የቅዱስነታቸው የሕይወት ታሪክ እንደሚከለው ይነበባል።

(ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም.)
ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር፤
– ብፁዓን ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት፤
– ክቡራን የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፤
– ክቡራን አምባሳደሮች፤
– የተከበራችሁ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የመጣችሁ የሃይማኖት ኃላፊዎች፤
በአጠቃላይ በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ዕረፍት ምክንያት በዚህ ካቴድራል የተገኛችሁ የኃዘናችን ተካፋዮች ሁላችሁ፤
‹‹ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር››
‹እግዚአብሔር ባወቀ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት በፈቃደ እግዚአብሔር የጻድቅ ሰው ሞት የከበረ ነው› ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት /መዝ. 115፡6/
የቅዱስነታቸውን ልደት፣ ዕድገትና ትምህርት በተመለከተ
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ክፍለ ሀገር በአድዋ አውራጃ በመደራ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ አራደች ተድላ ተወለዱ፡፡ ከስድስት ዓመታት ዕድሜ ጀምሮ እስከ ዕውቀት ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የአበው መነኮሳትን ሥርዓት የተከተለ ገዳማዊ ኑሮን በአባ ገሪማ ገዳም እያጠኑ አባቶችን እያገለገሉ አደጉ፡፡ ቀጥሎም ትምህርታቸውን በበለጠ ለማስፋፋት በጭህና በአባ ሐደራ ገዳማት በአጠቃላይ በሦስቱም ገዳማት በመዘዋወር ለዐሥራ አምስት ዓመታት፣
 ከመምህር ወልደ ሐዋርያት
 ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር፣
 ከመምህር ኪዳነ ማርያም፣
 ከመምህር ጳውሎስ፣
 ከመምህር አምሳሉ፣
 መምህር ገብረ ማርያም ከሚባሉ መምህራን ጸዋትወ ዜማን መዝገብ ቅዳሴን፣ ግዕዝ ሰዋሰውን በሚገባ ተምረዋል ፡፡
ክህነትን በተመለከተ
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ፤ ዲቁናን ከአቡነ ማርቆስ፣ ምንኩስናን ባደጉበት በአባ ገሪማ ገዳም ቅስናን ከአቡነ ይስሐቅ ተቀብለው ገዳማዊ አገልግሎታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል ፡፡
ቅዱስነታቸው በ1949 ዓ.ም. ገዳሙን አስፈቅደው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት በነበሩት በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፣ የሐረርጌ ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ፕሬዚዳንት በነበሩት በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በአዳሪነት ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን በመከታተል የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ በቆዩባቸው ዓመታት ይሰጥ የነበረውን ትምህርት በመከታተል ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሽልማትን አግኝተዋል፤ ቅዱስነታቸው በትምህርት ገበታና በምንኩስና ሕይወት እያሉ በወጣትነት የዕድሜ ጊዜ ወደ ምንኩስና ሕይወት መግባት አስተዋይነትን ትዕግሥትንና ጽናትን የሚጠይቅ ዓቢይ ጉዳይ በመሆኑ ንጉሠ ነገሥቱ በነበራቸው የጉብኝት ልምድ መሠረት ተማሪዎቹን ለመጎብኘት በመጡ ቁጥር ቅዱነታቸውን ያነጋግሩአቸውና ያበረታቷቸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ፡፡
የውጭ ሀገር ትምህርትን በተመለከተ
– ቅዱስነታቸው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት እንዳጠናቀቁ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያና በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዘሐረርጌ ፈቃድ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ይጠቅማሉ በሚል እምነት የትምሀርት ዕውቀታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሻሽሉ ወደ ውጭ ሀገር ወደ አሜሪካ ተላኩ፤
– በአጠቃላይ በአሜሪካ ሀገር በትምህርት በቆዩባቸው ዓመታት በተለያዩ ዕውቅና ባላቸው ዩኒቨርስቲዎች፤
– በቅዱስ ቪላዲሚር ራሽያ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት ዲፕሎማ፤
– ከየል ዩኒቨርስቲ በርክሌይ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ባችለር ኦፍ ድቪኒቲ ዲግሪ፣
– ከፕርስተን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት ማስተር ኦፍ ቲዮሎጂ፣
– ከፕርስተን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት በዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን ከፍተኛ የመጨረሻ ዶክትሬት ዶክተር ኦፍ ፊሎሶፊን አግኝተዋል፤
የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በተመለከተ
በአገራችን የሚነገሩት ቋንቋዎች ብዙዎች ቢሆኑም ቅዱነታቸው፤
– ግዕዝ፣
– ትግርኛ፣
– አማርኛ በሚገባ ያውቃሉ ፡፡
የውጭ ሀገር ቋንቋዎችን በተመለከተ
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርስቲዎች የገበዩዋቸውን ከፍተኛ ትምህርቶች ለመከታተል በቅድሚያ የተወሰኑ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋዎችን ማጥናትና ማወቅ ስለነበረባቸው በመናገር፣ በማንበብና በመጻፍ የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች፤
– እንግሊዝኛ፣
– ጀርመንኛ፣
– ፈረንሳይኛ ሲሆኑ ለምርምርም ያህል፣
– ዕብራይስጥ፣
– ግሪክኛና
– ላቲን በመጠኑ ያውቁ ነበር፣
የሀገር ውስጥ አገልግሎትን በተመለከተ
ሀ. ቅዱስነታቸው ከሕፃንነት ዕድሜ ጀምሮ ሥርዓተ ምንኩስናን በተቀበሉበት በመደራ አባ ገሪማ ገዳም፣
– ሽማግሌዎች አባቶችን በመታዘዝ፣
– ቤት በማጽዳት፣
– ውሀ በመቅዳት፣
– እንጨት በመስበር፣
– በገዳሙ ቤተ ማኅበር ውስጥ እንጀራ በመጋገር፣ በአጠቃላይ ከገዳሙ አርድእት አንዱን በመሆን በተጠሩበት ሁሉ ፍጹም ታዛዥነታቸውን በማሳየት ከዐሥራ አምስት ዓመታት ያላነሰ በዲቀናም፣ በምንኩስናም፣ በቅስናም አገልግለዋል፡፡
– በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ በትምህርት ገበታ ላይ በነበሩበት ጊዜም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መደበኛ ቀዳሽ በመሆን ባለማቋረጥ ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል ፡፡
– ቀጥሎም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በታሪክና በድርሰት፣ በስብከተ ወንጌል በጋዜጣ ዝግጅትና በሬድዮ ክፍል የበላይ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል ፡፡
– ቀጥሎም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የስደተኞች ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊና የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል ፡፡
ለ. የውጭ ሀገር አገልግሎትን በተመለከተ
ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ወኪል ሆነው እንዲያገለግሉ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ በታዘዙት መሠረት የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል፤
1. በአኀት አብያተ ክርስቲያናት ቀዋሚ ኮሚቴ፣
2. በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ባይብል ሶሳይቲ፣
3. በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የከተማና የእንዱስትሪ ተልእኮ፣
4. በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር እምነትና ሥርዓት /ፌዝ ኤንድ ኦርደር/ ኮሚሽን፣
5. በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የመካከለኛ ኮሚቴ /ሴንትራል ኮሚቴ/ አባል በመሆን ተመርጠው አገልግለዋል፣
6. በኦፕሳላ ስዊድን፣
7. በናይሮቢ ኬንያ፣
8. በቫንኮቨር ካናዳ በተሰበሰቡት ዓበይት ጉባኤያት፣
9. በጄኔቫ ስዊዘርላንድ፣
10. በክሬት ግሪክ፣
11. በአክራ ጋና፣
በተሰበሰቡት የመካከለኛ ኮሚቴ /ሴንትራል ኮሚቴ/ ስብሰባዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመልእክተኛነት ደረጃ አገልግለዋል፡፡
የቅዱስነታቸው የኤጲስ ቆጶስነት በዐለ ሢመት
ለውጭ ሀገር አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት የማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎት አንድ ኤጲስ ቆጶስ መርጦ መሾም አስፈላጊ በመሆኑ በግብረ ገብነታቸውና በትምህርታቸው ከታወቁት መነኰሳት መካከል አባ ገብረ መድኅን ገብረ ዮሐንስ ለዚሁ ለታሰበው የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት ብቁ ሆነው በመገኘታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ መራጭነት እንዲሾሙ ተወስኗል ፡፡
በዚሁ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከሌሎች ሁለት አበው መነኰሳት ጋር መስከረም 16 ቀን 1968 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ እድና በብፁዓን ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት ተራዳኢነት የኤጲስ ቆጶስነቱ በዐለ ሢመት በታላቅ መንፈሳዊ ስነ ሥርዓት ተከብሮ ስማቸውም ብፁዕ አባ ጳውሎስ ተብሎ ተሰየመ፡፡
ሐዋርያዊ ተግባር
ሀ/ የመከራ ዘመን በሀገር ውስጥ፤
ቅዱስነታቸው በደርግ መንግሥት ወደ ዕሥር ቤት መግባታቸው ይታወቃል፤ ሁኖም በመታሠራቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን አላቋረጡም፤ ወንጌልን ከመስበክና ቅዱስ ቃሉን ከመናገር አንዲት ጊዜም እንኳ አልቦዘኑም ነበር፤ ይልቁንም ከ500 በላይ የሚሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን በልዩ ዘዴ ተጻጽፈው ወደ ዕሥር ቤት በማስገባት ለዕሥረኞቹ አድለዋል ፡፡ የራሳቸውን ችግርና መከራ ሳያስቡ በዕሥር ቤት ያሉ ወገኖቻቸው እንዲጽናኑና መከራውን እንዲታገሡ ሲያስተምሩና ሐዋርያዊ ተልእኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተው ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ በደል ሳይፈጽሙ መታሰራቸውን የሚገልፅ ማስረጃ ተሰጥቷቸው በነፃ ተለቀዋል ፡፡
ለ. በውጭ ሀገር
በወታደራዊው ዘመነ መንግሥት ተከስቶ በነበረው የአስተዳደር ችግር ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን በመላ ዓለም ተበትነው ነበር፡፡ ከነዚህም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ጥገኝነትን ለመሻት ወደ አሜሪካን ሔደዋል፡፡ በደረሱበትም ሀገር የራሳችን የሚሉት ሀገር፣ የራሳችን የሚሉት ቤተ ክርስቲያን ባለማግኘታቸው ችግሩ ከባድ ነበር ፡፡ ይሁንና ኑሮው በግድ መቀጠል ስለነበረበት ልጅ መውለድ፣ ክርስትና ማስነሣት ብሎም መታመምና መሞት የመሳሰሉት የኑሮ ጠባዮች አላቋረጡም ነበር ፡፡ ለእነዚህና ለመሳሰሉትም የኑሮ ጠባዮች መንፈሳዊ አገልግሎትን ማግኘት ከምን ጊዜውም በበለጠ በባዕድ ሀገር አስፈላጊነቱ እጅግ የላቀ ነበር ፡፡ ከዚህ አንፃር ቅዱስነታቸው ወገኖቻቸው ተሰደው ወደሚገኙበት ሀገር ከሔዱ በኋላ ጊዜ ሳይወስዱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምእመናንን በማሰባሰብና በማጽናናት ትምህርተ ወንጌልን በበለጠ በማስፋፋት ሐዋርያዊውን አገልግሎት አጠናክረው ቀጠሉ፤ በዚሁ መሠረት ፤
1. የመድኃኒ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በኒውዮርክ፤
2. የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዳላስ ቴክሳስ
3. የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ፤
4. የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ፤
5. የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በፊኒክስ አሪዞና፤
6. የቅድስትሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በታምፓ ፍሎሪዳ፤
7. የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በላስ ቬጋስ ነባዳ በስነ ሥርዓት አቋቁመው እስከ አሁን ድረስ ምእመናን ምእመናት እየተገለገሉባቸው ይገኙሉ ፡፡
ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮ በበለጠ ለማጠናከርና አምልኮተ እግዚአብሔርን ለማጽናት ሃይማኖታዊ ባህልን ጭምር ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
1. የመድኃኔ ዓለም፤
2. የቅድስት ማርያም፤
3. የኪዳነ ምሕረት፤
4. የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
5. የቅዱስ ሚካኤልና
6. የቅዱስ ገብርኤል መንፈሳውያን ማኅበራትን አቋቁመዋል ፡፡.
ከዚህ በላይ የተገለፀው ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በዲቁና በምንኩስና፣ በቅስና በሊቀ ጳጳስነት ሕይወት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቆይታቸው ከፈጸሟቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መካከል ጥቂቱን ክፍል ብቻ የሚያመለክት ሲሆን ቀጣዩ የታሪክ ይዘት ወደ ፓትርያርክነቱ ሥልጣን የመጡበትንና ከትልቁ ሥልጣን ባሻገር ያከናወኗቸውን ተግባራት ከዚህ እንደሚከተለው እንመለከታለን ፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ምርጫን በተመለከተ
አምስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር ለማግኘት አፈጻጸሙ የጠየቀው መሥዋዕትነት ከባድ እንደነበር ቢታወቅም ፈተናውንና መሰናክሉን ሁሉ በማለፍ በብሔር አቀፍና በዓለም አቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤ የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የሚጣልባቸውንና ለተልእኮ የሚፋጠኑትን ለመምረጥ ሰፊ ጥረት ተደረገ፤ በተደረገውም ጥረት መሠረት ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ሊቀ ጳጳስ ሁሉንም አሟልተው የተገኙ በመሆናቸው ሰኔ 28 ቀን 1984 ዓ.ም. አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር እንዲመሩ ተመርጠዋል ፡፡
መራጮቹም፤
– የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣
– የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣
– የየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ካህናት፣
– የካህናት ተወካዮች፣
– የምእመናን ተወካዮች፣
– የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፣
– ቀደምት የአንድነት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና አበምኔቶች ናቸው ፡፡
የቅዱስነታቸውን የተለያዩ ተግባራት በተመለከተ፤
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ፤ ፓትርያርክ ከሆኑበት ጊዜ አንሥቶ ወንጌልን በጥልቀት ለማሰራጨት የቤተ ክርስቲንን አስተዳደር ለማጠናከርና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማስፋት ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡
በእግዚአብሔር ቸርነትና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ፈቃድ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኰሌጅ፣ የፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኰሌጅ እንዲከፈቱ አድርገዋል፤ በደርግ መንግሥት ተወርሰው የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎችንና ንብረቶችን እንደገና ለማስመለስ ችለዋል ፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ብዙ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን መርቀው ከፍተዋል፤ የቤተ ክርስቲያኗን የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆ ከማስፋት አኳያም በመላው ዓለም ተዘዋውረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከትን በመጎብኘት መመሪያን ሰጥተዋል ፡፡

ቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኦርየንታል ኦርቶዶክስ፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ እንዲሁም ከሌሎች የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠነክር ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል ፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔን ለመሻት የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች ከኤርትራ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ለሰላም ውይይት፤
– በኦስሎ -ኖርዌይ፣
– በጀርመን – ፍራንክፈርት፣
– በአሜሪካ – ኒውዮርክ፣
– በናይሮቢ – ኬንያ በተደረጉ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን የሃይማኖት መሪዎቸ ስብሰባ መርተዋል ፡፡
በኒውዮርክ በተባበሩ መንግሥታት በተካሔደው የሃይማኖትና የመንፈሳዊ መሪዎች ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳትፈዋል ፡፡ በዋሽንግተን አሜሪካ በኋይት ሐውስ በተካሔደው የዓለም የኤድስ ቀን ስብሰባ ተገኝተዋል ፡፡
ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔርን ቃል በማሰራጨት ኤድስን ለመቋቋም ያላሰለሰ ጥረትን ማድረጋቸው ተገልፃል ፡፡
የሰላምንና የስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የናንሰን ሜዳይ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኰሚሽን ተሸልመዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በአሜሪካ – ኒውዮርክ በተደረገው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ተገኝተው በግሎባላይዜሽን ላይ ታሪከዊ የሆነና ትኩረትን የሚስብ ንግግር አድርገዋል ፡፡ በተለይም የግሎባላይዜሽንን ጠቀሜታና ጎጂ ጎኖችን በመተንተን በኢኮኖሚ እድገትና በመገናኛ ዘዴዎች ዓለምን ማቀራረቡን አድንቀው፤ በግሎባላይዜሽን የተከሰቱት ችግሮች ስደተኛነት፣ ሥራ አጥነት፣ የሃይማኖት አክራሪነትና የመሳሰሉት መወገድ እንደሚገባቸው ጠቁመው መፍትሔውም ከግሎባላይዜሽን እንደሚገኝ አሳስበዋል ፡፡ ይኸውም ግሎባላይዜሽን ሰብአዊነትን መላበስ እንዳለበትና እንደሚያስፈልገው ሰፋ ባለ ትንተና አስረድተዋል ፡፡
የቅዱስነታቸው የሃያ ዓመታቱ ዘመነ ክህነት ሐዋርያዊና ማኅበራዊ ጉዞን በተመለከተ ተጠቃሎ በየጊዜው እየተመዘገበ መሰራጨቱ ቢታወቅም፤ ሌላውን ሁሉ ለታሪክ ዘጋቢዎች ትተን በዚህ የሃያ ዓመታት ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት ከተከናወነው የተግባር እንቅስቃሴ ጠቅለል ባለ መልኩ ለመግለፅ እንሞክራለን ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ዘመነ ክህነት የሀገርና የዓለም አቀፍ ይዘቷን እያጠናከረችና እያሰፋች የመጣችበት ወቅት በመሆኑ፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ስላለባት ቅዱስነታቸው ዘወትር በቢሮ ከሚያከናውነው የሥራ ፕሮግራም ባሻገር፣ ከውጭው ክፍለ ዓለም ጋር በመገናኘት ስለሀገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን፤ ስለዓለም ሰላም፣ ስለሰው ልጅ ደኅንነት፣ ዓለሙ በሚያውቀውና በሚገባው ቋንቋ በማስተማር ከአኅትና ከሌሎቹም ቀረቤታ ካላቸው፤ ከሌላቸው አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎችም የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል ፡፡ በሀገር ውስጥም ወደየአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በየገዳማቱና አድባራቱ እንዲሁም በገጠር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ከቤተ መቅደሱ ክህነታዊ አገልግሎት ጀምሮ በሚሰጡት ቀኖናዊ መመሪያ፤ አባታዊ ቡራኬ፣ ቃለ ምዕዳንና ትምህርተ ወንጌል፤ ካህናት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸው፤ ምእመናንም በእምነታቸውና በአንድነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
ይህም የዐሠራር ሒደት ቤተ ክርስቲያንን ከካህናት፤ ካህናትን ከሕዝበ ክርስቲያን፣ ሥራን ከሠራተኛ ለማገናኘት ታላቅ አርአያነትና ምሳሌነት ያለው አመራር በመሆኑ ትምህርት ሰጭነቱ የላቀ ነበር ፡፡
ከዚህም ጋር፤
– ሃይማኖተ ምግባር እንዲጸና ሀገር እንዲለማ ማድረጉ፤
– ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፤
– ወጣቶች ከአበው የተቀበሉትን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖቱንና ሥርዓቱን ጠብቀው በትምህርትና በስነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ፤
– የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከሩና ማስፋፋቱ፤
– የሰው ዘር ሁሉ ከረሀብ፣ ከእርዛት፣ ከበሽታና ከድንቁርና ተላቆ በሰላም፣ በአንድነት በመተሳሰብና በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማድረጉ፤
– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሩን ማመቻቸቱ፤
– የሰበካ ጉባኤን የሥራ ሒደት መከታተሉ ማስፋፋቱ፣ ማጠናከሩ፤
– የቤተ ክርስቲያኒቱን የዓለም አቀፉን ግንኙነት ማጠናከሩ፤
– በተለያየ ምክንያት ከየሀገራቸው የወጡትን፣ የተሰደዱትን በያሉበት መርዳቱና ማጽናናቱ፤
– ጧሪ፣ ቀባሪ የሌላቸው በዕድሜ የበለጸጉ አዛውንት እንዲጦሩ ጥረት መደረጉ፤
– የተቸገረ እንዲረዳ፣ ሰብሳቢ ያጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት፣ በአንድነት ተሰባስበው እየተረዱ፤ እየተማሩ እንዲያድጉ ማድረጉ፤
– የፈረሰ፣ የተጎሳቆለ፣ የተጎዳ ቤተ ክርስቲያን እንዲታደስ፣ እንዲጠገን፣ አዳዲስም እንዲሠራ ማድረጉ የቅዱስነታቸው የዘወትር ተግባር ነበር፤
– ከልደተ ክርስቶስ በፊት በአኵስም ጽዮን አደባባይ የተተከሉ ታሪካውያን ሐውልቶች መካከል ተወስዶ የነበረው አንዱ በመንግሥታችን ጥረት እንዲመለስ መደረጉ፤
– በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ዘመነ ክህነት በልዩ ስነ ጥበብ፣ ኪነ ጥበብ በአኵስም ጽዮን አሁን በመሠራት ላይ ያለው ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር አዲስ የታሪክ ገጽታ ያለው ሁኖ የሚታይ ነው ፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ፣ ታሪካዊ ገጽታና ዕይታ ያላቸው ሁነው በሌላም በኩል በመንበረ ፓትርያርክ ቅፅረ ግቢ ታንፆ ሕንፃው ተጠናቆ ለዕይታ ከበቃው ከጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ወቤተ መዘክር ጀምሮ በታሪካዊነታቸው፣ በስነ ጥበብና ኪነ ጥበብ አሠራራቸው በይዘታቸው፣ በውበታቸው አቻ የሌላቸው ተሠርተው ለአገልግሎት መብቃታቸው፤
– የሀገር ቅርስ እንዲጠበቅ፤ ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ያልነበራት ታሪካዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መሥራቱ፤ ማሠራቱ፤
– ትምህርት ቤቶች እንዲሠሩ፤ እንዲሰፉ፤ እንዲስፋፉ ማድረጉ፤
– ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ከየዓይነታቸው በብዛት እየታተሙ፤ እንዲሰራጩ መደረጉ፤ ማድረጉ፤
– ሐዋርያዊ ተልዕኮ እንዲፋጠን ማድረጉ፤
– ‹‹ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር›› ‹እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው› እንደተባለው የወጣቱ ትውልድ ሕይወት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲታነፅ ጥረትን ማድረጉ፤
– በኤች አይ ቪ ኤድስ ደዌ የተያዙት፣ የታመሙት፣ በአልጋ ቁራኛ፣ በደዌ ዳኛ የሚሰቃዩት ድኅነትን እንዲያገኙ፤ እንዲረዱ ማድረጉ፤
– ሰላም በሀገራችን፣ በአካባቢያችንና በዓለሙ ሁሉ እንዲሰፍን ቅዱስነታቸው ዘወትር የሚያደርገው ድካምና ጥረት ነበር ፡፡
ይህ ሁሉ አሠራር ከሀገር፣ ከአህጉርና ከወገን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን አግኝቶ ከላይ እንደተገለፀው፤
– ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የናንሰን ሜዳይ ተሸልመዋል፤

– ቅዱስነታቸው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሁነው እንዲሠሩ በአንድ ድምፅ በዓለሙ ኅብረተሰብእ ተመርጠዋል፤

ከዚህም አንፃር፤
– ከፖርቹጋልና ከእስፔን ሕዝብና መንግሥት ከፍተኛውን ኒሻን ተሸልመዋል፤
– እንዲሁም ቅዱስነታቸው በኢየሩሳሌም ቅዱስ ዮሐንስ የማልታ ክርስቲያናዊ ንቅናቄ ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ታላቁን ባለክንፍ መስቀል ኒሻን ተሸልመዋል፤ ይህ ዓይነቱ አሠራር እስከዛሬ በሀገራችን ታሪክ ጎልቶና ደምቆ ያልታየ በዘመናችን፣ በሀገራችን በፈቃደ እግዚአብሔር የሆነ ታላቅ ሀብት ነው ፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው፤
– በእግዚአብሔር ቸርነት፤
– በቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኝነት፤
– በመንግሥት ተባባሪነትና ድጋፍ ሰጭነት
– በካህናቱ፣ በዲያቆናቱ፣ በመዘምራኑ፣ አገልግሎት ሰጭነት፤
– በሕዝበ ክርስቲያኑ ኅብረትና አንድነት በመሆኑ የአመራሩ ሒደት የቅዱስነታቸውን የማስተባበር ሥራ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ በስማቸው ለመታሰቢያነት የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የቲቢና የካንሰር የማገገሚያና የሕክምና ማዕከል እንዲገነባ በፍጻሜ የሕይወት ዘመናቸው ከፍተኛውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውም ይህን የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከግቡ እንዲያደርሱ አደራ በማለት ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል ፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት ከመንግሥት ጎን በመሆን ይህኑ አደራ ተፈጻሚ በማድረግ ታሪክ እንድንሠራ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን ፡፡
– ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
– ክቡራን ክቡራት የኀዘናችን ተካፋዮች በሙሉ፤

ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት በሃያ ዓመታቱ የሥራ ጉዞ ካከናወኗቸው መካከል ለግንዛቤ ያህል ዋና ዋናውን ያቀረብን ቢሆንም የታሪካቸው መግለጫ የሆነው ተግባር ሁሉ ሕያው ሆኖ ሲያስታውሳቸው ይኖራል ፡፡
ይሁንና ‹‹መኑ ስብእ ዘየሐዩ ወኢይሬእያ ለሞት›› ‹ሕያው ሁኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው?› /መዝ. 88፡48/ ተብሎ በነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በተነገረው መሠረት ቅዱስ ፓትርያርካችን በጾመ ፍልሰታ ለማርያም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመቀደስና ሐዋርያዊውን ተልዕኮ በመፈጸም አንደኛውን ሱባኤ ካጠናቀቁ በኋላ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም. በዐሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሔደው በመታከም ላይ እንዳሉ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል ፡፡
የቅዱስነታቸው ዕረፍት እንደተሰማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቀብራቸው ስነ ሥርዓት አፈጻጸም ሒደት ተወያይቶ መርሐ ግብር አውጥቷል፡፡
ይህኑ መርሐ ግብር በተግባር የሚተረጉሙ ዓቢይ ኮሚቴና ንዑሳን ኮሚቴዎችን አቋቁሟል ፡፡ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ባወጡት መርሐ ግብር መሠረት የቅዱስነታቸው አስከሬን ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በመላ ሕዝበ ክርስቲያን ታጅቦ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ከተደረገ በኋላ በዚሁ ካቴድራል ሥርዓተ ጸሎቱ ሲፈጸም አድሮና አርፍዶ፤
– ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
– የመንግሥት ባለሥልጣናት፤
– የሃይማኖት መሪዎች፤
– ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች፤
– ከውጭ ሀገር የመጡ እንግዶች፤
– የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች፤
– የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተጠሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤
– የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤
– ዘመድ ወዳጆቻቸው በተገኙበት ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት የቀብሩ ስነ ሥርዓት ከላይ በተጠቀሰው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የቅዱስነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳኑ ጋር ይደምርልን!

ለቤተ ሰባቸው፣ ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያውያት ጽናቱን ይስጥልን!

ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት