ትምህርት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ትምህርት ለሰው ልጆች መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገት በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ‹‹ካልተማሩ አያውቁ፤ ካላወቁ አይጸድቁ›› የሚለው የማኅበረሰብእ ብሂልም ሁሉም ሰው ለትምህርት ትኩረት መስጠት እንዳለበት የሚያመለክት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በዕውቀት ያልተደገፈ አገልግሎት ሁሉ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮት ሲገጥመው የመቋረጥ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም በመንፈሳዊ አገልግሎትም ሆነ በማኅበራዊ አገልግሎት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ለምን? ስለምን? ለማን? የሚሉ ጥያቄዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲነሡ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መመለስ ይገባል፡፡ ይህንም ማድረግ እስከተቻለ ድረስ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ተግዳሮቶችን በቀላሉ ማለፍ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት እስከ ዛሬ ለትምህርት ቅድሚያ ትሰጣለች ትምህርቱም በቃልና በተግባር የሚከናወን ነው፡፡ በቃልና በተግባር ስለሚከናወነው መንፈሳዊ ትምህርት ከማየታችን በፊት ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ትምህርት አስፈላጊነት ምን እንደሚል እንመለከታለን፡፡
‹‹ወትምህርትከ ዘያጸንዐኒ ለዝሉፉ ወተግሣጽከ ውእቱ ዘይሜህረኒ — ትምህርትህ ለዘለዓለም ያጸናኛል፤ የሚያስተምረኝም ተግሣጽህ ነው (መዝ. 17፥35)፤ ‹‹ሀቦ ለጠቢብ ምክንያተ ወያፈደፍድ ጥበበ አምሮ ለጠቢብ ወይዌስክ ጥበበ — ለጥበበኛ ሰው ትምህርትን ስጠው ጥበብን ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው ዕውቀትን ያበዛል፤ (ምሳ. 9፥9) ‹‹ለትምህርተ መጻሕፍት አልቦ ዘይጸግቦን ወፈድፋደሰ እለ ይኄልዩ ጥበበ — የመጻሕፍትን ትምህርት ማንም አይሰለችም፤ ይልቁንም ጥበብን ለተማሩ ሰዎች (ጰላድዮስ ቄርሎስ ምዕ. 1)
ትምህርት ለማን ?
ስለ ትምህርት ስናወሳ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ዕውቀት ማንሣት ግድ ይለናል። በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረውና በልጅነት የከበረው የሰው ልጅ ፊደል የሚያስቆጥረው መምህር፥ የሚማርበት መማሪያ መጽሐፍ፥ የሚመራበት ሕግ ሳያስፈልገው በተፈጥሮ በተሰጠው ዕውቀት እንደ ቅዱሳን መላእክት እያመሰገነ እንዲኖር እንጂ በቀይ በጥቁር ቀለም በተጻፈ መጽሐፍ እንዲማር ሥጋዊ ደማዊ መምህር እንዲያስተምረው አልነበረም፤ ‹‹እስመ ኢተወልደ ሰብእ ለዝ ከመዝ በቀለም ወበማየ ሕመት ያጽንዑ ሃይማኖቶሙ እስመ ኢተፈጥረ ሰብእ ዘእንበለ ከመ መላእክት ከመ ይንበሩ ጻድቃነ ወንጹሓነ — እንደ መላእክት ጻድቃንና ንጹሓን ሁነው እንዲኖሩ ነው እንጂ ሰው ለእንደዚህ ያለ ሥራ አልተፈጠረም ነበርና በቀይ ቀለምና በጥቁር ቀለም ሃይማኖታቸውን ሊያጸኑ ሰው ለእንደዚህ ያለ ሥራ አልተወለደም ነበርና›› (ሄኖክ 19፥24)። የሰው ልጅ አምላኩ እግዚአብሔር የሰጠውን የጸጋ ዕውቀት በምክረ ከይሲ/ሰይጣን ተታሎ በመነጠቁ የሚያስተምረው መምህር፥ የሚማርበት መጽሐፍ፥ የሚመራበት ሕግ የሚያስፈልገው ሁኖተገኝቷል፡፡ ከዚህ የተነሣ የሰውን ድኅነት የሚሻ ልዑል እግዚብሔር ለአዳም ልጅ ሁሉ የሚማርበትን ፊደል ሰጥቶታል፤ የሚስተምረውንም መምህር ሹሞለታል። የሰው ልጅ ከፊደል ጋር የተዋወቀው በአዳም ሰባተኛ ትውልድ በሄኖስ እንደሆነ በቤተክርስቲያናችን ይታመናል፡፡ በመሆኑም ትምህርት ከድቀተ አዳም በኋላ ለሰው ልጅ የተሰጠ መሆኑን ከቃለ ሄኖክ መረዳት ይቻላል፡፡
ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ከማንም ያልተቀበለችው የራሷ የሆነ ሀገር በቀል ሥርዐተ ትምህርት አላት፡፡ ትምህርት ለሰው ልጆች የአእምሮ ማጎልበቻ፥ የችግር መግቻ፥ የሰብአዊነት መታወቂያ፥ ከድንቁርና መላቀቂያ፥ በተግባራዊነቱ መጽደቂያ መሆኑን በመረዳት፥ ባቋቋመቻቸው የአብነት ትምህርት ቤቶችና በአሁኑ ጊዜ ኮሌጆችን ጨምሮ ሕጻናት ከፊደል ጋር እንዲተዋወቁ፥ ካለማወቅ እንዲርቁ፥ በአእምሮ እንዲልቁ፥ በጥበብ እንዲራቀቁ ስታደርግ ኑራለች፤ በአሁኑም ሰዓት እየተገበረችው ትገኛለች፡፡
እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ትምህርት አይታሰብም ነበር፡፡ ከሁሉም የሚደንቀው እማራለሁ ብሎ ወደ እርሷ የመጣውን ሁሉ በራሷ ፈቃድ ሃይማኖት፥ ጾታ ሳትለይ ከፊደል ጋር አስተዋውቃለች፤ ለንባብም አብቅታለች። ይህንም እውነታ በታሪክ ተረድተናል፤ ከክርስትናው ውጪ ያሉ ወገኖቻችን በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ሲመሰክሩም ሰምተናል፡፡
ሀ. ትምህርት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ
መዝሙረኛው ዳዊት ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ሲል ሀገረ እግዚአብሔርነቷን የመሰከረላት ኢትዮጵያ፥ ከልደተ ክርስቶስ በፊት በውስጧ ትምህርትና የአምልኮ ሥርዐት እንደነበር ኢትዮጵያዊው ጀንደረባ እንዲሁም ሊቃውንት ይመሰክራሉ፡፡ ‹‹ሠለስተ ጊዜያተ በዓመት ግበሩ ሊተ በዓለ — በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል አድርጉልኝ ባለው ቃል መሠረት›› (ዘፀ. 23፥14) ሥርዐተ አምልኮውን ለመፈጸም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘውና ሥርዐተ አምልኮውን ፈጽሞ ሲመለስ ‹‹እንደ በግ ሊታረድ መጣ የበግ ጠቦት በሸላቹ ፊት እንደማይናገር እንዲሁ አፉን አልገለጠም›› እያለ የኢሳይያስን የትንቢት መጽሐፍ እያነበበ በመንፈስ ቅዱስ የተጐበኘው፥ በፊልጶስ የታየው ኢትዮጵያዊው ጀንደረባ (ባኮስ) በኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ለመኖሩ ታላቅ ምስክር ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤት ባይኖር ለንባብ የሚያበቃ ዕውቀትን ከማን አገኘ? ኢየሩሳሌም ነው እንዳንል ወደ ኢየሩሳሌም ሂዶ ለፈጣሪው ለመስገድ የተነሣው ከኢትዮጵያ ነው፤ ወደ ኢየሩሳሌም ሂዶ ለመስገድ የሚያስችለውን ዕውቀት ከኢትዮጵያ ካላገኘ ከማን ሊያገኝ ይችላል? እንዴትስ ለመሄድ ተነሣሣ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሣታቸው ግድ ነው፡፡
ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር›› እንዳለ፥ ቀደም ሲል ከታቦተ ጽዮን ጋር በቀዳማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ያነበበው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የትንቢቱን መጽሐፍ እያበበ ፅንሰ ሐሳቡን መረዳት ሲሳነው በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት፥ በወንጌላዊው ፊልጶስ አስተማሪነት የብሉዩን ንባብ በሐዲስ ኪዳን የገቢር ትርጓሜ ተርጒሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምኖ በመጠመቅ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝቶ በልጅነት ከብሮ ደስተኛ ሆኖ ተመልሷል፡፡ (ግብ. ሐዋ. 8፥27-39)
ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የክርስትና እምነትን በብሔራዊ ደረጃ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አባትነት በደጋጉ ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ መሪነት በአራተኛው ምእት ዓመት በዐዋጅ ለሁሉም ከማዳረሷ በፊት ከኢየሩሳሌም ቀጥላ ከሁሉም አህጉር ቀድማ በመጀመሪያው ምእት ዓመት በ34 ዓ.ም በጃንደረባው (ባኮስ) አማካይነት የክርስትና እምነትን ተቀብላለች፤ በብሉይ ኪዳን ‹‹ይወርዳል፤ ይወለዳል … የሚለውን የትንቢት ንባብ ‹‹ወረደ፥ ተወለደ፥ ተጠመቀ፥ መከራ ተቀበለ፥ ሞተ፥ ተነሣ፥ ዐረገ፥ ዳግመኛ ይመጣል›› እያለች በመንፈሰ ረድኤት ያይደለ በመንፈሰ ልደት እየተረጐመች ለምስጋና ወደ እግዚአብሔር የተዘረጉ እጆቿ ሳይታጠፉ ኑራለች ወደፊት ትቀጥላለች፡፡
ለ. ትምህርት ድኅረ ልደተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ
የሐዲስ ኪዳን መዳረሻ ሁኖ ሲያገለግል የቆየው የብሉይ ኪዳን ትምህርት ታቦተ ጽዮንን አጅበው በመጡ ሌዋውያንና ተከታዮቻቸው በየዘመናቱ ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በሐዲሱ ዘመን በሐዲሱ ትውልድ እጆቿን ዘወትር ዘርግታ የምታመሰግነውንና የምትማፀነውን የኢትዮጵያን ልመና እግዚአብሔር ተቀብሎ ሰማያዊውን ትምህርት በልጇ ቅዱስ ያሬድ አማካይነት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሰጣት፡፡
መሪጌታ ልሳነወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ ‹‹ጥንታዊ ሥርዐተ ማሕሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ›› በሚል ርእስ በጻፉት መጽሐፋቸው ‹‹አፄ ገብረ መስቀል መስከረም 25 ቀን በ534 ዓ.ም እንደ ነገሡ ቅዱስ ያሬድን የወደደ ሀገሪቱ ኢትዮጵያንም የመረጠ እግዚአብሔር ኅዳር 5 ቀን አሮድዮን የሚባሉ ሦስት ነጫጭ ወፎችን በነግህ /በጧት/ ከገነተ ኤዶም ላከለት፤ ቅዱስ ያሬድ በሚያስተምርበት ስፍራ አንጻር በአየር ላይ ረበው ያሬድ ሆይ፥ የበቃህ ብፁዕነህ አንተን የተሸከመች ማሕፀንና አንተን አጥብተው ያሳደጉ ጡቶች የተመሰገኑ ናቸው ብለው በግእዝ ቋንቋ አመሰገኑት፡፡
ወሶበ ሰምዐ ዘንተ ቃለ ያሬድ አንቃዕደወ ሰማየ ወነጸረ ሠለስተ አዕዋፈ ወይቤሎን እምአይቴ መጻእክን እምገነተ ኤዶምኑ ዘትትናገራ ከመ ሰብእ ወትቤሎ አሐቲ ዖፍ እምሠለስቱ አዕዋፍ ተፈነውነ ኀቤ ከእምገነተ ኤዶም ከመ ንንግርከ ወንዜኑከ ዘከመ ትነሥእ ማሕሌተ እምዕሥራ ወአርባዕቱ ካህናተ ሰማይ ወእንዘ ይትናገራ ዘንተ ተመሥጠ ያሬድ ወእማንቱ አዕዋፍ ቦአ ውስተ ገነተ ኤዶም ወተሠወራ እምአዕንቲሁ — ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን ወፎች አየና እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችሁ፥ ከገነተ ኤዶም ነውን አላቸው።
ከሦስቱ ወፎች አንዷ ወፍ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌት ሰምተህ እንድታዜም ዕድል የተሰጠህ መሆኑን እንነግርህና አበሥርህ ዘንድ ከገነተ ኤዶም ወደ አንተ ተልከናል አለችው። ይህን እየተነጋገገሩ ሳሉ ወዲያው ያሬድ ወደ ገነተ ኤዶም ተመሠጠ /ተነጠቀ/ ወደ ገነተ ኤዶምም ገብተው ከዐይኑ ተሰወሩ ቅዱስ ያሬድም በዚያ ቁሞ ሳለ እነዚያ ወፎች በረው ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሲገቡ እርሱም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ገባ፤ በዚያም ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔርን በእንዚራ በአርጋኖንና በመሰንቆ ከፍ ባለ ዜማ ዘወትር ሲያመሰግኑት ሰማ፡፡
ቅዱስ ያሬድም ይህን ማሕሌት በሰማ ጊዜ ካለበት ቦታ ዘሎ ወደ እነርሱ ለመግባት ፈለገ ወደዚያ መግባት አልተቻለውም፡፡ እነዚያ ወፎችም መጡና ከእነርሱ አንዷ ወፍ፦ የሰማኸውን ማሕሌት አላስተዋልክምን ብላ ተናገረችው። ያስተዋልኩት ነገር የለም አላት፡፡ ወትቤሎ አነ «እነግረከ በዘትሌቡ ጸውዕ ስሞ ሐዲሰ ለእግዚአብሔር ዝ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወትነሥእ ማሕሌተ እምዕሥራ ወዐርባዕቱ ካህናተ ሰማይ በበዜማሁ — እኔ በምታስተውልበት ነገር እነግርሃለሁ የእግዚአብሔርን አዲስ ስም ጥራ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም በየዓይነቱ ዜማን ትማራለህ» አለችው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሲጠራ ሰማያዊ ዜማ ተገለጠለት፡፡ ወዲያውም በግእዝ፥ በእዝል በአራራይ ማዜም ጀመረ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደሚያስተምርበት ቤተ ቀጢን ተመልሶ ፊቱን በምሥራቅ አቅጣጫ ታቦተ ጽዮን ወደአለችበት አዙሮ ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ›› ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድ ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል የጽዮን መጀመሪያዋ እግዚአብሔር ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም የድንኳኑን ሥራ እንዴት መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው›› በማለት ልዩ በሆነ ጣዕመ ዜማ አዜመ፡፡ (ዘፀ. 25፥8)
በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ በተበረከተው ሰማያዊ ዜማ ኢትዮጵያ በዕውቀት አበራች፥ ልዕልናዋን በዓለም አሳያች ከራሷም አልፋ የአፍሪካ ኩራት ለመባል በቃች፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በግእዝ ቋንቋ በብራና የተጻፈ ወንጌል ያላት እኮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያን ናት ይህች ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ የተግባር ብርሃን ያበራችና እያበራች ያለች መሆኗ እየታወቀ በዘመናችን በቢጽ ሐሳውያን ኢትዮጵያን ወደኋላ እንደ ጎተተች ተደርጎ መቅረቡ አላዋቂነትን የሚሳይ ጨለምተኝነትን የሚያንጸባርቅ የስሕተት ንግግር ነው፡፡
ትምህርት ለዕውቀት ወይስ ለሕይወት?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀትን ከሕይወት ሕይወትን ከዕውቀት አዋሕዳ ታስተምራለች ሕይወት የሌለው ዕውቀት (ትምህርት) ነፍስ የተለየው በድን ማለት ነው መማርም ሆነ ማስተማር የሚያጸድቀው ሲተገበርነው፡፡ ዕውቀትና ሕይወት የተስማሙለት ታላቁሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቦኑ በአጽምዖ መጻሕፍት ይጸድቁ በቅድመ እግዚአብሔር አኮኑ ዳእሙ በገቢሮቱ ይጸድቁ — በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይጸድቁምና (ሮሜ 2፥13) እንዳለ፥ ለዕብራውያን በጻፈው መልእክቱም፦ ‹‹እስመ ስሙዓን ንሕነ በከመ ሰምዑ እልክቱ ወባሕቱ ለእልክቱሰ ኢበቊዖሙ ቃል ዘሰምዑ እስመ ኢተቶስሐ ልቦሙ በሃይማኖት ምስለ እለ ሰምዑ — ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምሥራች ተሰብኮልናልና ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም›› (ዕብ. 4፥2)፡፡ በሥርዐተ ቅዳሴውም ‹‹እግዚእነ ወአምላክነ ፈኑ ላዕሌነ ብርሃነከ ወጽድቀከ ወአብርህ አዕይንተ አልባቢነ ወሕሊናነ ወረስየነ ድልዋነ ንስማዕ ቃለ ወንጌልከ ቅዱስ አኮ ዘንሰምዕ ባሕቲቱ አላ ንግበር በከመ ሰማዕነ ከመ ይፍረይ ላዕሌነ ፍሬ ሠናየ ህየንተ አሐዱ ሠላሳ ወስሳ ወምእተ — ጌታችን አምላካችን ሆይ፥ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክልን፤ የልቡናችንና የሕሊናችን ዐይኖች አብራልን፤ የቅዱስ ወንጌልህን ቃል በመጨከን እንሰማ ዘንድ የበቃን አድርገን፤ የምንሰማ ብቻ አይደለም፤ እንደ ሰማን ልንሠራም ነው እንጂ ስለአንዱ ፈንታ ሠላሳ፥ ስልሳና መቶም መልካም ፍሬን በላያችን ያፈራ ዘንድ…›› ይላል (ሥርዐተ ቅዳሴ ቊ. 187)፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስገነዝቡን የተማርነውንና የምናስተምረውን ቃል በተግባር ላይ መዋል እንዳለብን ነው የተማርነውን በተግባር ላይ ካላዋልነው ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ለኢትዮጵያ ዕድገት ካበረከተቻቸው በጥቂቱ
- ትምህርት፦ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷ ፊደል፥ ቀመር፥ ሥርዐተ ትምህርት ያላት በራስዋ ማንነት የቆመች መጽሐፍ ቅዱስን ከሀገር በቀል ትምህርቷ ጋር አስማምታ የሀገር መሪዎቿን የአስተዳደር ጥበብን፥ ፍቅረ ሀገርን ፈሪሀ እግዚአብሔርን እያስተማረች አንድነቷን ያስጠበቀች ከእርሷ ተወልደው ከእርሷም ተምረው ባደጉ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ልጆቿ ነው፡፡
- ታሪካዊ ቅርስ፦ ከርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ጀምሮ እስከ እንጦጦ ማርያም ድረስ በሁሉም ክልሎች ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኙ ዕድሜ ጠገብ የብራና መጻሕፍት፥ የወርቅ፥ የብር፥ የናስና የዕፅ መስቀል፤ ከበሮ፥ ጸናጽልና መቋሚያ፥ ልብሶ ተክህኖ፥ ዘውዶች ወዘተ. በአጠቃላይ በተለያየ ምከንያት ከሀገር የወጡና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት ከቤተ ክርስቲያን የተገኙ የኢትዮጵያን ሥልጣኔና ዕድገት የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የሚመጡት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ቅርሶቿን ለመጎብኘት የበዓል አከባበር ሥርዐቷን በተለይ በዓለ ልደት፥ ጥምቀትና መስቀልን ለመመልከት እንደሆነ ሁሉም የሚረዳው ሐቅ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን፦ ኢትዮጵያን አሳደገች እንጂ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ጎተተች እንዴት ሊባል ይችላል?! ==
- ነጻነት ከእነ ክብሩ፦ በታሪክ እንደሚታወቀው የአፍሪካ ሀገሮችን ምዕራባውያን እንደ ቅርጫት ሥጋ ተከፋፍለው በቅኝ ግዛት ሲያንበረክኳቸው ኢትዮጵያ ግን ለማንም ወራሪ ያልተበረከከች፥ ባህሏን፥ ታሪኳንና ክብሯን ጠብቃ የኖረች፥ ማንነቷን ያላስደፈረች፥ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገች መሆኗ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ለነጻነቷ ያገዛት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለኢትዮጵያ ይዕቀባ እመዓተ ወልዳ›› እያለች በሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በእያንዳንዷ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በጋራ በሚጸለየው ጸሎት ታስባታለች፤ ጸሎቱም ሰይፍ ጋሻ ሁኗት በራሷ ማንነት ተከብራ አንድትኖር አስችሏታል፡፡
ሁለተኛው ነጻነቷን ተጋፍቶ ድንብሯን ጥሶ የመጣውን የፋሽሽት ጣሊያን ወራሪጠላት ለመመከት ታቦቷን ይዛ በንጉሠ ነገሥት ዐጼ ምኒልክ መሪነት ሕዝቡ ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን ተሰልፎ የሀገር ወራሪን እንዲመክት አስቻላለች፡፡ ከአርባ ዓመት በኋላ የቀደመ ሽንፈቱን ለማካካስ ቢመጣም ሰማዕታተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያንና አቡነ ሚካኤልዘጎሬን ፊት ለፊት አሰልፋ ‹‹ ለሀገራችሁና ለሃይማኖታችሁ መሥዋዕት መሆን አለባችሁ›› በማለት መሥዋዕትነቷን በተግባር አረጋግጣለች፡፡ ‹‹በጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› እንዲሉ የደም ዋጋ ከፍላ የሀገር አንድነትን ያስጠበቀች ቤተ ክርስተያን መከበርና መሸለም ሲገባት ትምህርቷን የሚበርዙ፥ እውነተኛ ታሪኳን የሚሠርዙ፥ በምቀኝነት የደነዘዙ ኢትዮጵያውያን ሁነው የኢትዮጵያን አንድነት የማይወዱ ጎረምሶች እያፋቸሉባት ይገኛሉ፡፡
በመጨረሻም በረከታቸው ይድረሰንና የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያን የታሪክ መጽሐፋቸው ቤተ ክርስቲያናችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቻቸውን በጽሑፋቸው እንደገለጡት ማጠቃለያ አድርጎ ማቅረብ እውነታውን የሚያረጋግጥ ሆኖ በመገኘቱ እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርቦአል፡፡
- ሙሉ ትምህርት
- ፍጹም ቋንቋ ከእነ ፊደሉ
- ሥነ ጽሑፍ ከነጠባዩ ከነሙያው
- ኪነ ጥበብ በየዓይነቱ
- ሥነ ጥበብ በየመልኩ
- ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ
- እምነት ከነፍልስፍናው
- ነፃነት ከነክብሩ
- አንድነት ከነጀግንነቱ
- ሀገር ከነድንበሩ ከነፍቅሩ
- ስም ከነምልክቱ
ይህን ሁሉ ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ብርሃንን አላበራችም፤ ኢትዮጵያን አላሳደገችም ማለት ይቻላል? ዘቦ ዕዝን ሰሚዐ ለይስማዕ (ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ)፡፡
መጋቤ ሐዲስ ኀይለ እግዚእ አሰፋ
የሰ/ብ/ቅ/ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን