትናገራለህ? ትናገሪያለሽ? ሳትል፦ ወለዘሂ መጽአ ኀቤየ ኢይሰድዶ ወኢያወጽኦ አፍኣ — ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም» (ዮሐ. 6፥37) የሚለውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ እንኳን ኢትዮጵያዊ ይቅርና የውጭ ዜጋም ቢሆን አማኝ ሆኖ የተገኘ ሁሉ ፆታ (ወንድ ሴት)፥ ዕድሜ (ሕፃን ሽማግሌ)፥ አፍሪካዊ አውሮፓዊ፥ ቀይ ጥቁር፥ አጭር ረጅም ሳትል፥ የሕይወት ታሪካቸው፥ ተጋድሎአቸውና ቃል ኪዳናቸው በሙሉ በክብር መዝገብ ማለትም በስንክሳር ላይ፥ እንዲሁም ገድል፥ ድርሳንና ተአምር እየጻፈች ለትውልድ ታስተላልፋለች፤ በቃል ኪዳናቸውም ትማጸናለች።
ገዳማትና አድባራት
በስማቸውም ገዳማትና አድባራት በመመሥረት፥ በስማቸውም በሚፈልቁ ማየ ጸሎትና በሚከሰቱ አስደናቂ ተአምራቶች ይከሰታሉ፥ ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡ፥ የማይፈወሱ ናቸው ተብለው በምድራዊ ሕክምና የሚታመኑ ሕመሞች ሳይቀሩ ሲፈወሱና ሲድኑ ይታያሉ። ምክንያቱም በሰው ዘንድ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይቻል የለምና ነው (ማር. 9፥23፤ 11፥23)። ፍጹምና ጥርጥር የሌለው እምነት ይዘን ከተገኘንም የተመኘነውን ሁሉ የማግኘት ዕድላችን የሰፋ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በልቡአ ሙሉነት በክብረ ቅዱሳን ላይ አምና የምታስተምረው።
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ መሥራችዋና እንደ ፈጣሪዋ እግዚአብሔር ሰው ለሆነ ሁሉ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ዜጋ፥ ቀለም፥ ወንድ ሴት፥ ሕፃን ሽማግሌ ሳትል በእኩል ዐይን እንደምታይና እንደምትወድ ሁሉ፥ እኛ ኢትዮጵያውያንም ከላይ በመግቢያው ላይ የጠቀስናቸው በተለያየ ስም የሚጠሩ ቦታዎች በሙሉ የጋራችን መሆናቸውን ከልብ በመረዳትና እንደ ጥንቱ ብሔር የማይለየን መሆኑን አምነን በመቀበል እንደ አንድ ልብ መካሪ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነን ሀገራችንንና ሕዝባችንን በሰላምና በፍቅር ለመጠበቅ እንድንችል የፍጥረታት አስገኝ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን የ2015 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት የሰላምና የፍቅር በዓል ያድርግልን፤ አሜን።
ርእሰ ደብር መሓሪ ኀይሉ
የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት
ዋና ሥራ አስኪያጅ