ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””
፩ኛ የጉባኤው ርዕሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የቤተክርስቲያን ችግሮችና መፍትሔዎችን በሚገባ የገለጸ መልዕክት ማስተላለፋቸውና ጉባኤውን ፍጹም በተረጋጋ መልኩ የመሩበት መሆኑ፤
፪ኛ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጉባኤው በተረጋጋ መልኩ እንዲካሔድ ከአድሎአዊነት በጸዳ መልኩ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ የአመራር ጥበብ ግልጽነት በተሞላበት መንፈስ በመምራት የአመራር ጥበብና ችሎታቸውን
ባረጋገጠ መልኩ በመምራት በታሪክ የሚመዘገብ የመሪነት ሚናቸውን ማሳየታቸው፤
፫ኛ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በትዕግሥትና በምልዓት በጉባኤው ላይ በመሳተፍና ገንቢ ዐሳቦችን በመስጠት በሚገባ የተሳተፉበት ጉባኤ መሆኑ፤
፬ኛ መላው የጉባኤ አባላት በምልዐት፣ያለመሰላቸት፣በመረጋጋትና በትዕግሥት መልዕክቶችን በማዳመጥ ፍጹም መንፈሳዊነት በተሞለበት ሁኔታ የተሳተፉበት ጉባኤ መሆኑ፤
፭ኛ በጉባኤው ላይ የቀረቡ አብዛኛው ሪፖሮቶች ያልተጋነኑ፣በሐቅ ላይ የተመሠረቱ፣ችግሮችና መፍትሔዎች የተጠቆሙባቸው፣ከቅድስት ቤተክርስቲያን የወጡና ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን የመጡ ምእመናን ቁጥር በንጽጽር የተገለጸበት፣የወደፊት አቅጣጫዎች የተጠቆሙበት ሪፖርት የተሰማበት መሆኑ፤
፮ኛ በምልዓት በተደረገው ውይይት ከመሞጋገስና ችግሮችን ከመሸፋፈን ይልቅ ችግሮች በግልጽ የተጠቆሙበት፣ለተገለጹ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው የሚታመንባቸው የመፍትሔ ዐሳቦች የተጠቆሙበት ግልጽና ነጻ ውይይት መደረጉ፤
፯ኛ በቡድን ውይይት ወቅት ለመወያያነጥቦች ተብለው የተለዩ የውይይት ርእሶችን መሠረት ያደረገ ግልጽና ነጻ ውይይቶችን ሳታፊዎች ማድረግ መቻላቸውና ከጉባኤው ተሳታፊዎች በውይይት የተገኙ የመፍትሔ ዐሳቦችና አቅጣጫዎችን በግልጽነት መቀመጣቸው፤
፰ኛ የመወያያ ርእሶችን እንዲያዘጋጁ የተመረጡት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አሁናዊ የቤተክርስቲያን ሁኔታን በአግባቡ የሚፈትሹ የመወያያ ርእሶችን በመለየት ቤተክርስቲያን ከፈተና የምትወጣበትን አቅጣጫ የሚያሳዩ ነጥቦችን ማቅረብ መቻላቸው፤
፱ኛ የቡድን ውይይቶቹን እንዲመሩ የተመደቡት የቡድን አወያዮች በቀረበው የመወያያ ርእስ ዙሪያ የቡድን ተወያዮቹ ግልጽነት የተሞላበት ነጻ ውይይት እንዲያደርጉ ማድረጋቸውና በየ ቡድኑ የተነሡ ዐሳቦችን በሚገባ ቀምረው ለምልዓተ ጉባኤው ማቅረባቸው፤
፲ኛ በቡድን ውይይቶቹ የተነሡ ነጻና ግልጽ ዐሳቦችን በጥልቀት በመዘርዘር ተገቢ፣ወቅታዊ፣ግልጽና ተቋማዊ ማጠቃለያን በመስጠት የጉባኤተኛውን ሙሉ ድጋፍ ያገኘና ቀጣይ የሥራ መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ማጠቃለያ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መስጠታቸው፤
፲፩ኛ የጉባኤውን ቆይታ፣የተነሱ፣ዐሳቦችን፣የተቀመጡ የመፍትሔ ዐሳቦችን፣ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚገባ በመዘገብ ግልጽና ውጤታማ የዐቋም መግለጫ መቅረቡ በመጨረሻም በተቀመጠው የሽልማት መስፈርት መሰረት ሽልማት ለሚገባቸው ሽልማት መሰጠቱ፤
፲፪ኛ ለተሸላሚዎች የተሰጠው ሽልማት ቤተክርስቲያንን ማዕከል ያደረገ የሁል ጊዜ ማስታወሻ እንዲሆን መደረጉ ወዘተ …. በ፵፪ኛው ዓለም አቀፍ አጠቃላይ ጉባኤ ከተመዘገቡ በርካታ ስኬቶች ጥቂቶቹ ሆነው በታሪክ ተመዝግቧል።