ግንቦት ፲፮ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ዓ.ም አስከ ግንቦት ፲፭ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ድርስ በ ፲፰ አጀንዳዎች ዙሪያ የርክበ ካህናት ጉባኤውን ሲያካሒድ ከቆየ በኋላ ዛሬ ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ዓ.ም ፲ ነጦቦችን የያዘ መግለጫ በማውጣት ጉባኤውን አጠናቋል።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመክፈቻ ንግግር ጉባኤውን በይፋ የጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በተያዙት አጀንዳዎች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ውይይት በማድረግ ልዩልዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል ።የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 1 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡ ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት እና መንፈሳዊ ዕድገት ትኩረት በመስጠት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ጉልላት እንደመሆኗ ሰላም መሠረታዊ ተልእኮዋ ነው፡፡ ስለዚህ ወቅታዊውን ችግር ታሳቢ በማድረግ በመላው አገራችን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ተቋማት ጋራ የሚሠራ፣ በሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚኖረው የሰላም ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡
በትግራይ ክልል በሚገኙት አህጉረ ስብከት ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ልዑክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ተልዕኮውን እንዲፈጽም ምልዓተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ ወገኖቻችን ያሉበትን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ በማድረግ አስቸኳይ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በወቅታዊ ችግር ምክንያት በመላው ሀገራችን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ በአጠቃላይ ችግሮቹን በጥናት በመለየት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ልጆቿን በማስተባበር ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ የማጽናናትና የመጎብኘት መርሐ-ግብሮች እንዲደረጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
መቀሌ የሚገኘው የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሠራተኞችን ደመወዝና የሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲለቀቅና በ2016 በጀት ዓመት ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የሆነ የመማር ማስተማሩ የሥራ ሂደት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጪው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግብ መሪ ዕቅድ በማጽደቅ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅሮች ተግባራዊ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን ቀደምት አበው በቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም ገዳማት እንዲስፋፉ ሁሉ የነሱን አሰረ ፍኖት በመከተል በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ካልፎርኒያ ግዛት የተቋቋመው ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም እንዲጠናከር፤ በተጨማሪም በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የአስተዳደር፣ የጽሙና፣ የትምህርትና የምርምር ማዕከል እንዲመሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ አስተላልፏል፡፡
በኦሮምያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአህጉረ ስብከትና በአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት ስለተቋረጠ፣ በርካታ ምእመናንና ካህናት በእስርና እንግልት ላይ ስለሚገኙ በዚሁ መነሻነት ችግሮች እንዲቀረፉና ወደ መደበኛው የአሠራር መዋቅር እንዲመለስ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን በመሠየም ከፌዴራልና ከኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የመንፈሳዊ ኮሌጆች መከፈት እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር በተመለከተ በኢሉ አባቦራ የመቱ ፈለገ ሕይወት የነገረ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲከፈት የተፈቀደ ሲሆን በሌሎች አህጉረ ስብከት ሊከፈቱ የታሰቡ ኮሌጆችን እና የአብነት ት/ቤቶችን መሠረታዊ ጥናት ተደርጎ ለ2016 ዓ.ም. የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ ክፍት በሆኑና በተደራቢነት በተያዙ፣ ጉልህና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው በኦሮምያ ክልልና በደቡብ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከት ላይ 9 ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡ ወደፊትም ተደርበው በተያዙና አስፈላጊ በሆኑ አህጉረ ስብከት እንደአስፈላጊነቱ በመንበረ ፓትርያርክ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩትን አላስፈላጊ ግጭቶች የዜጐች መፈናቀል፣ ስደት ተወግዶ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ በእኩልነት፣ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ በአንድነት እንዲኖር፤ ለማድረግ ግጭቶችና አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡ እንዲሁም በመላው ዓለም ጦርነት ባለባቸው ሀገራት ሁሉ ሰላም እና ዕርቅ እንዲሰፍን በመመኘት እና በመጸለይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ