ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለ272 አገልጋዮች ሥልጣነ ክህነት ሰጡ።

ነሐሴ ፲፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በዓለምገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተገኝተው ለ272 የአብነት ተማሪዎችና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሥልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።
ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና ብፁዕ ዋና ፀሐፊው በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ተምረው ፈተና ላለፉ ለ238 የዲቁና፣ ለ 33 የቅስና ሥልጣነ ክህነት ለ1 አባት ደግሞ የቁምስና ማዕርገ ክህነት ሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አባቶቻችን በጊዜያቸውን ቤተክርስቲያንን አገልግለው ለእኛ እንዳስረከቡን ሁሉ እኛ ደግሞ በጊዜያችን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተሳካና የተቃና ይሆን ዘንድ ያለ ዕረፍት ለ24 ሰዓት እያገለገልን ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ምትክ አገልጋይ እንደሚያስፈልጋት በመግለጽ ትምህርታቸውን ሲከታቱሉ ቆይተው ትምርታቸውን ላጠናቀቁ ሥልጣነ ክህነት እንደሰጡ ተናግረዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዛሬ ዕለት ሥልጣነ ክህነት ለተቀበሉ ሁሉ ሃይማኖታቸውን ጠንክረው በመጠበቅ በትጋት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስም ክህነት መጠራት መሆኑን በመግለጽ ቅዱሳን ሐዋርያት ከልዩ ልዩ የሥራ መስክ ተጠርተው ቤተ ክርስቲያንን እንዳስፋፉ ሁሉ በዛሬው ዕለት ሥልጣነ ክህነት ለተቀበሉ አገልጋዮች ሰው ካልተማረ ማገልገል ኣይችልምና የቀረባቸውን ትምህርት በደምብ በመማርና የጎደላቸውን ትምህርት በማሟላት ምእመናንን በማስተማር የቤተ ክርስቲያን ተከታዮችን ማብዛትና መጠበቅና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ክህነት ሰማያዊ እና ሰማያዊ ንጉሥ ለማገልገል መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ፣ በዛሬው ዕለት በክህነት እንድታገለግሉ ተጠርታቹኋል፤ የሰው አገልጋዮች ሳትሆኑ የሰማያዊ ንጉሥ አገልጋዮች ናችሁ፤ አሁን ተቀብታቹኋል ተቀድሳቹኋል እና በትሕትና በቅድስና ሁናችሁ ማገልገል አለባችሁ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኅን ሥርጭት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አካለወልድ ተሰማ፣ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ዓለማዮ ተፈራ፣ ሊቀ ሥዩማን ተስፋዬ ለሜቻ የሸር ከተመ ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ፣ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሐረት ፀጋዬ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

የደብረ ታቦር በዓል በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ከምታከብራቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዓበይት በዓላት አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በተለምዶ ቡሄ በመባል ይታወቃል፡፡
በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የገዳሙ አገልጋዮችና እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የደብረ ታቦር በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል /ማቴ. ፲፯፥፩፤ ማር.፱፥፩፤ ሉቃ.፱፥፳፰/፡፡ በዚህ በዓል መለኮታዊ ክብሩ፣ የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት ይተረጎምበታል፡፡
የገዳሙ የደብረ ታቦር በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት በዓሉ ሲከበር ዘንድሮ ለ53ኛ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “የተሰባሰብንበት ዋና ዓላማው የደብረ ታቦርን በዓል ለማክበር ሲሆን የበዓሉ አከባበር ቀደም ባሉት ጊዜያት በገዳሙ ይኖሩ በነበሩ ጥቂት ዲያቆናትና የመነኮሳት አርድእት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በየዓመቱ በዳቦና ሻይ ከማክበር ተነሥቶ ፈቃደ እግዚአብሔር ተጨምሮበት ለበርካታ ዓመታት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህ ታላቅ በዓል መከበር ከጀመረ 53ኛ ዓመቱን” ይዟል፡፡
ሪፖርቱ አያይዞም በገዳማችን ይህ በዓል ሲከበር ተመሳሳይ ዓላማ ቢኖረውም ነገር ግን ከዚህም ባለፈ በገዳሙ የነበሩ አባቶችና ወንድሞች በተለያየ የሕይወት አጋጣሚ ከገዳሙ ሲወጡ በዚያው ርቀው እንዳይቀሩ ይህንን ገዳም እንደራሳቸው ቤት እንዲመለከቱ ለማድረግም ጭምር ሲሆን በፍቅር ይህን በዓል ሲታደሙ ከአዲሱ ትውልድ ጋር ለመተዋወቅና ለመቀራረብ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “ይህ በዓል በቤተክርስቲያናችን ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው የከፍታ በዓል ነው፤ ከፍ ያሉ ዝቅ፣ ዝቅ ያሉ ከፍ ያሉበት በዓል ነው፡፡ ሕያዋን ሙታን የተገናኙበት፣ ሙሴና ኤልያስ በመካከላቸው ሰፊ ዘመናት ያላቸውን እግዚአብሔር ያገናኘበት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ ያዕቆብና በዓል ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ሰውን እንደሚያገናኝ እናያለን፡፡ ይህም ቤተክርስቲያን የተለያዩ ሰዎችን በአንድነት እንደምታገናኝ የሚያሳይ ነውና በሌላ በኩል ይህ በዓል በአብነት ትምህርት ቤት የተማሪ በዓል ይባላል፤ ተማሪዎች ለምነው ስኮላርሺፕ የሰጣቸውን ሕዝብ የሚመግቡበት፣ የራሳቸውን ፍቅር ያሳዩበት በዓል ነው፡፡” ሲሉ ገልጻዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ባስተላለፉት መልእክት “በዛሬው በገዳማችን በሚከበረው በዓል ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ስለተገኙ አመሰግናለሁ፡፡ በዚህ ገዳም በቀደሙት ዓመትት በየዓመቱ ተማሪዎች የደብረ ታቦር በዓል ያከብሩ ነበር፡፡ ዛሬም የገዳሙ ዲያቆናት የቀደሙትን መሠረት በማድረግ ሰው አስተባብረው በጋራ የሚያከብሩት፡፡ እግዚአብሔር ሰላሙን ሰጥቶ በሰላም እንድናከብር ያደረገ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ የሰለላም በዓል ያድርግልን” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ለመግለጽ የታቦር ተራራን የመረጠው፤ ትንቢትና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱ፡- “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ወይሴብሑ ለስምከ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” /መዝ. ፹፰፥፲፪/ በማለት ነቢዩ ዳዊት ትንቢት ተናግሮ ነበርና ጌታም ብርሃነ መለኮቱን በታቦር ተራራ በመግለጹ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ ምሳሌው፡- ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ይኸውም መስፍኑ ባርቅ ሲሣራን በታቦር ተራራ ድል ነስቶታል /መሳ. ፬፥፬—፳፬/፡፡
የደብረ ታቦር በዓል በቤተክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ማሕሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው “በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርኩልህ” የሚለው መዝሙር በመዘመር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ተሰጥቶት ይውላል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት ሃይማኖትን የሚማሩ ናቸውና ለሐዋርያት ነገረ መለኮቱን የገለጠ አምላክ እንዲገልጥላቸው በዓለ ደብረ ታቦርን በተለየ ድምቀት ያከብሩታል፡፡ በዚህም መሠረት በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳምም በዓሉ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በባሕታዊ አባ ተስፋ ማርያም ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ኅዘን በመግለጽ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፤ የብፁዕነታቸው አባታዊ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል::

የኃዘን መግለጫ
‹‹ነገረ ገድሉ መዓርዒር፣ ለተናግሮ ዕፁብ ግብር፣ ወዲበ ርእሱኒ አክሊል ዘየዐስዮ መኰንነ ጽድቅ…. የተጋድሎው ነገር ያማረ፣
ሥራውም ለመናገር ድንቅ የሆነ፣ በራሱም ላይ መኰንነ ጽድቅ እግዚአብሔር የሚያስረክበውን ድል የመንሣት አክሊል የሚቀዳጅ ነው›› (2ጢሞ 4÷8፤ቅዱስ ያሬድ ዘእምነገረ ቅዱስ አትናቴዎስ)
የላመ የጣመ ሳይቀምሱ፣የሞቀ የደመቀ ሳይለብሱ፣በዐት አጽንተው፣ሥርዓተ ምንኵስናውን አክብረው ድንቅ በሆነ
መንፈሳዊ ተጋድሎ ከ50 ዓመት በላይ የኖሩት፣ ለራያና አካባቢው
ሕዝበ ክርስቲያን የእምነትና የመንፈስ ጽናት ምሳሌ የነበሩት ባሕታዊ አባ ተስፋ ማርያም ጌታሁን ማረፋቸውን የሰማነው በከፍተኛ ኃዘን ነው፡፡
ከዓለማዊ ግብር በመለየት፣ እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት የብሕትውናውን ሕይወት በእውነት የኖሩት እኒህ አባት ነቀፋ የሌለበት እምነታቸውና የምነና ሕይወታቸው በእግዚአብሔርና በሰው ፊት የከበረ በመሆኑ የጽድቅ ባሕርይ ምሳሌ ሆነው በምንኵስና ተጋድሎ ታሪክ በክብር ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡
በመከራ ከተሞላው ከዚህ ክፉ ዓለም ድካም ማረፍ ለእርሳቸው የማይጠፋ የሕይወት አክሊልን የሚቀዳጁበት ቢሆንም በፍቅር የሚገሥጽ፣በመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያንጽ አባትን ማጣት ለእኛ ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሆነ ጥላቻንና መራራቅን የሚያሰፉ ንግግሮችና ድርጊቶች በበዙበት፣ሕዝባችን በልዩ ልዩ ችግር ውስጥ ባለበት፣በዚህ ጊዜ ለእውነትና ለፍትሕ ቆመው የኖሩትን፣
በጸሎት በምክር የሚረዱንን እኒህን ደግና ታላቅ አባት በማጣታችን ኀዘናችንጥልቅ ነው፡፡
በመሆኑም በባሕታዊ አባ ተስፋ ማርያም ጌታሁን ሕልፈተ ሕይወት የተሰማንን ኃዘን እየገለጸን ለእርሳቸው ዕረፍተ ነፍስን ለመላው የራያና አካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን መጽናናትን
እንመኛለን፡፡
ነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
አባ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ ጠቅላዬ ሥራ አስኪያጂና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው ቤተክርስቲያን የምታከናውናቸውን የልማት ሥራዎች አፈጻጸምን ተዘዋውረው ተመለከቱ።

ነሐሴ 11ቀን 2018 ዓ.ም አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአራት ሳይቶች ማለትም በአራት ኪሎ፣በፒያሳና በአሮጌው ቄራ አካባቢ የምታስገነባቸውን ግዙፍና ሁለ ገብ የሕንጻ የግንባታ ሥራዎች የሚገኙበትን አፈጻጸም ደረጃ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ብፁዓን አባቶቹ በጉብኝታቸው ወቅት የግንባታ ሥራውን በሚያከናውኑ ባለሙያዎችና በጠቅላይ ቤተክህነት መሐንዲሶች ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን በየሳይቶቹ ከተመዘገቡት ውጤቶች በመነሳት ቀሪ ሥራዎች በተቀላጠፈና ውጤታማ በሆነ መልኩ መከናወን እንዲችሉ አስፈላገው ክትትልና ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን በመግለጽ አመራር ሰጥተዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት 14ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በመከበር ላይ ይገኛል።

ነሐሴ 10ቀን 2018 ዓ.ም
የአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም ምክር ቤት የክብር ፕሬዚደንት አሥራ አራተኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እየተከበረ ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሐምሌ 5 ቀን 1986ዓ.ም. ጀምሮ ለ20 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በርእሰ አበውነት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በ76 ዓመት ዕድሜያቸው ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ሐሙስ ከንጋቱ 11 ስዓት ላይ በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል የሕክምና ርዳታ ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር የመደበላቸውን ጊዜ በታማኝነትና ይህ ቀረው በማይባል ስኬት አጠናቀው ከዚህዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በጾመ ማርያም የመጀመሪያውን ሳምንት ሱባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቀድሰው በማቊረብና በማስተማር መሰንበታቸውና የመጀመሪያው ሳምንት ሱባኤ በተጠናቀቀበት ወቅት፦ “አባቶች ሱባኤው ተጠናቋል” በማለት በወቅቱ አብረዋቸው ለነበሩ ብፁዓን አባቶች መግለጻቸውና አባቶችም፦ “ቅዱስ አባታችን ገና እኮ ሳምንት ይቀራል” ሲሏቸው “የእኔን አጠናቅቄአለሁ”ማለታቸውን ብፁዓን አባቶች ያስታውሳሉ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ1928 ዓ.ም. በትግራይ ክፍለ ሀገር በአድዋ አውራጃ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው በሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመጀመር በዚሁ ገዳም ከዲቁና እስከ ምንኩስና መዓርግ የደረሱ ሲሆን፤ በመቀጠል የቤተ ክርስቲያንን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ዕውታቸው ጣምራ ችሎታ የነበራቸው ለመንበረ ማርቆስ የተገቡ ዓለም አቀፋዊ የጥበብ ሰው እንደነበሩ፡፡ የውጭ ምሁራን ሳይቀሩ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ታላላቅ ምሁራን ውስጥ አንዱ የሆኑና በኢትዮጵያ አርእስተ አበው (ፓትርያርኮች) ታሪክ ውስጥ ወደር ያልተገኘላቸው ብቸኛው ፓትርያርክ ናቸው” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተውላቸው ነበር።
ስም ወደ ሥራ ይመራል እንዲሉ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የመናገር ተሰጥዖ የነበራቸው፥ በወንጌል ስብከታቸው የብዙኃኑን ልቡና የዳሰሱና አጥንትን የሚያለመልም አንደበት የነበራቸው የወንጌል ገበሬ ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው በፓትርያርክነት ዘመናቸው ያስመዘገቡት አስደናቂ ታሪክ ሁሉ በተጋድሎና በፍጹም የእምነት ጽናታቸው መሥዋዕትን ከፍለው የሠሩት እንጂ ነገሮች ሁሉ ቀና ሆነው የአልጋ በአልጋ የሆነ ውጤት የተመዘገበበት አልነበረም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለሀገር ሰላምና ዕድገት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በሀገራዊ ፍቅር በሰላምና በፍቅርበጋራ እንዲሠሩና ሀገራቸውን እንዲገነቡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂነታቸው አማካኝነት ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል፤ ተጨባጭ ውጤትም አስመዝግበዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥም በሁሉም የሃይማኖት አባቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፉ አባትም ነበሩ፡፡

ስምከ ሕያው ዘኢመውት ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፤ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም ምክር ቤት የክብር ፕሬዚደንትና የዓለም የሰላም አምባሳደር ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ከተለዩን እነሆ አሥራ አራት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡
እነዚህ አሥራ አራት ዓመታት ውስጥ ቅዱስነታቸውንና ሥራዎቻቸውን የሚዘክሩ በተቋም ደረጃ የተጻፉም ሆነ ዝክረ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተከናወነ ምንም ዓይነት ሥነ ሥርዓት አለመደረጉ ዘወትር የሚያስቆጭና በምክንያትነት የሚገለጽ አንዳች ነገር አለመኖሩ ደግሞ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ እዚህ ላይ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አማካኝነት በየዓመቱ የሚደረገውን ዝክረ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አለማድነቅና ምስጋና አለመቸር ትዝብት ላይ ይጥላልና ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን በማመስገን ረጅም ዕድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር ስንመኝላቸው የቅዱስነታቸው በረከት እንዳይለያቸው ከመጸለይ ጋር ነው፡፡ እናም በዚህ ጽሑፍ ላይ ቅዱስነታቸውን እንደሚከተለው እንዘክራቸዋለን፡፡
ቅዱስነታቸው ከሐምሌ 5 ቀን 1986ዓ.ም. ጀምሮ ለ20 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በርእሰ አበውነት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በ76 ዓመት ዕድሜያቸው ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ሐሙስ ከንጋቱ 11 ስዓት ላይ በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል የሕክምና ርዳታ ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር የመደበላቸውን ጊዜ በታማኝነትና ይህ ቀረው በማይባል ስኬት አጠናቀው ከዚህዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በጾመ ማርያም የመጀመሪያውን ሳምንት ሱባኤ በመንበረ ፓትርያርክቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቀድሰው በማቊረብና በማስተማር መሰንበታቸውና የመጀመሪያው ሳምንት ሱባኤ በተጠናቀቀበት ወቅት፦ “አባቶች ሱባኤው ተጠናቋል” በማለት በወቅቱ አብረዋቸው ለነበሩ ብፁዓን አባቶችመግለጻቸውና አባቶችም፦ “ቅዱስ አባታችን ገና እኮ ሳምንት ይቀራል” ሲሏቸው “የእኔን አጠናቅቄአለሁ”
ማለታቸውን ብፁዓን አባቶች ያስታውሳሉ፡፡ እንዳሉትም በነጋታው ሆስፒታል ገብተው ለሦስት ቀናት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን በከፍተኛ ኃዘን በማስታወስ ቅዱስነታቸውን መዘከራችንን እንጀምር
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ1928 ዓ.ም. በትግራይ ክፍለ ሀገር በአድዋ አውራጃ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው በሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመጀመርበዚሁ ገዳም ከዲቁና እስከ ምንኩስና መዓርግ የደረሱ ሲሆን፤ በመቀጠል የቤተ ክርስቲያንን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በመግባት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል፡፡
በነበራቸው ትጋትና ልዩ የመማር ፍላጎት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድ ወደ አሜሪካ ለከፍተኛ ትምህርት ተልከው በሴንት ቭላዲሚ ርኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ኮሌጅና በሌሎችም የትምህርት ተቋማት በመማር ተደራራቢ ዲግሪዎችን አግኝተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጵጵስና ጊዜያቸው በደርግ አገዛዝ ለ7 ዓመታት በእስር ቤት ቆይተዋል፡፡ ከዚያም ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ ወደ አሜሪካ በመመለስ የጀመሩትን ትምህርት በመቀጠል በታላቁ በፕሪስቶን ዩኒቨርሲቲ ፒኤች.ዲ. ዲድግሪያቸውን ሠርተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሕፃንነት ዕድሜያቸው ጀምረው በገዳማዊ ሥርዓትና ሕግ ያደጉ፤ በክርስቶስ ወንጌል ምክንያት የታሠሩ፤ በአጠቃላይ እንደ ወርቅ ተፈትኖ ያለፈ ሕይወት የነበራቸውና በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ዕውቀት በጣምራ ችሎታዎች የተካኑ ዓለም አቀፍ አባት ነበሩ፡፡
ቅዱስነታቸው ረቡዕ ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሱባዔውን ጸሎት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በተሰማቸው ሕመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱና ያለምንም ስቃይና ጻዕረ ሞት እንዳረፉ ይነገራል፡፡ ይህም ቅዱስነታቸው “እኔ የምፈልገው እንደ አባቶቼ በሰላም ማንቀላፋት ነው” በማለት ዘወትር ፈጣሪያቸውን ሲለምኑ የነበረው ልመናቸው በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ነው፡፡ በሌላ በኩልም የቅዱስነታቸውን ጻድቅነትና ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን ቀረቤታ ይመሰክራል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ዕውታቸው ጣምራ ችሎታ የነበራቸው ለመንበረ ማርቆስ የተገቡ ዓለም አቀፋዊ የጥበብ ሰው እንደነበሩ፡፡ የውጭ ምሁራን ሳይቀሩ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ታላላቅ ምሁራን ውስጥ አንዱ የሆኑና በኢትዮጵያ አርእስተ አበው (ፓትርያርኮች) ታሪክ ውስጥ ወደር ያልተገኘላቸው ብቸኛው ፓትርያርክ ናቸው” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተውላቸው ነበር። ስም ወደ ሥራ ይመራል እንዲሉ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የመናገር ተሰጥዖ የነበራቸው፥ በወንጌል ስብከታቸው የብዙኃኑን ልቡና የዳሰሱና አጥንትን የሚያለመልም አንደበት የነበራቸው የወንጌል ገበሬ ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው በፓትርያርክነት ዘመናቸው ያስመዘገቡት አስደናቂ ታሪክ ሁሉ በተጋድሎና በፍጹም የእምነት ጽናታቸው መሥዋዕትን ከፍለው የሠሩት እንጂ ነገሮች ሁሉ ቀና ሆነው የአልጋ በአልጋ የሆነ ውጤት የተመዘገበበት አልነበረም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን ምሁራን “ሰማዕት ዘእንበለ ደም” በማለት ለሠሩት መልካም ሥራ በመመስገን ፈንታ ይወረወርባቸው የነበረውን የቃላት ሰይፍ ለመግለጽ እንደተጠቀሙበት በወቅቱ ተመልክተናል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያውያን ፥ ከዚያም አልፎ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ በሰላምና በመተሳሰብ በእግዚአብሔር ዓለም በፍቅርና በአንድነት እንዲኖርበማስተማርና እንዲቀራረብ በማድረጉ ሥራ ታሪክየማይዘነጋ ውጤትን አስገኝተዋል፡፡
በሀገር ውስጥና በአፍሪካም፥ በኢትዮጵያና በኤርትራ˖ እንዲሁም በሱማሌ የእርስበርስ ጦርነትን ለማስቆም፥ _ በጦርነቱ የተጎዱትንም በመርዳት፥ በደርግ ዘመን ያሰሯቸውን የደርግ ባለሥልጣናት በማስፈታትና ግብረ ሰዶማዊነትን በግልጽ በአደባባይ በመቃወም ሌት ከቀን በትጋት ሠርተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው “ከአፍሪካውያን የበለጠ አፍሪካን የሚወድ ማንም የለም” ስለዚህ በአፍሪካ ላለው የሰላም ችግር“አፍሪካዊ መፍትሄ ማግኘቱ ወሳኝ ነው” በሚሉት ስሜት ቀስቃሽና በጥበብ የተቀመሙ አነጋገራቸው በብዙኃኑ የውጪውን ብረተሰብ ጭምር ይታወቃሉ ::
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለሀገር ሰላምና ዕድገት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በሀገራዊ ፍቅር በመተሳሰር በሰላምና በፍቅርበጋራ እንዲሠሩና ሀገራቸውን እንዲገነቡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂነታቸው አማካኝነት ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል፤ ተጨባጭ ውጤትም አስመዝግበዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥም በሁሉም የሃይማኖት አባቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፉ አባትም ነበሩ፡፡
የቅዱስነታቸውን ታላቅ የሥራ የሰላምና የፍቅርሰውነት በሀገር ውስጥና _ በውጪው ዓለም የሚገኙ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች፡ እንዲሁም የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ መሪዎች በኃዘን መግለጫቸው ደጋግመው በመዘገብ የቅዱስነታቸውን ታላቅ ሰብእና በማጉላት መስክረውላቸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለዓለም ሰላምና ለሰብአዊ ርኅራኄ ሥራዎች ባደረጓቸው ጉልህ ዓለም አቀፍ ውጤቶች በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይኮሚሽን የናንሰን (Nansen) ሜዳልን ተሸልመዋል፡፡ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባደረጉት አስተዋጽኦም ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው ዓለም የፍቅር ዐይኑን ያሳረፈባቸው፥ በታላቅ መንፈሳዊ አባትነታቸው ያመነባቸው የሰላምና የመቀራረብ ማሳያ የነበሩ መሆናቸውን ያለ ልዩነት የሚስማማበት ሀቅ ነው፡፡
ለዚህም ምስክሩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክርቤት ፕሬዚደንት አድርጎ የመረጣቸው መሆኑ፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት ሆነው እንዲሠሩ ያደረጋቸው መሆኑ፤ የዓለም የሰላም አምባሳደርነትን ሥልጣን በማግኘት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና የመጀመሪያው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ _ መሆናቸው ለማሳያነት በቂ ይሆናሉ፡፡ ሌላው ቅዱስነታቸውን ልዩ የሚያደርጋቸው ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ሥልጣን ከበቁበት ዕለት ጀምረው የእረፍት ጊዜ ሳይኖራቸው በየሆስፒታሉ፥ በየእስር ቤቱ እየሄዱ በመጠየቅ ለሞቱት ወገኖቻችን ከካህናት ጋርእኩል ቆመው ጸሎተ ፍትሃትን በማድረግ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚጋሩ ትሑትና ሰው አክባሪ አባት ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው የበደላቸውን ይቅር የሚሉና የሚሾሙ፥ ከዚህ በፊት በድሎኛልና ልበቀለው የማይሉ ፍጹም የይቅርታ አባትም ነበሩ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተጠሩበት ከፍተኛ የፓትርያርክነት ሥልጣን በሥራቸው የሚተማመኑ የሚወሰኑና በሚያደርጉት ሁሉ በልበ ሙሉነት ሃላፊነትን ለመውሰድ ወደኋላ የማያፈገፍጉ ፍጹም የአመራርና የእውነት ሰው ነበሩ ለዚህም ችሎታቸው በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያከናወኗቸው ሥራዎች ሕያውና ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዘመነ ሢመታቸው ያለ ዕረፍት በመሥራት ጽሑፍ የማይወስነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ከቤተ ክርስቲያናችን አልፎ ለመላው ኢትዮጵያዊ ኩራት የሆነ ሕያው ሥራን በማከናወን ተጨባጭ ውጤቶችን ያስመዘገቡ ፓትርያርክ ነበሩ ቢባሉ የሚበዛባቸው አይሆንም፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ሢመት ቤተ ክርስቲያን የተረሣውን ታሪኳን አድሳ˖ የተወረሰውን ንብረቷን አስመልሳ፥ እንደገና በሕያውነት የተንቀሳቀሰችበት˖ በዓለም _ አቀፍ ደረጃ የታሪክና የሉአላዊነት ብኩርናዋን ያረጋገጠችበት፥ ድምፅዋ በዓለም ጆሮ ተሰሚነትን፥ ሥራዋ ትኩረትን ያገኘበት ዘመን ነበረ፡፡ ይህም በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ዓለም አቀፋዊ ቅርጽን የያዘችበት ወቅት እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ሊኖሩን የሚገባ ተቋማት ቢኖሩ ትምህርት ቤቶች ናቸው በማለት ቅዱስነታቸው የሰጡትን አባታዊ መመሪያ ተከትሎ መክነው የነበሩ ጥቅም አልባ ቦታዎች ዛሬ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ የሕክምናና ሌሎች ለኅብረተሰቡ ጥቅም የሚሰጡና ለቤተ ክርስቲያናችን የገቢ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉ ተቋማትን ማስገኘት ችለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እስከአሁን ድረስ በሀገርውስጥ ካከናወኗቸው ዐበይት የሥራ ውጤቶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ከ50 በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተተኪ የሆኑ አባቶች ኤጲስቆጶሳትን ሹመዋል፤ ለብዙ ዓመታት ተወርሰው የቆዩትን የቤተ ክርስቲያን ሀብታት አስመልሰው የቤተ ክርስቲያንን _ መብት በማስከበር ቤተ ክርስቲያናችን በሀብቷ እንድትጠቀም አድርገዋል፤
ታላቁ የቤተ ክርስቲያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነውንና በደርግ ዘመን ተወርሶ የነበረውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን አስመልሰው _ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል፤ አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንም አቋቁመዋል፤
ቀደም ባሉት ዘመናት የቤተ ክርስቲያኒቱ የገቢ ምንጭ የነበሩና በደርግ ዘመን የተወረሱትን ታላላቅ _ ሕንጻዎች አስመልሰዋል፤
በደርግ ዘመን ተዘግተው የነበሩትን የአብያተ ክርስቲያናት ዋና በሮች እንዲከፈቱ በማድረግ ምእመናን እንደ ልብ በሚቀርባቸው የመግቢያ በርበነፃነት ገብተው ጸሎታቸውን ማድረስ እንዲችሉ አድርገዋል፤
ቤተ ክርስቲያን የልዩ ልዩ ከፍተኛ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ትምህርት ቤቶች፥ የሕክምና፥ የተግባረ ዕድና የሌሎችም የመሳሰሉት ከፍተኛ ተቋማት ባለቤት በመሆን ራሷን መቻል የምትችልበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፤ ይህ በመሆኑም ዛሬ አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባለቤት እንዲሆኑ አድርገዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ የኮሌጆች˖ የክሊኒኮች፥ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ታላላቅ ሕንጻዎች ባለንብረት እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
ሥራ ታዲያ ለቤተ ክርስቲያን የተሟላ ሕይወት የጀርባ አጥንት የሆነ ተግባር በመሆኑ በመላዋ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይህንኑ ልምድ በመውሰድ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
ቅዱስነታቸው ለቀደምት አባቶቻችን ታላቅ ክብርን የሚሰጡ፥ ለቅርሶች መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡ አባት በመሆናቸው በውጭ መንግሥታት ተዘርፈው የነበሩ የታሪክ ቅርሶችና ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲመለሱ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ስኬታማ በመሆን የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት የሆኑ ቅርሶች እንዲመለሱ አድርገዋል ከእነዚህ መካከልም የአክሱም ሐውልትና አፍሮ አይገባ መስቀል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኘው ጥንታዊ ቅርስም በአንድ ማዕከል በዘመናዊ አደረጃጀት ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በነበራቸው ጽኑ አቋምም የቤተ ክርስቲያንና የሀገሪቱ አኩሪ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶችን ዓለም አቀፋዊ በሆነ ደረጃ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ሀገርጎብኝዎች ዝግጁ ሆኖ መቅረብ እንዲችል የአክሱም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን በዘመናዊ መንገድ ማስገንባት ጀምረው ፍጻሜውን ሳያዩ ቀርተዋል፡፡ ፕሮጀክቱም የቅዱስነታቸውን ሕልፈት ተከትሎ ቆሟል ለማለትያስደፍራል፡፡
አማርኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ የተደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያናችን የእምነትና የታሪክምንጭ የሆኑ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ከግእዝ ቋንቋ ወደ አዳዲስ መጻሕፍትም እንዲዘጋጁ የተመቻቸ ዕድል እንዲፈጠር በማድረጋቸው በዘመነ ሢመታቸው 81ዱ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ አያሌ መጻሕፍት ታትመው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንትና ባለፉት ሃያ ዓመታት አገልግሎታቸው ያከናወናቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በዚህ አጭር ጽሑፍ ቀርቶ ራሱን በቻለ መድብልም መግለጽ አይቻልም ለበረከትና ቅዱስነታቸውን ለመዘከር ያህል በመጠኑ ይህን ካቀረብን ወደፊት በዝርዝር የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በመዘገብ የቤተ ክርስቲያናችንን ውጤታማ ተግባራት ለመግለጽ የምንሞክር ሲሆን፤ የእውነት አምላክ እግዚአብሔር የቅዱሱን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነፍስ ከወዳጆቹ ከአብርሃም ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጎን ያኑርልን የቅዱስነታቸው በረከትና ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለተመደቡት ለመልአከ ብርሃን መምህር ሰሎሞን በቀለ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
መልአከ ብርሃን መምህር ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው መመደባቸውን ተከትሎ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ በመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ከህነት ሥራ አስኪያጆች፤ የሀገረ ስብከቱና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሠራተኞች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ አደራሽ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
መልአከ ብርሃን መምህር ሰሎሞን በቀለ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲመደቡ፤ ፍትሐዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፤ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ፍትሕና ርትዕ እንዲያሰፍኑ መሆኑን ተገልጻል።
በአቀባበሉ ሥነ ሥርዓት የተገኙት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ፣ ቀደም ሲል ፈተና ያለፉት መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ወደ ሀገረ ስብከቱ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመደቡ በሥራና በአሠራር ስር ነቀል የሆነ ለውጥ እንዲያመጡ ተብሎ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለም፤ በቤተ ክርስቲያን አባቶች የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት፤ ብቻቸውን ሳይሆን በጋራ መሥራት ሲቻል መሆኑን በመግለጽ በክብር እንደገቡ በክብር እንዲወጡ በጸሎት አግዙኝ ብለዋል።
በአቀባበሉ መርሐ ግብር፤ ቅኔ በሊቃውንት፣ የእንኳን ደኅና መጡ እና የመልካም ሥራ ምስክርነት በሀገረ ስብከቱ እና በክፍለ ከተማው ሠራተኞች የቀረበ ሲሆን አገባባቸው ብቻ ሳይሆን አወጣጣቸውም በመልካም እንዲሆን ተመኝተዋል።
መልአከ ብርሃን መምህር ሰሎሞን በቀለ የቦሌ ገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርግስ እና ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ን በስብከተ ወንጌል ።
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ የደብረ ሰላም ቦሌ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያን እና የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተ ክርስቲያን ዋና ፀሐፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤
የቦሌ ሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እና የቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ያገለገሉ አባት ናቸው።
በቀጣይ ከሱባኤ በኋላ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና የሥራ ሐላፊዎች እንዲሁም ከሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር የሥራ ትውውቅ መርሐ ግብር እንደሚኖር በአቀባበል መርሐ ግብሩ ተጠቁሟል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ፲፬ኛ ዓመት በዓለ ዕረፍት መታሰቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፭ኛ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፲፬ኛ ዓመት በዓለ ዕረፍት መታሰቢያ በዓል እሑድ ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በጸሎት ታስቦ ይውላል።
​​ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት እና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ነበር። እነሆ ፲፬ ዓመታት ተቆጠሩ።
ቅዱስነታቸው በጥቂቱ ሲታወሱ፡-
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ወንጌልን በማስፋፋት የቤተክርስቲያንን አስተዳደር ለማጠናከርና የቤተክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማስፋት ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከውጭው ክፍለ ዓለም ጋር በመገናኘት ከኦርየንታልና ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠነክር አድርገዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ያላት ተሰሚነትና ተቀባይነት አንዲያድግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ዓለም እንድትስፋፋ ያደረጉ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ አባት ነበሩ፡፡
ቤተክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘመነ ክህነት የሀገርና የዓለም አቀፍ ይዘቷን እያጠናከረችና እያሰፋች በመጣችበት ወቅት፤የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኰሌጅ፣ የፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኰሌጅ እንዲከፈቱ አድርገዋል፤ በደርግ መንግሥት ተወርሰው የነበሩትን የቤተክርስቲያን ሕንፃዎችንና ንብረቶችን አስመልሰዋል፡፡በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲታነጽ አድርገዋል፡፡ ወደ የአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በየገዳማቱና አድባራቱ እንዲሁም በገጠር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ከቤተ መቅደሱ ክህነታዊ አገልግሎት ጀምሮ በሚሰጡት ቀኖናዊ መመሪያ፤ አባታዊ ቡራኬ፣ ቃለ ምዕዳንና ትምህርተ ወንጌል፤ካህናት በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው፤ምእመናንም በእምነታቸውና በአንድነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ሰብሳቢ ያጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት፣ በአንድነት ተሰባስበው እየተማሩ እንዲያድጉ በማድረግ፤ የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደስ፣ በተለያዩ ቦታዎች አዳዲስም አብያተ ክርስቲያናት እንዲሠሩ ማድረግ የቅዱስነታቸው የዘወትር ተግባር ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ጠንካራ ሥራ ከሀገር፣ ከአህጉርና ከወገን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የናንሰን ሜዳይ ተሸልመዋል፡፡
​​በአጠቃላይ ቅዱስነታቸው በፕትርክና ዘመናቸው የቤተክርስቲያንን ሉዓላዊነት ያስከበሩ፣ የቋንቋ ባለቤትና የባለ ምጡቅ አእምሮ ባለቤት ሲሆኑ፤ በመስቀል ደመራና በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በሚያስተምሯቸው ትምህርቶችና በሚያስተላልፏቸው ዓለማቀፋዊ መልእክቶች የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ የሳቡ ነበሩ፡፡ የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት United Nations Educational, Scientific and Cultural Organization( UNESCO) በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያደረጉና በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ሲታወሱ የሚኖሩ አባት ናቸው፡፡
በዓለ ዕረፍት
እሑድ ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም የቅዱስነታቸው ክቡር ሥጋቸው ባረፈበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ካህናት፣ ምእመናንን የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ያሳደጓቸው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው፣ በተገኙበት ከጧቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በረከታቸው ይድረሰን፡፡ አሜን!!!
@የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

14ኛ ዓመት ዕረፍት መታሰቢያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ

የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር፤ 13ኛ ዓመት ዕረፍት ነሐሴ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በመንበረ ጻባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
ልደት፣ ዕድገትና ትምህርት
ቅዱስነታቸው ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ክፍለ ሀገር በዐድዋ አውራጃ በመደራ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ አራደች ተድላ ተወለዱ፡፡ ከስድስት ዓመታት ዕድሜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የአበው መነኮሳትን ሥርዓት የተከተለ ገዳማዊ ኑሮን በአባ ገሪማ ገዳም እያጠኑ አባቶችን እያገለገሉ አደጉ፡፡
ቀጥሎም ትምህርታቸውን በበለጠ ለማስፋፋት በጭህና በአባ ሐደራ ገዳማት በመዘዋወር ከመምህር ወልደ ሐዋርያት፣ ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር፣ ከመምህር ኪዳነ ማርያም፣ ከመምህር ጳውሎስ፣ ከመምህር አምሳሉ፣ መምህር ገብረ ማርያም ከሚባሉ መምህራን ጸዋትወ ዜማን መዝገብ ቅዳሴን፣ ግዕዝ ሰዋሰውን በሚገባ ተምረዋል፡፡
ማዕረገ ክህነት
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ዲቁናን ከአቡነ ማርቆስ፣ ምንኩስናን ባደጉበት በአባ ገሪማ ገዳም ቅስናን ከአቡነ ይስሐቅ ተቀብለው ገዳማዊ አገልግሎታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡
በ1949 ዓ.ም. ገዳሙን አስፈቅደው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት በነበሩት በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፣ የሐረርጌ ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ፕሬዚዳንት በነበሩት በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በአዳሪነት ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን በመከታተል የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ በቆዩባቸው ዓመታት ይሰጥ የነበረውን ትምህርት በመከታተል ከቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሽልማትን አግኝተዋል፤ ንጉሠ ነገሥቱ ተማሪዎቹን ለመጎብኘት በመጡ ቁጥር ቅዱስነታቸውን ያነጋግሩአቸውና ያበረታቷቸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
የውጭ ሀገር ትምህርት
ቅዱስነታቸው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት እንዳጠናቀቁ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያና በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዘሐረርጌ ፈቃድ የትምሀርት ዕውቀታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሻሽሉ ወደ ውጭ ሀገር ወደ አሜሪካ ተላኩ፡፡
በአሜሪካ ሀገር በትምህርት በቆዩባቸው ዓመታትም በተለያዩ ዕውቅና ባላቸው ዩኒቨርስቲዎች፤በቅዱስ ቪላዲሚር ራሽያ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት በዲፕሎማ፤ ከየል ዩኒቨርስቲ በርክሌይ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ባችለር ኦፍ ድቪኒቲ ዲግሪ፣ ከፕሪስተን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት ማስተር ኦፍ ቲዮሎጂ፣ ከፕሪስተን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን ከፍተኛ የመጨረሻ ዶክትሬት ዶክተር ኦፍ ፊሎሶፊን አግኝተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በቋንቋ ረገድም ግዕዝ፣ትግርኛ፣አማርኛ በሚገባ ያውቃሉ፤በውጭ ሀገር ዓለም አቀፋዊ ቋንቋዎችም እንግሊዝኛ፣ጀርመንኛ፣ፈረንሳይኛ የሚናገሩ ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ ለምርምር ያህል፣ዕብራይስጥ፣ግሪክኛና ላቲን በመጠኑ ያውቁ ነበር፡፡
የምንኩስና ሕይወት አገልግሎት
ቅዱስነታቸው ከሕፃንነት ዕድሜ ጀምሮ ሥርዐተ ምንኩስናን በተቀበሉበት በመደራ አባ ገሪማ ገዳም፣በገዳሙ ቤተ ማኅበር ውስጥ እንጀራ በመጋገር፣ በአጠቃላይ ከገዳሙ አርድእት አንዱን በመሆን በተጠሩበት ሁሉ ፍጹም ታዛዥነታቸውን በማሳየት ከዐሥራ አምስት ዓመታት ያላነሰ በዲቀና፣ በምንኩስና፣ በቅስና አገልግለዋል፡፡
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ በትምህርት ገበታ ላይ በነበሩበት ጊዜም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መደበኛ ቀዳሽ በመሆን ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክና በድርሰት፣ በስብከተ ወንጌል በጋዜጣ ዝግጅትና በሬድዮ ክፍል የበላይ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የስደተኞች ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊና የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነርም ሆነው አገልግለዋል፡፡
የውጭ ሀገር አገልግሎትም ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተክርስቲያናችን ወኪል ሆነው እንዲያገለግሉ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ በታዘዙት መሠረት፤ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል፤ በአኀት አብያተ ክርስቲያናት ቋሚ ኮሚቴ፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ባይብል ሶሳይቲ፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የከተማና የኢንዱስትሪ ተልእኮ፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር እምነትና ሥርዓት ኮሚሽን፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የመካከለኛ ኮሚቴ አባል በመሆን ተመርጠው አገልግለዋል፣በተሰበሰቡት የመካከለኛ ኮሚቴ ስብሰባዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመልእክተኛነት ደረጃ አገልግለዋል፡፡
ኤጲስ ቆጶስነት
ለውጭ ሀገር አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት አገልግሎት አንድ ኤጲስ ቆጶስ መርጦ መሾም አስፈላጊ በመሆኑ፤ በግብረ ገብነታቸውና በትምህርታቸው ከታወቁት መነኰሳት መካከል አባ ገብረ መድኅን ገብረ ዮሐንስ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከሌሎች ሁለት አበው መነኰሳት ጋር መስከረም 16 ቀን 1968 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ እድ የኤጲስ ቆጶስነቱ በዐለ ሢመት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ተከብሮ ስማቸውም “ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ” ተብሎ ተሰየመ፡፡
ሐዋርያዊ አገልግሎት በእስር ቤት ቅዱስነታቸው በደርግ መንግሥት ወደ እሥር ቤት መግባታቸው ይታወቃል፤ ሁኖም በመታሠራቸው ሃይማኖታዊ ሥርዐታቸውን አላቋረጡም፤ በእስር ቤት ወንጌልን በመስበክ የብዙዎችን ሕይወት ቀይረዋል፡፡
ይልቁንም ከ500 በላይ የሚሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን በልዩ ዘዴ ተጻጽፈው ወደ እስር ቤት በማስገባት ለእስረኞቹ አድለዋል፡፡ የራሳቸውን ችግርና መከራ ሳያስቡ በእስር ቤት ያሉ ወገኖቻቸው እንዲጽናኑና መከራውን እንዲታገሡ ሲያስተምሩና ሐዋርያዊ ተልእኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተው ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ በደል ሳይፈጽሙ መታሰራቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ተሰጥቷቸው በነጻ ተለቀዋል፡፡
ሐዋርያዊ አገልግሎት በሰሜን አሜሪካ
በወታደራዊው ዘመነ መንግሥት ቅዱስነታቸው ወገኖቻቸው ተሰደው ወደሚገኙበት ሀገር ከሔዱ በኋላ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምእመናንን በማሰባሰብና በማጽናናት ትምህርተ ወንጌልን በበለጠ በማስፋፋት ሐዋርያዊውን አገልግሎት አጠናክረው ቀጠሉ፤ በዚሁ መሠረት፡- የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በኒውዮርክ፤ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዳላስ ቴክሳስ፣ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ፤የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ ፤ የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በፊኒክስ አሪዞና ፤የቅድስትሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በታምፓ ፍሎሪዳ፤የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በላስ ቬጋስ ነባዳ በሥነ ሥርዓት አቋቁመው እስከ አሁን ድረስ ምእመናን ምእመናት እየተገለገሉባቸው ይገኙሉ፡፡
ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮ በበለጠ ለማጠናከርና አምልኮተ እግዚአብሔርን ለማጽናት ሃይማኖታዊ ባህልን ጭምር ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፡- የመድኃኔ ዓለም፣የቅድስት ማርያም፣ የኪዳነ ምሕረት፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሚካኤልና የቅዱስ ገብርኤል መንፈሳውያን ማኅበራትን አቋቁመዋል፡፡
ከዚህ በላይ የተገለፀው ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በዲቁና በምንኩስና፣ በቅስና በሊቀ ጳጳስነት ሕይወት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቆይታቸው ከፈጸሟቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መካከል ጥቂቱን ክፍል ብቻ የሚያመለክት ሲሆን ቀጣዩ የታሪክ ይዘት ወደ ፓትርያርክነቱ ሥልጣን የመጡበትንና ከትልቁ ሥልጣን ባሻገር ያከናወኗቸውን ተግባራት ከዚህ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ
አምስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር ለማግኘት አፈጻጸሙ የጠየቀው መሥዋዕትነት ከባድ እንደነበር ቢታወቅም ፈተናውንና መሰናክሉን ሁሉ በማለፍ በሀገር በቀል እና በዓለም አቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውን ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ሊቀ ጳጳስ ሁሉንም አሟልተው የተገኙ በመሆናቸው ሰኔ 28 ቀን 1984 ዓ.ም. አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር እንዲመሩ ተመረጡ፡፡
የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ከሆኑበት ጊዜ አንሥቶ ወንጌልን በማስፋፋት የቤተ ክርስቲንን አስተዳደር ለማጠናከርና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማስፋት ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኰሌጅ ፣ የፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኰሌጅ እንዲከፈቱ አድርገዋል፤ በደርግ መንግሥት ተወርሰው የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎችንና ንብረቶችን እንደገና ለማስመለስ ችለዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ብዙ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን መርቀው ከፍተዋል፤ የቤተ ክርስቲያኗን የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆ ከማስፋት አኳያም በመላው ዓለም ተዘዋውረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከትን በመጎብኘት መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኦርየንታል ኦርቶዶክስ፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ እንዲሁም ከሌሎች የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠነክር ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔን ለመሻት የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች ከኤርትራ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ለሰላም ውይይት፡- በኦስሎ -ኖርዌይ፣ በጀርመን – ፍራንክፈርት፣ በአሜሪካ – ኒውዮርክ፣ በናይሮቢ – ኬንያ በተደረጉ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን የሃይማኖት መሪዎቸ ስብሰባ መርተዋል፡፡ በኒውዮርክ በተባበሩ መንግሥታት በተካሔደው የሃይማኖትና የመንፈሳዊ መሪዎች ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳትፈዋል፡፡
በዋሽንግተን አሜሪካ በኋይት ሐውስ በተካሔደው የዓለም የኤድስ ቀን ስብሰባ ተገኝተዋል፡፡ ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔርን ቃል በማሰራጨት ኤድስን ለመቋቋም ያላሰለሰ ጥረትን ማድረጋቸው ተገልፃል፡፡ የሰላምንና የስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የናንሰን ሜዳይ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኰሚሽን ተሸልመዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ዘመነ ክህነት የሀገርና የዓለም አቀፍ ይዘቷን እያጠናከረችና እያሰፋች የመጣችበት ወቅት በመሆኑ፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ስላለባት ቅዱስነታቸው ዘወትር በቢሮ ከሚያከናውነው የሥራ ፕሮግራም ባሻገር፣ ከውጭው ክፍለ ዓለም ጋር በመገናኘት ስለሀገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን፤ ስለዓለም ሰላም፣ ስለሰው ልጅ ደኅንነት፣ ዓለሙ በሚያውቀውና በሚገባው ቋንቋ በማስተማር ከአኅትና ከሌሎቹም ቀረቤታ ካላቸው፤ ከሌላቸው አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎችም የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ወደየአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በየገዳማቱና አድባራቱ እንዲሁም በገጠር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ከቤተ መቅደሱ ክህነታዊ አገልግሎት ጀምሮ በሚሰጡት ቀኖናዊ መመሪያ፤ አባታዊ ቡራኬ፣ ቃለ ምዕዳንና ትምህርተ ወንጌል፤ካህናት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸው፤ምእመናንም በእምነታቸውና በአንድነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖተ ምግባር እንዲጸና ሀገር እንዲለማ በማድረግ፣ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፤ወጣቶች ከአበው የተቀበሉትን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖቱንና ሥርዓቱን ጠብቀው በትምህርትና በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከሩና ማስፋፋቱ፤የሰው ዘር ሁሉ ከረሀብ፣ከእርዛት፣ከበሽታና ከድንቁርና ተላቆ በሰላም፣ በአንድነት በመተሳሰብና በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማድረግ ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሩን ማመቻቸት ፤ የሰበካ ጉባኤን ማጠናከር፤የቤተ ክርስቲያኒቱን የዓለም አቀፉን ግንኙነት ማጠናከሩ፤በተለያየ ምክንያት ከየሀገራቸው የወጡትን ፣ የተሰደዱትን በያሉበት መርዳቱና ማጽናናቱ ፤የተቸገረ እንዲረዳ ፣ሰብሳቢ ያጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት፣ በአንድነት ተሰባስበው እየተረዱ፤ እየተማሩ እንዲያድጉ ማድረግ፤ የፈረሰ፣ የተጎሳቆለ፣ የተጎዳ ቤተ ክርስቲያን እንዲታደስ፣ እንዲጠገን፣ አዳዲስም እንዲሠራ ማድረግ የቅዱስነታቸው የዘወትር ተግባር ነበር፡፡
ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ በመንበረ ፓትርያርክ ቅጽረ ግቢ የሚገኘውን ታሪካዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በታሪካዊነታቸው፣ በይዘታቸው፣አቻ የሌላቸው የሀገር ቅርስ እንዲጠበቅ በማድረግ፤ ትምህርት ቤቶች እንዲሰፉ፤ቅዱሳት መጻሕፍት ከየዓይነታቸው በብዛት እየታተሙ እንዲሰራጩ፤ ሐዋርያዊ ተልዕኮ እንዲፋጠን ወጣቱ ትውልድ በሃይማኖት እንዲታነጽ፣ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝባቸውን ወገኖች እንዲረዱ፣ ሰላም በሀገራችን፣ በአካባቢያችንና በዓለሙ ሁሉ እንዲሰፍን ቅዱስነታቸው ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ይህ ሁሉ ጠንካራ ሥራ ከሀገር፣ ከአህጉርና ከወገን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን አግኝቶ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የናንሰን ሜዳይ ተሸልመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሁነው እንዲሠሩ በአንድ ድምፅ በዓለሙ ኅብረተሰብ ተመርጠዋል፤ እንዲሁም ቅዱስነታቸው በኢየሩሳሌም “ቅዱስ ዮሐንስ የማልታ ክርስቲያናዊ ንቅናቄ” ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ታላቁን ባለክንፍ መስቀል ኒሻን ተሸልመዋል፡፡
የቅዱስነታቸው ዕረፍት
በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሕያው ሁኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው?” /መዝ. 88፡48/ ብሎ እንደተናገረው ቅዱስነታቸው በጾመ ፍልሰታ ለማርያም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመቀደስና ሐዋርያዊውን ተልዕኮ በመፈጸም አንደኛውን ሱባኤ ካጠናቀቁ በኋላ፤ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በዐሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሔደው በመታከም ላይ እንዳሉ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
የቅዱስነታቸው አስከሬን ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በመላ ሕዝበ ክርስቲያን ታጅቦ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ከተደረገ በኋላ በዚሁ ካቴድራል ሥርዓተ ጸሎቱ ሲፈጸም አድሮ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤የሃይማኖት መሪዎች፤ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ከውጭ ሀገር የመጡ እንግዶች፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች፤የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተጠሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ዘመድ ወዳጆቻቸው በተገኙበት ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት የቀብሩ ሥነ ሥርዐት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
የቅዱስነታቸው በረከት ይደርብን!
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሠራሯን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አጠናቃ ተግባራዊ ልታደርግ መሆኑን ተገለጸ።

​
ነሐሴ 7 ቀን 2018 ዓ.ም
​የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአሠራር ሥርዓቷን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ወደ ሆነ የዲጂታል አሠራር ለማሸጋገር የሚረዱ የመሠረተ ልማት እና የሶፍትዌር ፕሮጀክቶችን አጠናቃ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ልትሸጋገር መሆኑ ተገለጸ።
በዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀው ​ውይይት መድረክ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች እና በዘርፉ በኩል የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል።
​የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የአይሲቲ እና ዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ፣ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ የፀደቁትና አቅጣጫ የሚያሳዩት ሰነዶች በቀጥታ ወደ ተግባራዊ ሥራ የሚመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
​የአማካሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለጊዜው ተጠናቀው የተዘጋጁ የተለያዩ ሲስተሞችን በውይይት መድረኩ ላይ አቅርበዋል። እነዚህም፦
  1. ​በቤተ ክርስቲያኗ መምሪያዎችና አህጉረ ስብከት የሚካሄዱ በርካታ ድረ-ገጾችንና የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን ጠቅልሎ እንደ ዋና መግቢያ በር የሚያገለግል ዋና የመረጃ መግቢያ ድረ-ገጽ (Web Portal) ተገንብቷል። ይህ ፖርታል የቤተ ክርስቲያኗን ስያሜ፣ ማንነትና ታሪክ የሚያሳይ ሲሆን፣ በውስጡም የሰነድ ማደራጃ (Documentation)፣ የእውቀት ማኔጅመንት (Knowledge Management) እና የአርካይቭ ሥርዓቶችን ያካተተ ነው።
  2. የሰበካ ጉባኤ ምዕመናን መመዝገቢያ የዲጂታል ሥርዓት ሲሆን የምዕመናን፣ የጥምቀት፣ የጋብቻ እና የዕረፍተ ሥጋ (ሞት) መረጃዎች በማዕከል ደረጃ የሚመዘገቡበት ሥርዓት ነው። መረጃው በአድባራቱ ደረጃ የሚመዘገብ ቢሆንም፣ አደረጃጀቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በአህጉረ ስብከት፣ በወረዳና በክፍለ ከተማ እስከ ደብር ድረስ ወርዶ የበላይ ኃላፊዎችና አባቶች ሙሉ መረጃውን በቀላሉ ማየትና መከታተል የሚያስችላቸው ነው።
  3. የሰው ኃይል አስተዳደር ሥርዓት (HR System) ሲሆን በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር በሁሉም ደረጃ የሚገኙ አገልጋዮችና ሠራተኞች የሚመዘገቡበት ነው። ጊዜና ቦታ ሳይገድበው ባለሙያዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት አማካይነት መረጃዎችን ማስገባትና በአንድ ማዕከል ማየት የሚያስችልም ነው ብለዋል።
​በተጨማሪም የሀብት አስተዳደር የኢአርፒ (ERP) ሲስተሞች፣ የዲጂታል ላይብረሪ እና የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የዲጂታል ሽግግሩ ዋና መርሕ ቴክኖሎጂን ለመግዛት ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ተልዕኮን ለማሳካትና አሠራርን ለማዘመን እንደሆነ ተጠቅሷል።
​ቀሲስ ዮሐንስ አክለውም ሥራው ቢጀመርም ወደ ዲጂታሉ ዓለም ለመውሰድ የታቀዱ በርካታ ተግባራት የሚቀሩ በመሆኑ፣ በዘርፉ ዕውቀቱና አቅሙ ያላቸው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ባሉበት ሆነው የቴክኖሎጂ ዕድገቷን እንዲደግፉና አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።
​በመድረኩ የመምሪያ ኃላፊዎች ለዘርፉ ባለሙያዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ተግባር የቤተ ክርስቲያኗን ጥንታዊነትና ልዕልና ለዓለም የሚያስተዋውቅ፣ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚያጎለብትና ገጽታዋን የሚቀይር በመሆኑ በፍጥነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ደብር መዋቅሩ ተዘርግቶ መሬት ላይ ወርዶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
​እንዲሁም ሥራውን ወደ ተግባር ለማውረድ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ትብብርና ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
​የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሼል አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከልማት ሥራዎች ሁሉ በላይ ሆኖ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አፅንዖት በመስጠት ተናግረዋል። “ቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ናት፤ አሁን ላይ ከቴክኖሎጂ አንጻር ወደ ኋላ ቀርተናል” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም፣ የቤተ ክርስቲያኗን ክብርና ልዕልና ጠብቆ ከዓለም እና ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ማቀራረብና አብሮ መፍጠን እንደሚገባ ገልጸዋል።
​ቤተ ክርስቲያን የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የሚመራ ክፍል በመምሪያ ደረጃ አዋቅራ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ መዋቅሩ እንዲዘረጋ መመሪያ የወረደ መሆኑ ተገልጿል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/