ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ

፩.ሃይማኖተ ኦሪት

በአንድ እግዚአብሔር ማመን ሃይማኖተ ኦሪት ወይም ሃይማኖተ አይሁድ ይባላል፡፡ኢትዮጵያ ነገደካም፣ ነገደሴም፣ ነገደ እስራኤል(1) የተባሉ ሕዝቦች ከሰፈሩባት ጊዜ ጀምሮ ሃይማኖተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማመን) የታወቀባት ሀገር መሆንዋ ብዙዎች የታሪክ ምንጮች ያስረዳሉ(2) በተለይም ክብረነገሥት ተባለውን ታሪክ መጽሐፍ መሠረት አድርገው የተጻፉ ታሪክ መዛግብት ቀጥተኛ ጊዜውን በመግለፅ በአንድ እግዚአብሔር ማመን በኢትዮጵያ የተጀመረው በአንድሺህ ዐመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ መጀመሪያ በንግሥተ ሳባ እና በልጅዋ በቀዳማዊ ንጉሥ ምኒልክ መሆኑንያስረዳሉ፡፡(3) መጽሐፍ ቅዱስን ግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰለሞንን ለመጐብኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ እንደ ነበረች ያስረዳል፡፡(4) ክብረ ነገሥት የተባለውም የታሪክ መጽሐፍ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አጕልቶ በመግለፅ ንግሥተ ሳባ ከንጉስ ሰለሞን ጸንሳ ወደ ኢትዮጵያ መመለስዋን፣ በኃላም ልጅዋ ምንሊክ ተወልዶ ለአካለ መጠን ሲደርስ ወደኢየሩሳሌም  በመሄድ ከአባቱ ጋር ተገናኝቶ በሚመለስበት ጊዜ በአባቱ መልካም ፍቃድ ከሕዝበ እስራኤል የተወጣጡ የበኩር ልጆች የሰዶቀ ልጅ አዛሪያስን፣ሌዋውያን መምህራን ኦሪትን፣ ካህናትንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ እንደተመለሰና በአክሱም እንደተቀመጠ ዘርዝሮ ያስረዳል፡፡ከዚህጊዜጀምሮየኢትዮጵያህዝብሃይማኖትኦሪትን (ሃይማኖተአይሁድን )አምኖካህናተኦሪት፣ሴማውያን በአክሱም ታቦተ ጽዮንን ያገለግላሉ፣ ሕገ ኦሪትን ያስተምሩ ነበር(5) ይህ ይታወቅ ዘንድ ከ ሕገ ኦሪት ፣ ሥርዐተ አይሁድ፣ ባህለ አይሁድና ልማደ አይሁድ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰርጸው ይገኛሉ፡፡(6) ይህ ሃይማኖተ ኦሪት፣ ሥርዐተ አይሁድና አይሁዳዊ ባህል ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብና ሕዝበ ኢስራኤል የረዥምየታሪክ ትስስር እንዲኖራቸው አድርጎአቸዋል ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት ሃይማኖተ ኦሪትን (ሃይማኖተ አይሁድን ) አምኖ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ጠቅለል ባለ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅድመ ሃይማኖተ ክርስትና በሃይማኖተ ኦሪት (ሃይማኖተ አይሁድ) ለረዥም ዘመናት መኖሩን በሁለት ዐበይት የታሪክ ነጥቦች መረጋገጥ ይቻላል፡፡

  1. ከዚህበላይየተገለጹትሕገኦሪት፣ሥርዐተአይሁድናባህለአይሁድበኢትዮጵያህዝብህልው(አኗኗር) ሰርጸውመገኘታቸውነው፡
  2. ሕጽዋ ለንግስት ሕንደኬ (የንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ) ለአምልኮተ እግዚአብሔር (ለእግዚአብሔር ለመስገድ ) ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና ከብሉይ ኪዳን ክፍል ምጽሐፈ ኢሳይያስን ሲያነብ መገኘቱ ነው ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሕዝቦች ቀድሞ በሃይማኖተ እግዚአብሔር የተመሰረተ ስለነበረ ሃይማኖተ ክርስትናን ለመቀበል ያዳገተው አንድም ነገር አልነበረም፡፡

፪. ሃይማኖተ ክርስትና በኢትዮጵያ

፪.፩. ሕጽዋ ለሕንደኬ

በኢትዮጵያየሃይማነተክርስትናታሪክመነሻውበግብረሐዋሪያትምዕራፍ፰፡፹፮-፵የተመዘገበውመልእከተመንፈስቅዱስናሐዋርያዊተልእኮነው፡፡ይህየመጽሐፍቅዱስክፍልህንደኬየምትባልንግስትበአንደኛውመቶክፍለዘመንበኢትዮጵያነግሳእንደነበረ ‹‹ሕጽዋለህንደኬ›› በሚባል የሚታወቅ አንድ የዕቃ ግምጃ ቤት አዛዥ(ሹም) እንደነበራት ያስረዳል የሀው ሕጽዋ ለንግስት ህንደኬ (ንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ) እግዚያብሔር ሊሰግድ በ፴፬ ዐ/ም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር(7) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከላይ እንደተገለፀው ከ1000 ዐመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ሕገ ኦሪትን ፣ሥርዐተ ኦሪትን ማክበርና እግዚአብሄርን የማምለክ ልምድ ነበረውና ፡፡ሕጽዋ ለንግስት ህንደኬ ለአምልኮተ እግዚያብሔር ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ መልአከ እግዚአብሄር ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የሆነው ፊሊጶስን ‹‹ከኢየሩሳሌምወደጋዘየሚወስድውንመንገድሂድ›› ብሎት ሲሄድ ይህን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘው፡፡ ኢትዮጵያዊ የንግስቲቱ ጃንደረባ ለእግዚያብሔር ሰግዶ ሲመለስ በሰረገላው ተቀምጦ መፅሐፈ ኢሳያስ ያነብ ነበር፡፡በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ጃንደረባው የተቀመጠበትን ሰረገላ ተከተለው ብሎ አዘዘ፡፡ፊሊጶስም ይህን የመንፈስ ቅዱስን ትዕዛዝ ተቀብሎ ሮጠ ሰረገላው ደረሰበት፡፡

ፊሊጶስ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ቍ 7-8 ያለውን ቃለ ትንቢት ሲያነብ ሰምቶ ጃንደረባውን ‹‹የምታነውንታውቃለህን›› ብሎ ጠየቀው ጃንደረባውም ያስተማረው ሰው እንዳለ ነበረና የንባቡን ጥልቅ ምስጢር እንደማያውቅ ገልጾ መለሰለት፡፡ፊሊጶስም እንደማያውቅ  ከገለጸለት መነሻ ሐሳብ ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ አስረዳው፡፡ጃንደረባው ቀድሞውም በሃይማነኖት እግዚአብሔር የሚኖር ነበር፡፡ፊሊጶስ ትምህርት ረክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልዳ እግዚአብሔር እንደሆኑ ወዲያውኑ በፍጹም ልቡ አመነ፤በአፉም መሰከረ፡፡አያይዞም ፊሊጶስ እንዲያጠምቀው ጥያቄ አቀረበ፡፡ ፊሊጶስም ጃንደረባው ለመጠመቅ ሙሉ ፍቃደኛ መሆኑንና በመንፈስ ቅዱስ የተላከበት ዐላማ መሆኑን በመገንዘብ ወዲያውኑ ውሀ ካለበት ወንዝ ወስዶ አጠመቀው፡፡ኢትዮጵያዊው ጃነደረባም የተነገረውን የእግዚአብሔር ቃል

በመረዳቱ፤ ሃይማኖተ ክርስትናን በማመኑና በመጠመቁ ደሰ እያለው ወደአገሩ ተመለሰ8፡፡ይህ በግብረ ሐዋርያት ምዕራፍ ፰፡፳፮የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ነው፡፡

በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የተሌዩ መሠረተውያን ነጥቦች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡ ከነዚህ አንዱ መሠረታዊ ሐሳብ ፈቃደ እግዚአብሔር ነው፡፡ከላይ በተገለፅው የግብረ ሐዋሪያት ክፍል (ግብ.ሐዋ.ም ፰.፹፮) መልአከ እግዚአብሔር ፊሊጶስ ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ወደ ጋዛ እንዲሄድ መንገሩና መንፈስ ክዱስ በዚህ በጋዛ መንገድ ላይ የሚጓዘውን የጃንደረባው ሰረገላ ተከትሎ እንዲሄድ ፊሊጶስን ማዘዙ ክርስትና ሃይማኖትና ጥምቀት ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሐዋሪያት በቀጥታ እንዲተላለፍ የእግዚያብሔር ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ሁለተኛው የዚህ ክፍል መሠረታዊ ሐሳብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትና የልብ ቅንነት ነው፡፡ኢትዮጵያዊው የንግስት ህንደኬ ጃንደረባ ለእግዚያብሕር ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና መጽሐፈ ኢሳያስን ሲያነብ መገኘቱ ከሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት በተጨማሪ ፊሊጶስ ጃንደረባውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምስጢረ ሥጋዌ ባስተማረው ጊዜ እንደ አሕዛብ ወይም እንደ አይሁድ ሳይጠራጠር፣ ሳይከራከር በአንድ ጊዜ በፍጹም ልቡ አምኖ፣ በአፉም መስክሮ መጠመቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌላው ዐለም ቀድሞ በሃይማኖተ እግዚያብሔር የተመሠረተ ቅንና ጽኑዕ ልቡና ያለው ሕዝብ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሃይማኖተ ክርስትናን አምኖና ተጠምቆ ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኃላ ፊሊጶስ ያስተማረውን ትምህርተ ክርስትና ያጠመቀውን ጥምቀት ከቤተ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ አስተምሮአል፡፡(9) ሕጽዋ ለህንደኬ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ ካስተማረበት ከ፴፬ ዓ/ም ጀምሮ ሃይማኖተ ክርስትና እና ጥምቀት በኢትዮጵያ እንደተመሠረተ የማይጠራጠር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቅ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ሊቅ መጽሐፈ ምሥጢር በተባለው ድርሰታቸው ‹‹ጥምቀትን ያመጣልን የንግሥት ህንደኬ መጋቢ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ነው›› በማለት ጃንደረባው አምኖና ተጠምቆ ወደ አገሩ ከመጣ በኃላ ይህን ሃይማኖተ ጥምቀት ማስተማሩን ገልጸዋል(10)፡፡ይህን የአባ ጊዮርጊስ ገለጻ በመከተል የጻፉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ብዙዎች ናቸው፡፡ከነዚህም መካከል አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ የተባሉ ‹‹መርሐ ልቡና›› በተባለ መጽሐፋቸው የሚከተለውን ጽፈዋል፡፡

‹‹ጌታችን ባረገ 3ኛው ዘመን የገርሳሞት ንግሥት (በግብረ ሐዋሪያት ህንደኬ የተባለችው) የእርሷ ባለሟል መኰንን ጃንደረባ ስለጌታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነገር ወደ ኢየሩሳሌም ተልኮ ሄዶ አምኖ ተጠምቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሃይማኖትንና ጥምቀትን አስተማረ፡፡(ግብ ሐዋ 8፡26-39)

ነገር ግን በዚያ ጊዜ የተጻፈ ወንጌል ስላላገኘን በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል እንደተባለ የወንጌል ትምሕርት በቃል ብቻ ሲነገር ነበረ፡፡እያደረ ግን እየጠፋባቸው እምነትንና ጥምቀትን ብቻ ይዘው እስከ 317 ዓ/ም ተቀመጡ፡፡በ317 ዓ/ም አብርሀና አጽብሐ ሁለት ወንድማማቾች በነገሡ በ11ኛ ዐመት በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሃይማኖትና ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሠለጠነ እንጂ አባ ሰላማ ቀድሞ ያልነበረውን ጥምቀት ያመጣ አይመስልም››(11)

በጽሑፍ የገለጸው ይህ ሐሳብ ክርስትና ሃይማኖትና ጥምቀት ከአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በፊት በ1መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ መመሥረቱን ያረጋግጣል፡፡በሌላም በኩል ከተለያየ የዐለም ክፍል የተሰበሰበ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ በበዐለ ሐምሳ ቀን በዐሉን ለማክበር በኢየሩሳሌም በተገኘ ጊዜ ኢትዮጵውያንም በዚያ በዐል ተገኝተው እንደነበሩና በሐዋርያው ጴጥሮስ ስብከት እንዳመኑ ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያም ተመልሰው ሃይማኖተ ክርስትናን እንዳስተማሩ ዮሐንስ አፈወርቅ በስብከቱ መግለፁን ጠቅሰውየጻፉጥቂቶችአይደሉም(12) በተመሳሳይሁኔታሩፊኖስ፣ሶቅራጥስ፣ቴኦዶሪቶስና ሶዞሚኖስ የተባሉ የታሪክ ጸሓፊዎች በአንደኛ መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ማቴዎስ ሐዋርያ ወደኢትዮጵያ መጥቶ ወንጌለ ክርስቶስን ማስተማሩን እንደገለፁ ጠቅሰው የጻፉ ምሁራን አሉ፡፡(13)በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕጽዋ ለህንኬ ትምህርት፣በቅዱስ ጴጥሮስ የበዐለሐምሳው ስብከት በአመኑ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ሃይማኖተ ክርስትናን አምኖ፣ጥምቀተ ክርስትናን ተጠምቆ ይኖር ነበር፡፡ነገር ግን እስከ አራተኛ መቶክፍለ ዘመንድሕረ ልደተ ክርስቶስ ቍርባን፣ክህነት፣ጠቅላላየምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አፈጻጸም አልነበሩትም፡፡ይህይሟላ ዘንድ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት በአጋጣሚ ሳይሆን በጥበበ እግዚአብሔር የሚከተለው ታሪክ ሊፈጸም ችለዋል፡፡

፪.፪.አቡነ ሰላማ ከሳቴብርሃን(ፍሬምናጦስ)

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ሜሮጵዮስ የተባለ ፈላስፋ ፍልስፈናን የሚያስተምራቸው ሁለት ዘመዶቹ ወጣቶችን አስከትሎ ከጢሮስ ወደህንድ ለመሄድ በቀይ ባሕር(ብሕረ-ኤርትራ) በመርከብ ጉዞ ጅምሮ ነበር፡፡

እነዚህ ሁለት ወጣቶች  1.ኤዶስዮስ 2.ፍሬምናጦስ ይባሉ ነበር፡፡ሁሉም በቀይ ባሕር በመርከብ ሲጓዙ በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ የባሕር ወደብ(የባሕር ጠረፍ) በነበረቺው በአዱሊስ አጠገብ ዐርፈው ነበር፡፡ነገር ግን ሜሮጵዮስ የግድያ አደጋ አጋጥሞት እዚው ሞተ፡፡የሜሮጵዮስን ገዳዮች በተመለከተ የተለያዩ የታሪክ አባባሎች አሉ፡፡አንዳንዶቹ የታሪክ ጸሓፊዎች አትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ቅኚ ግዛትን ትቃወም ስለነበረ በዚህ መርከብ ውስጥ የነበሩ ሜሮጵዮስና የመርከቡ ቀዛፊዎች የሮማ ሰላዮች መስለዋቸው የኢትዮጵያ ጠረፍ ጠባቂዎች እንደ ገደሉዋቸው ይገልጻሉ(14)፡፡ሌሎች የታሪክ ጸሓፊዎች ግን ሜሮጵዮስ የገደሉ ሽፍቶች እንደነበሩይተርካሉ(15)ይሁን እንጂ ሁለቱም የታሪክ ምንጮች ሜሮጵዮስን በቀይባሕር ወደብ በአዱሊስ መገደሉን ያረጋግጣሉ፡፡

ሁለቱን ወጣች ግን ኢትዮጵያውያን ሰዎች ከሞት አዳኑአቸው፡፡ወደ አክሱም ወስደውም ለንጉስ አልአሜ አስረከቡአችው፡፡ ንጉሱም በፍቅር ተቀብሎ ኤዶስዮስን የግቢው አዛዥ፣ፍረምናጦስን የጽሕፈት ክፍል ሐላፊና የልጆች አስተማሪ አድርጎ ሾማቸው፡፡ለንጉሠ አክሱም ኢዛና እና ሳይዛና የተባሉ ሁለትሕጻናት ልጆች ነበሩት፡፡ኤዶስዮስና ፍረሚናጦስ ከነዚህ ሁለት ሕጻናት ጋር ሆነው በአክሱም ቤተ ቀጢን በተባለ ቦታ ላይ በነበረው ትምህርት ቤት ግእዝ ቋንቋንና በዚያ ጊዜ የነበረውን የቤተክርስትያን ትምህርት ሁለት ለሰባት ዐመታት ተምረዋል፡፡ በዚህ መካከል ንጉሡ አልአሜዳ ብዙ ሳይቆይ ታምሞ ከዚህ ዐለም ተለየ(ሞተ)፡፡ንግሥቲቱ አሕየዋ(ሶፊያ) ከአልአሜ ሞት በኃላ በልጆቹ በኢዛናና ሳይዛና ስም መንግሰስቱን ታስተዳድር ጀመር፡፡ ታላቁ የንጉሥ ልጅ ኢዛና ለአካለ መጠን ደርሶ ዙፋኑን በወረሠ ጊዜ ፍሬሚናጦስና ኤዶስዮስ ወደ አገራቸው ለመመለስ የስንብት ጥያቄ አቀረቡ፡፡በጥያቄው መሠረትም እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው ኤዶስያስ ወደ አገሩ ሄደ፡፡ ፍሬሚናቶስ ግን በአክሱም ሃይማኖተ ክርስትና፣ጥምቀት እንጂ፡፡ቍርባን፣ካህንነትና ምሥጢራተ ቤተክርስትያንን የሚያከናውኑ(የሚፈጽሙ) ካህናት ወደ አብያተ ክርስትያናት ሄዶ ጳጳስ ማምጣት እንደ ሚያስፈልግ በመገንዘብ ይህን ሐሳቡ ለንግስቲቱና ለአብርሀ፣ለአጽብሓ አቀረበላቸው፡፡ንግሥቲቱም ሆነ ወጣቶቹ ነገስታትም ሐሳቡን ተቀብለው ፍሬሚናጦስ የኢትዮጵያን ቋንቋና ባህል በዚያውም ልክ የውጪውን ቋንቋና ባህል ያውቅ ስለነበረ እሱ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ ካህናትን ጳጳስን እንዲያመጣላቸው ላኩት፡፡ፍሬሚናጦስም የነገሥታቱን መልእክት ይዞ በ325 ዐ/ም ወደ እስክንድሪያ ሄደ፡፡የኢትዮጵያ ነገስታት የላኩትንም መልእክት ለእስክንድሪያው ፓትሪያርክ ለቅዱስ እስክንድሮስ አቀረበ፡፡ነገር ግን ቅዱስ እስክንድሮስ በወቅቱ ታምሞ ስለነበረ ብዙ ጊዜ ሳይቆይ በ328 ዐ/ም ዐረፈ፡፡ጉዳዩ ግን በእርሱ ለተተካው ለቅዱስ አትናቴዎስ ቀረቦለት ፍሬሚናጦስ መንፈሳዊ ሕይወትና እውቀት ያለው አባት ስለነበረ

በ330 ዐ/ም በቅዱስ አትናቴዎስ አንብሮት እድ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ስሙም ፍሬሚናጦስ የነበረው ስሙም አባ ሰላማ ተብሎ ተሰየመ፡፡(16)

ዝኒ ከማሁ

አቡነስላማማዕርገጵጵስናንተሾሞወደአክሱምበመጣጊዜነገሥታቱኢዛናናሳይዛናበክብርበደስታ ተቀበሉት፡፡ አቡነ ሰላማ ጵጵስናን ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ወንጌለ ክርስቶስን የማስተማር ሥራው ተያያዘው፡፡ በመጀመሪያ ነገሥታቱ ኢዛናንና ሳይዛናን ከበፊቱ በበለጠ አስተምሮ አጥምቆአቸዋል፡፡የክርስትና ስማቸውንም ‹‹ኢዛናን አብርሀ እና ሳይዛናን አጽብሐ›› ብሎ ሰይሞአቸዋል፡፡ቤተክርስትያን በዐራቱ የኢትዮጵያ ማዕዘን እንድትሰፋ፣ወንጌለ ክርስቶስ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደርስ ከፍተኛ ሐዋሪያዊ ትጋት አድርጎአል፡፡የወንጌል የእወቅት ብርሃን በኢትዮጵያ ስለአበራም የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ከሳቴ ብርሀን›› ቅጻላዊ ስያሜ ሰይሞታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅና ቅዱስ ያሬድ ይህን የአቡነ ሰላማ ሢመተ ጵጵስናን ሐዋሪያዊ ተልእኮን ሲገልጽ፦

‹‹ዓሣተ ሥላሴ ዜነ

ከዕለ ሐዋሪያት ዲቤሁ ተክዕወ፤ “ይክሥት ብርሃነ ተፈነወ አባ ሰላማ ዘድልው ለጵጵስና ሢመተ ክህነቱ ርቱዕ በሕገ ቀኖና”፡፡ በአማርኛ

‹ የሥላሴን ሥልጣን አበሰረ፤

የሐዋሪያት ሀብት በላዩ ላይ ፈሰሰ፤   ብርሃንን ሊገልጽ ተላከ

ለጵጵስና የተገባ አባ ሰላማ    የክህነቱ ሹመት በቀኖና ሕግ የተገባ ነው››፡፡

በማለት በሰማያዊ ዜማው መስክሮአል፡፡ አቡነ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ከዚህ በላይ በተገለፀው ትጋቱና በተመሰከረለት ሢመተ ጵጵስናው ወንጌለ ክርስቶስን አስተምሮ ብዙ ሕዝብን ካጠመቀ በኃላ ጠንካራና በሁለመናው የተደራጀ መንበረ ጵጵስናን በአክሱም አቋቋመ፡፡የክህነት አገልግሎት በስፋት እንዲሰጥ ከዱቁና ክስከ ኤጲሰ ቆጶሶነት ባሉት ማዕርገ ክህነትየሐዱስ ኪዳን ካህናትንሾመ፡፡

ሢመተ ካህናት

አቡነ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ሊቀ ጳጳስ ወንጌለ ክርስቶስን ከማስተማር ሐዋሪያዊ ተግበሩ ጎን ለጎን በአክሱም የብሉይ ኪዳን ደብተራ (ድንኳን) አገልጋዪች የነበሩትን ካሕናተ ኦሪት አስተምሮ ከሃይማኖተ አይሁድ ወደ ሃይማኖተ ክርስትና ከመለሳቸው በኃላ ካሕናተ ሐዲስ ኪዳን አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አንጠሮተ እድ እንደተሾሙ በታሪክ የሚታወቁ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን የሐዱስ ኪዳን ካህናት የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዲያቆናት ቀሳውስት ኤጲሶቆጶሳት
የብሉይኪዳንስማቸው የሐዲስ ኪዳን ስማቸው
፩  ፊንሐስ ተንሥአ ክርስቶስ ተክለሃይማኖት እንበረም-ሕዝበ ቀድስ
፪  አሮን ስምዖን ገብረመስቀል
፫  አዛርያስ ማቴዎስ
፬  አቤሜሌክ ዘእግዚእ
፭  ላእከሄኖክ አማኑኤል
፮  መልከጼዴቅ አሐዱ አምላክ
፯  ሳዶቅ ማዕቀበ እግዚእ

በሚል ስያሜ የሐዲስ ኪዳን ካህናት አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡እዚህ ከተገለፁት ካህናት መካከል የሁለቱ ቀሳውስት የብሉይ ኪዳን ስማቸው አልተገኘም፡፡በኋላ ሁሉንም ዲያቆናት ቀሳውስት አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡በቅዳሴ በሥርዐተ ቁርባን እና ሕዝቡን በማስተማር እንዲረዱት አድርጎአቸዋል፡፡ብፁዕ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በመንፈስ ቅዱስ አየተመራ ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮውን በተሳካ መልኩ በማከናወን ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሐምሌ ፳፮ ቀን  ዓረፈ፡፡ይህ ሐዋርያዊ ሰንሰለት ተያይዞ አሁን እስከ አሉ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት ቀሳውስትና ዲያቆናትደርሶአል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢጥዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዚህ ሐዋርያዊ ታሪክ አካል ናቸው፡፡

  1. የካም፣ የሴም፣ የኢስራኤል ወገኖች፣ ዘሮች ማለት ነው፡፡
  2. የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ( )የብሉይና የሀዲስ ኪዳን መጻህፍት
  3. budg(1922) the qeen of sheba and her only son Menylik,ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል (2005) የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ ጠቅላላ የቤተክርስትያን ታሪክ)ገጽ .151
  4. የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር (   ) የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት
  5. ኅሩይ ወልደ ሥላሴ(፲፱፻፹፩)(1991) ዋዜማ ገጽ፲፮-፲፯
  6. አባ ጎርጎሪዮስ የሸዋ ሊቅ ጳጳስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ታሪክ ገጽ .15
  7. ምክረ ሥላሤ ገ/አማኑኤል(ቀ.ዶ.ር(2005) የእግዚያብሔር መንግስት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተክርስትያን ታሪክ) ገጽ.156
  8. ማሕበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት (፲፱፻፶፫) ወንጌል ቅዱስ ሀእግዚአነ ወአምላክነ ወመድሓኒነ ኢየሱስ ክርስቶስገጽ.፻፺፫.
  9. sergew Hable selassie (1997) establishment of the Ethiopian church, in the church of Ethiopia, a panorama of history and spiritual life.P.3.
  10. መጽሐፈ ምሥጢር.ገጽ.
  11. አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ (  ) መርሐ ልቡና ገጽ 23፣24
  12. Sergew Hable Slassie(1997) The establishment of the Ethiopian church ,A panorama of history and spiritual life.p.3
  13. ምክረ ሥላሤ ገ/አማኑኤል(ቀ.ዶ.ር(2005)የእግዚያብሔር መንግስት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላየቤተክርስትያን ታሪክ) ገጽ.157