(ግንቦት ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም )
++++++++++++++++++
የ2015 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት የሁለተኛው ቀን ውሎን አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒውዮርክና አካባባቢዋ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ማብራሪያ ሰጡ።
ለኢኦተቤ ቴቪ (EOTC TV) ዕለታዊ ማብራሪያ የሰጡት ብፁዕነታቸው በሁለተኛው ቀን በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮች መወያያየቱን ገልጸዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በቀዳሚነት በሀገር ሰላም ዙሪያ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ጉባኤው ብዙ ሲወያይ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ማድረግ ትችላለች : ምእመናንም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ይሰማሉ የሚለው ሐሳብ አሸንፎ ; በዚህ ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው የሚሰሩ ሦስት ብፁዓን አባቶች ተመርጠው የሀገር ሰላምን በተመለከተ ረዥም ርቀት በመሔድና ከሚመለከተው አካል ጋር ሁሉ በመነጋገር በሀገር ሰላም ዙሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና አሁን ካለንበት መከራ የምንወጣበትን መፍትሔ እንዲያመጡ ተመርጠዋል።
በቀጣይነት በወቅታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ችግር አስመልክቶ በትግራይና በኦሮሚያ አህጉረ ስብከት የነበሩትን ችግሮች መነሻ በማድረግ
ሀ) በክልል ትግራይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የትግራይ አባቶችና አባላቱን በአካል ለማነጋገር በቋሚ ሲኖዶስ የተመረጠውን ኮሚቴ ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥል ወስኗል።
+ በተጨማሪም ተቋርጦ የነበረው በጀት እንዲለቀቅ
+ የማጽናኛ መርሐ ግብር እንዲካሄድና በተቻለ መጠን አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ በጉባኤው ተወስኗል።
ለ) በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም የተከሰተውን የቤተ ክርስቲያን ፈተና በተመለከተ
ሰፊ ውይይት ከተደረገ እና ወደ መግባቢያ ሐሳቦች መደረሱን ገልጸው
በስድስት አኅጉረ ስብከቶች ምንም ዓይነት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ
የማያዳግም የመፍትሔ ለመስጠት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ከሦስቱ ብፁዓን አባቶች ጋር አራት ብፁዓን አባቶችን ተጨማሪ በማድረግ
በቀጥታ የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ መቀረፉንና ከአንድ ሲኖዶስ ውጪ ሌላ አለመኖሩን ለመንግሥት አካላት በጋራ ሔደው የተደረሰበትን ስምምነት ተገቢውን መረጃ እንዲሰጡ
ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስን
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤልን
ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን
ብፁፅ አቡነ ሳዊሮስን
ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስን
እና ብፁዕ አቡነ ኤውስጣቴዎስን
በመመደብ እነዚህ ሰባት ብፁዓን አባቶች በአንድ ላይ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ፍጹም በሆነ የመግባባት ስምምነት መፈጠሩን ገልጸው
ከእንግዲህ በኋላ የተከፋፈለ ሲኖዶስ እንደሌለ እና ከዚህ ሐሳብ ውጪ የሆነ አካል ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ውጪ የሆነ መሆኑን በአንድነት ለመንግሥት እንዲያሳውቁ መወከላቸውንም ገልጸዋል።
በቀጣይም ያሉንን የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች በዚህ መልኩ በመግባባትና በመተማመን በመፍታት በሀገርና በቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነትን በማያዳግም ሁኔታ የሚያውጅ ቆይታ ይሆን ዘንድ መላው ሕዝበ ክርስቲያን በጸሎት አስቡን በማለት ብፁዕነታቸው አባታዊ መልእክታቸውንና ቡራኬአቸውን በመስጠት
የሁለተኛውን ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሎ አጠር ባለ መልኩ ገልጸውልናል።