የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዕድሳት የደረሰበትን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለብፁዓን አባቶች መግለጫ ቀረበ
ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም
የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዕድሳት አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘኣክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮሰ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አሀጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱሰ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የራያ ሀገረ ስበከት ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮሰ የቴክሳስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን የሚሳለሙት ታሪካዊው የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ የሕንጻውን ጥንታዊነት ለመጠበቅና ምዕመናን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሰፊ የዕድሳት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል ።
መገለጫዉን ያቀረቡት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮሰ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ የዚህ ታላቅ የዕድሳት ፕሮጀክት ዓላማ በጊዜ ብዛትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በቤተክርስቲያኑ ጣሪያ፣ ግድግዳ እና ውጫዊ አካላት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን መጠገን እና የቤተክርስቲያኑን ጥንታዊ የኪነ-ሕንጻ ጥበብና ታሪካዊ ይዘት ሳይለቅ በባለሙያዎች የታገዘ ጥገና ማካሄድ እንደሆነ ባቀረቡት ማብራሪያ ገልጸዋል ።
ብፁዕነታቸው ዕድሳቱ በብዙ ምዕራፎች የተከፈለ መሆኑን ገልጸው ጥናትና የዲዛይን ሥራዎችን ማጠናቀቅ ፣ የቤተክርስቲያኑን ዋና አካል (መቅደስና ቅኔ ማኅሌት) የመጠገን ሥራ ፣ የአጸዱንና በዙሪያው ያሉ አገልግሎት መስጫዎችን የማዘመን ሥራን ያካትታል ብለዋል ።
ብፁዕነታቸው ይህ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት ሥፍራ ብቻ ሳይሆን የሀገር ቅርስ ቢሆንም ፤ ላለፉት 64 ዓመታት ዕድሳት ሳይደረግበት የቆየው ሕንጻ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ዕድሳቱ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ለዕድሳቱ የሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ ከ134 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያሰፈልግም ተጠቁሟል ።
ለዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ስኬት ምዕመናን በጸሎት፣ በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በገዳሙ ስም በተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች አማካኝነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥሪ አቅርበዋል።©EOTCTV