የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ፲፬ኛ ዓመት በዓለ ዕረፍት መታሰቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፭ኛ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፲፬ኛ ዓመት በዓለ ዕረፍት መታሰቢያ በዓል እሑድ ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በጸሎት ታስቦ ይውላል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት እና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ነበር። እነሆ ፲፬ ዓመታት ተቆጠሩ።
ቅዱስነታቸው በጥቂቱ ሲታወሱ፡-
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ወንጌልን በማስፋፋት የቤተክርስቲያንን አስተዳደር ለማጠናከርና የቤተክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማስፋት ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከውጭው ክፍለ ዓለም ጋር በመገናኘት ከኦርየንታልና ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠነክር አድርገዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ያላት ተሰሚነትና ተቀባይነት አንዲያድግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ዓለም እንድትስፋፋ ያደረጉ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ አባት ነበሩ፡፡
ቤተክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘመነ ክህነት የሀገርና የዓለም አቀፍ ይዘቷን እያጠናከረችና እያሰፋች በመጣችበት ወቅት፤የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኰሌጅ፣ የፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኰሌጅ እንዲከፈቱ አድርገዋል፤ በደርግ መንግሥት ተወርሰው የነበሩትን የቤተክርስቲያን ሕንፃዎችንና ንብረቶችን አስመልሰዋል፡፡በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲታነጽ አድርገዋል፡፡ ወደ የአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በየገዳማቱና አድባራቱ እንዲሁም በገጠር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ከቤተ መቅደሱ ክህነታዊ አገልግሎት ጀምሮ በሚሰጡት ቀኖናዊ መመሪያ፤ አባታዊ ቡራኬ፣ ቃለ ምዕዳንና ትምህርተ ወንጌል፤ካህናት በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው፤ምእመናንም በእምነታቸውና በአንድነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ሰብሳቢ ያጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት፣ በአንድነት ተሰባስበው እየተማሩ እንዲያድጉ በማድረግ፤ የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደስ፣ በተለያዩ ቦታዎች አዳዲስም አብያተ ክርስቲያናት እንዲሠሩ ማድረግ የቅዱስነታቸው የዘወትር ተግባር ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ጠንካራ ሥራ ከሀገር፣ ከአህጉርና ከወገን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የናንሰን ሜዳይ ተሸልመዋል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስነታቸው በፕትርክና ዘመናቸው የቤተክርስቲያንን ሉዓላዊነት ያስከበሩ፣ የቋንቋ ባለቤትና የባለ ምጡቅ አእምሮ ባለቤት ሲሆኑ፤ በመስቀል ደመራና በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በሚያስተምሯቸው ትምህርቶችና በሚያስተላልፏቸው ዓለማቀፋዊ መልእክቶች የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ የሳቡ ነበሩ፡፡ የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት United Nations Educational, Scientific and Cultural Organization( UNESCO) በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያደረጉና በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ሲታወሱ የሚኖሩ አባት ናቸው፡፡
በዓለ ዕረፍት
እሑድ ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም የቅዱስነታቸው ክቡር ሥጋቸው ባረፈበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ካህናት፣ ምእመናንን የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ያሳደጓቸው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው፣ በተገኙበት ከጧቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በረከታቸው ይድረሰን፡፡ አሜን!!!
@የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/