ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም
“””””””””””””””””””””””

– ለሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ ለ13 ወረዳ ሊቃነ ካህናትና ሠራተኞች ከ2.1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የስምንት ወር ደመወዝ ተከፍሏቸዋል።

– ለ317 ነዳያን ከ ብር 523,000.00 በላይ ወጪ ተደርጎ ድጋፍ ተደርጓል።

– በሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊና ሕጋዊ አግባብን የተከተለ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።

– በሀገረ ስብከቱ ፣በካህናት፣ በምዕመናን፣ በወጣቶችና በሕዝበ ክርስቲያኑ መካከል መልካም የሚባል ሕግና ሥርዓትን የጠበቀ ግንኙነት በመጠናከሩ ሠፊ መንፈሳዊ አገልግሎት በመሰጠት ላይ ይገኛል።

የጋምቤላ፣ የአሶሳ፣ የቄለም ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በግንቦት ወር ፳፻፲፭ ዓ/ም በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ አህጉረ ስብከት አዳዲስ ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ ጳጳሳቱ ወደየተሾሙባቸው አህጉረ ስብከት በመሔድ አገልግሎት እንዲጀምሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ብፁዕነታቸው አንዱ ሀገረ ስብከታቸው ወደ ሆነው ወደ ቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት መጓዛቸውን በመግለጽ በሀገረ ስብከቱ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት የተከናወኑትን ዋና ዋና ሥራዎች በመግለጽ መረጃውን አድርሰውናል።

በዚህም መሠረት በጥር ወር ፳፻፲፭ ዓ/ም የተከናወነውን ሕገ ወጥ ሢመት ተከትሎ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ላለፉት ስምንት ወራት ደመወዛቸው ሳይከፈላቸው የቀሩ የሀገረ ስብከቱና የወረዳዎቹ ሊቃነ ካህናትና ሰራተኞች መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ በማድረግ ተቋርጦ የቆየውን ደመወዛቸውን ከሁለት ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ እንዲከፈላቸው ተደርጓል ያሉት ብፁዕነታቸው ከሦስት መቶ አሥራ ሰባት በላይ ለሚሆኑ ነዳያንም ከአምስት መቶ ሀያ ሦስት ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሀገረ ስብከቱ በተረጋጋ መልኩ መዋቅራዊ አንድነቱን በማጠናከር ሥራውን እየሠራ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምዕመናንና ከወጣቶች ጋር ባደረግናቸው ተደጋጋሚ ውይይቶች መዋቅራችንን በማስከበር ሥራዎቻችንን በሚገባ ማከናወን የምንችልበት ስልት ቀይሰን በመሥራት ላይ እንገኛለን፤ ሀገረ ስብከታችንም ፍጹም ሰላማዊና ሥራዎች በመግባባት የሚከናወኑበት ተቋም በመሆን ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በማያያዝም በሀገረ ስብከቱ ሥር በምትገኘው በታሪካዊቷና በንጉሥ ጆቴ ቱሉ ዘመን በተተከለችው በታቦር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ማሳለፋቸውን የገለጹት ብፁዕነታቸው ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም በተከበረው የፍልሰታ ለማርያም በዓል ላይ ቤተክርስቲያኑ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ የካቴድራልነት ማዕረግ እንደተሰጠው ገልጸዋል። ከሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፱፲፭ ዓ/ም ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሰነበቱ መሆናተውን የገለጹት ብፁዕነታቸው በሀገር ሽማግሌዎችና በአባ ገዳዎች ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው አስታውሰው እስከ ዘመን መለወጫ ድረስ በሀገረ ስብከቱ የሚሰጡትን አገልግሎት አጠናክረው እንደሚቀጥሉና በሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉና በየደረጃቸው ሲያገለግሉ ለቆዩ በርካታ አገልጋዮች ሥልጣነ ክህነትን እንደሚሰጡም ጨምረው ገልጸዋል።