ዱራሜ
====
ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””

በዚሁ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ የዱራሜ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳዊት አሽሮ እና የከንባታ ዞን የመንግስት ተጠሪና የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ ስዩም ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም፦ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፊደል ቀርጻ፣ ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣ ለትምህርትና ዕውቀት መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች።” ያሉት የከተማዋ ከንቲባ አገራችን ኢትዮጵያን የውጭ ወራሪዎች ሊወሯት በመጡ ጊዜ ታቦታቷን ይዛ ህዝቧን አስተባብራ ጠላቶችን በመመከት ሕዝብን ከነክብሩ አገርን ከነዳር ድንበሩ ለትወልድ ያስተላለፈች ቀድምት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ገልጸው “ቤተክርስቲያኗ ጥንታዊትና ታሪካዊት የአገር ባለ ውለታ በመሆኗ ክብር ይገባታል” ብለዋል።

ወደፊትም በሰላምና በሀገር እድገት ዙሪያ ታላቅ አስተዋጽኦ የምታበረክት ተቋም መሆኗን የገለጹት የመግሥት የሥራ ኃላፊዎቹ እንኳን ደህና መጡ በማለት ለብፁዕነታቸው የመልካም ምኞት መግለጫ መልክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው “ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ወደዚህ ቦታ የላከችኝ ለመንፈሳዊ ተልዕኮ ብቻ አይደለም ይልቅኑ ሕዝቡ በሚያከናውነው ኢኮኖሚያዊና ልማታዊ ሥራዎች የበኩሌን አስተዋጽኦ ማበርከት አንድችል ነው ቅዱስ ሲኖዶስ የላከኝኝ ብለዋል።” አያይዘውም “ይህን ደግ ህዝብ እንድናገለግል እኔንና እናንተን ለመረጠ እግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል።” ካሉ በኋላ የተሰጠንን ኃላፊት በመወጣት መንፈሳዊ በረከትን ለማግኘት ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

በዚሁ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ለመንበረ ጵጵስና መሥሪያ የሚሆን ቦታ እንዲሰጠው ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን የመንበረ ጵጵስና መሥሪያ ቦታ ጥያቄው በከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እንዳገኘ ወዲያውኑ የመንበረ ጵጵስናውን ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችል የሁለት ሚሊየን ብር በጀት በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ መመደቡ ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባም ጥያቄው በዚህ ቦታ መቅረቡንና በእምነት ቦታውን እንደምታገኙ ተማምናችሁ ጥያቄ ማቅረባችሁንና በጀት መመደባችሁን አደንቃለሁ ካሉ በኋላ ጥያቄው በሕጋዊ መልኩ እንዲቀርብ አሳስበው ጥያቄው አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት እንዲችል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰሜን አሜሪካ የሚኔንሶታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ስምኦን ጴጥሮስ ሆይ ከእነዚል ይልቅ ትወደኛለህን?” በማለትጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስምኦን ጴጥሮስ ያቀረበለትን ጥያቄ ርዕስ በማድረግ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ሊቃውንት ቅኔ፣ የሰንበት ትምቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን ለብፁዓን አባቶች ከሀገረ ስብከቱ፣ ከየወረዳው ቤተክህነት ጽሕፈት ቤትና ከምዕመናን የተዘጋጀ ሥጦታ ተበርክቶ እንደተጠናቀቀ በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል ሲል የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙንት ክፍል በላከልን ዘገባ ገልጿል::