የጥምቀት በዓል አከባበር  በአኃት አብየተ ክርስቲያናት፤ በምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያንና በምዕራቡ ዓለም 

በመልአከ መዊዕ ሳሙኤል እሸቱ

የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ

የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተብለው የሚጠሩት በዋናነት ኮንስታንቲኖፕል የሚገኘውን ኢኮሚኒካል ፓትርያርክ ርእሰ መንበርነት  ተቀብለውና የራሳቸው የማይናወጥ አስተዳደርና ፓትርያርክ ኖሯቸው እምነታቸውን የሚመሩ የግሪክ ፤ሩሲያ፤ ቡልጋሪያ፤ ዩክሬን፤ ጆርጂያ፤ ቼክ፤ ቆጵሮስ፤ ቦስንያና ወዘተ … የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በምሥራቁ ኦርቶዶክስ ክፍለ ዓለም  ከልደት እስከ ጥምቀት ያለው ወቅት ኤጲፋኒያ ተብሎ ይጠራል፡፡የጥምቀት ጊዜ ደግሞ ቴዎፋኒ ይባላል፡፡ ኤጲፋኒያ አጠቃላይ የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ለመግለጽ የሚጠቀምበት ሲሆን ቴዎፋኒ ጥምቀቱንና በዚያም የተገለጠውን ምስጢር ለመግለጥ ሚጠቀሙበት ቃላት ነው፡፡ትርጓሜውም መገለጥ ፤ማሳየት አልፎ ተርፎም  ማሳወቅ ማለት ነው፡፡ይኸውም መድኅን ክርስቶስ ሥጋ በመልበስ ሰውን ለማዳን የተገለጠበትን ለማመልከት ነው፡፡በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ያለው የጥምቀት አከባበበር አብዛኛው ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም መንፈሳዊ ይዘቱንና ባህላዊ ክንውኑን በመጠኑ በዚህ ጽሑፍ እንዳስሳለን፡፡

በምሥራቁ በዓለ ጥምቀት (ኤጲፋንያ ፤የቴዎፋኒ) የገናን በዓል ተከትሎ የሚከበር ሲሆን እሱም ታኅሣሥ 29 ቀን ተጀምሮ ጥር 11 ቀን ያበቃል። በዘመነ ቴዎፋኒያ ታላቁ የውኃ በረከት በዚህ ቀን ይፈጸማል፣ የተባረከውን ቅዱስ ውሃ  ምዕመናን ይጠመቁበታል ።የአጥቢያው ካህንም የምእመናንን ቤቶች እየዞረ በቅዱሱ ውኃ ይባረካል፡፡

  • በግሪክኦርቶዶክስ 

በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ በዓላት መካከል ቴዎፋኒ (ኤጲፋኒያ) አንዱና ዋነኛው ሲሆን በዓሉ በበርካታ ክርስቲያናዊ ባህል በልጽጎ የሚከበር ነው ፡፡ ጌታ መጠምቁን  ተድላን እንፈጽም ዘንድ ግድ ነው  ብሎ  በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ  ወንዝ መጠመቁን የሚዘክር በመሆኑ የደስታና የሓሴት ቀን ተብሎ በግሪክ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ይከበራል፡፡በበዐሉ ከሚታየው ትርዒት መካከል  ካህኑ  ከቅዱስ መስቀል ጋር የውሃውን በረከት ይዞ በሕዝቡ ፊት በመቅረብ ለበዓሉ የሚገባውን ጸሎት

‹‹በዮርዳኖስ ወንዝ ውኃ ውስጥ፣ በዚህ ቀን የሁሉ ጌታ ዮሐንስን፡- አትፍራ እኔንም ከማጥመቅ ወደኋላ አትበል፤ እኔ አስቀድሞ የተፈጠረውን አዳምን ለማዳን መጥቻለሁና ብሎ ጮኸ››።

የሚለውን አሰምቶ በተከተረው ውሃ ወይም በወንዙ አልያም በሀይቅ  ቅዱስ መስቀሉን በወረወረ ጊዜ ዋናተኞች እየዘለሉ ወደ ውሃው ውስጥ በመግባት መስቀሉን ለማግኘት የሚያሳዩት ሥርዓትም በእጅጉ ማራኪ ነው። በዚህ ትዕይንት ውስጥ መስቀሉን ቀድሞ ይዞ ወደ ካህኑ የሚያመጣው ሰው  ዓመቱን ሙሉ ይባረካል ተብሎ ስለሚታሰብ በከፍተኛ ፉክክር የታጀበ ትዕይንት ይከናወናል።

በሀገራቸው የጥምቀት በዓል ልክ እንደ ገና  የራሱ ልዩ የምስጋና  መዝሙር አለው ከሚጠቀሱት መካከል

  ‹‹ዛብሎን ሆይ፥ ተዘጋጅ :ንፍታሌም ሆይ፥ ተዘጋጅ ! የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ጉዞህን ቀጥል እና አሁን ለመጠመቅ የሚመጣውን ሉዓላዊ ጌታን ለመቀበል በደስታ ዝለል። አዳም ሆይ ደስ ይበልህ እናታችን ሔዋን ደስ ይበልሽ፡፡በገነት ውስጥ እንደ ቀድሞው አትደብቁ።ራቁትህን አይቶ የፊተኛውን ልብስ ሊያለብስህ  ክርስቶስ  አሁን ተገለጠ። ፍጥረትን ሁሉ ለማደስ በእውነት ይፈልጋልና››

በባህላዊ ረገድ ልጆች ስለ በዓሉ እየዘመሩ ገንዘብ እና ጣፋጮች ምግቦችን ያገኛሉ፡፡ልጆች ከሚዘምሩት የጥምቀት ዜማዎች ውስጥ ቅዱስ ዮሐንስ ራዕዩን ባየበት  በደሴተ ፍጥሞ ላይ የተዘመሩ መዝሙሮች  የበዐሉን መልእክት የሚይዝ ነው፡፡ይህም  ዝማሬ የሚጀምረው ስለ ፍጥረተ ዓለም ስለ ውሃ አፈጣጠርና የእግዚአብር መንፈስ በውሃ ላይ ስለመስፈፉ እና በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ቀን ስለነበረው ክብር ይገልጻል፡፡ ማዕከላዊው ግሪክ  የበዓሉ ዋነኛ መስህብ የሚንጸባረቅበት ቦታ ሲሆን ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ሰዎች ልብስ ለብሰው ከቤት ወደ ቤት እየዞሩ ዜማውን እየዘመሩ ገንዘብ ይሸለማሉ።እያንዳንዱ ቡድንም በአለባበሱ ወቅት ሊያካትታቸው የሚገቡት  አልባሳት የሙሽራና ሙሽሪት ፤የቄስ ፣ የአያት ፣ የዶክተር እና በግሪክ ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን  አለባበስ መልበስ ግዴታቸው ነው፡፡ሌላው በጥምቀት የሚከናወነውን ጥንታዊ ሥርዓት ሰዎች ርኩሳን መናፍስትን ከከተማው ለማስወጣት በሚል አስፈሪ ጭምብሎችን ለብሰው ትርኢት በመሥራት ጭንብል የለበሱት ሰዎች ርኩሳን መናፍስትን የሚወክሉትን በማባረር የሚያሳዩት ትርኢት የበዓለ ጥምቀት አንዱ ገጽታ ነው

  • በሩስያኦርቶዶክስ

በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀት ልክ እንደ ግሪክ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ  በዓላት አንዱ ሲሆን መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን  በዮርዳኖስ ወንዝ ያጠመቀበት ቀን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው፡፡የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በጥምቀት ምሥጢረ ሥላሴ መተርጎሙን በዝማሬ እንዲህ እያለች በበዓሉ ታመሰግናለች

  ‹‹አቤቱ በዮርዳኖስ በተጠመክ ጊዜ የሥላሴ ሕልውና  ተገለጠ። አብ በድምጹ የተወደደ ልጄ ብሎ ሲጠራህ ልጅነትህን  መስክሮልሃልና። መንፈስም በርግብ አምሳል የቃሉን እውነት አረጋገጠ። የበሥጋ የተገለጥክ ዓለምን ያበራህ አምላካችን ክርስቶስ ሆይ ክብር ላንተ ይሁን››።

በሩሲያ በዓሉ በቤተ ክርስቲያንና በአደባባይ የማክበር ልማድ ያላቸው ሲሆን በመስቀል ቅርጽ በረዷማ ወንዞችን በመከተር በዓሉ ሲከበርም በቀዝቃዛው በወንዙ ውስጥ  ዘልቆ በመዘፈቅ በቀዘቀዘ በረዶ ውስጥ የመጠመቅ ወይም የመዋኘት ሥርዓት ይደረጋል፡፡

  • በቡልጋርያኦርቶዶክስ 

በቡልጋርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም  የበዓሉ አከባበር  በጣም የተለየ ክስተት አለው፡፡ በዋዜማው ቅዳሴ ተደርጎ ውሃን የመባረክ ሥርዓት ይደረጋል ሕዝቡና ካህናቱ እግዚአብሔር የምድሪቱን ውሃ እንዲባርክ ይጸልያሉ ፡፡በእምነታቸው የምድር ሁሉ ውሃ መባረኪያ ቀን የጥምቀት ቀን እንደሆነ ያምናሉ ፡፡

በጥምቀት ዕለት ያለው ባህላዊ ክዋኔ ዘማሪዎች(የባህል ዘፈን አቀንቃኞች) በቀዝቃዛ በረዶ ውሀ ውስጥ በመግባት ባህላዊውን ዘፈን እየዘፈኑ ቄሱ ለበዓሉ የሚስማማውን ጸሎት አድርጎ የሚወረውረውን መስቀል ለመያዝ ይጠባበቃሉ፡፡ በሌሎቹ ምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንደተመለከትነው  መስቀሉን ቀድሞ ያገኘ ወንዙ ውስጥ ባሉት ሰዎች  ተከቦ እየዘመሩ በዓሉን ያከብራሉ ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ምእምናን ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሁለንተናቸውን  ለመባረክ የተባረከውን ውሃ ወደ ቤታቸው በመውሰድ ዓመቱን ሙሉ በጠበልነት ይጠቀሙበታል ፡፡

  • በዩክሬንኦርቶዶክስ

በዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት  በዓል ብዙ ልማዶች እና ወጎች አሉት፡፡ ልክ እንደ ሌሎቹ የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን በባህር ዳርቻ የሚደረገው ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ጊዜ ጾምን የሚጨርሱበት ወቅት በመሆኑ  ለጥምቀት ልዩ ልዩ ምግቦችን በማዘጋጀት የመጀመሪያው ኮከብ በሰማይ ላይ ከታየ በኋላ እራት ይመገባሉ፡፡ በእርግጥ ዋናው በዓል  ውሃን መቀደስ የሚለው በመሆኑ ካህኑ መስቀልን  “ዮርዳኖስ” ተብሎ ወደ  ሚጠራው ልዩ ሆኖ  በተሠራው የበረዶ ጉድጓድ ውስጥ አድርጎ ጸሎቱን ያቀርባል ሲጨርስ ውሃው ኢየሱስ እንደተጠመቀበት  እንደ ዮርዳኖስ ወንዝ ቅዱስ ስለሆነ በሽታ ሊፈውስ በሚችል ልዩ ባሕሪያትና ኃይል እንዳለው ሲያውጅ አማኞች በዚህ ውኃ ለመዘፈቅ ተሸቀዳድመው ይገባሉ  ፡፡በዚህ ውሃ በመጠመቅ ከሥጋ ደዌና ከአእምሮ በሽታ እንደሚፈወሱ ያምናሉ ፡፡ከቅዱስ ውሃ በመውሰድም  ቤታቸውንና ግቢያቸውን በመርጨት ክፉ መናፍስትን ያርቁበታል፡፡

  • በኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን

የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓልን ቀደም ባሉ ጊዚያት ከባህላዊው ኪያክ  ወር ጋር ተገጣጥሞ ቀደም ባሉት ጊዚያት ወደ ዓባይ ወንዝ በመውረድ የሚከበር የነበረ ሲሆን  በአሁኑ ወቅት ግን በዓሉን በአደባባይ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን  በቅዳሴ ሥርዓት ታጅቦ ይከበራል ፡፡

  • በምዕራቡዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት

በምዕራቡ ዓለም ያለውን የጥምቀት አከባበር ስንቃኝ  በሁለት ዝግጅቶች ላይ በዋናነት ያጠነጠነ ነው፡፡  እርሱም የጥበብ ሰዎች ለሕጻኑ ኢየሱስና ለእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የሰጡት ስጦታና በቃና ገሊላ ስለተደረገው ሠርግና ተአምራት በማዘከር ነው፡፡ ሰብአ ሰገል  ሕፃኑንና እናቱን ማርያምን በኮከብ ተመርተው በማግኘት ስጦታ ወይም አምኃ እንዳቀረቡ ሁሉ አማኞቹ  ከልጆች ጋር የስጦታ ዝግጅትን በማድረግና ስጦታን በመስጠት ያከብራሉ፡፡

ማጠቃለያ 

የጥምቀት በዓልን አከባበር ከላይ በሁሉም ሀገርና አብያተ ክርስቲያናት እንደቃኘነው አብዛኛዎች በጥቂት ቁጥርና በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በዓሉን ያከብራሉ፡፡ የአከባበር ሁኔታውም ቢሆን በከተማና በገጠር በተለያየ ሁኔታ ያከናውኑታል፡፡ ዘመናዊነት እንደፈጣን አውሎ ንፋስ ምድራችንን እያጥለቀለቀ ባለበት በዚህ ጊዜ መሠል በዓላትን በጥቂቱም ቢሆን እያከበሩ የሚገኙት ኦርቶዶክሳውያኑ አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን ስናይ የወንጌል እውነት እንዳይበረዝ ባህልና ወግ እንዳይጠፋ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ባለውለታ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከሁሉም ግን የሚያስደንቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ለሁለት ሺህ ዓመት ይህን እውነት ጠብቃ በዓላትን በአደባባይ እንዲከበር ማድረጓ በእምነት የጸናች በነጻነቷ የተከበረች ባህልና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ተባለች ሀገር በአፍሪካ ምድር እንደ እንቁዕ እንድታበራ አድርጋለች ለዚህም ነው ኦርቶዶክስ ሀገር ናት ያስባለው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር