ለፉት አራት ቀናት በኬንያ ንይሮቢ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሰነበቱት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል

ሚያዝያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
በኬንያ ናይሮቢ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲያከናውኑ የሰነበቱ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዛሬ አመሻሹ ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ሁለቱ ብፁዓን አባቶች ሚያዚያ 9ቀን 2018 ዓ.ም ናይሮቢ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የናይሮቢ ደብረ መድኀኒት መድኅኔዓለም ቤተክርስቲያን ካህናት፣ምዕመናንና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በናይሮቢ ደብረ መድሃኒት መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያንም የአቀባበል መርሐ ግብር የተደረገላቸው መሆኑ ይታወሳል።
ብፁዓን አባቶቹ በናይሮቢ ደብረ መድሃኒት መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሜና እሑድን በቅዳሴና በስብከተወንጌል አገልግሎት ሕዝበ ክርስቲያኑን ሲያገለግሉ መቆየታቸውና
ሚያዚያ 10ቀን2018ዓ.ም በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉብኝት ማድረጋቸውም በወቅቱ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
በኬንያ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉብኝት ወቅት የሚሲዮኑ ዲፕሎማቶች እና ሠራተኞች ደማቅ አቀባባል ያደረጉላቸው ሲሆን፣ የሚሲዮኑ ምክትል መሪ ክቡር አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ለብፁዓን አባቶች ስለኤምባሲው አመሰራረት እንዲሁም በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው መልካም ግንኙነት እና ትብብር ገለጻ እንዳደረጉላቸው በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።
ሁለቱ ብፁዓን አባቶች በናይሮቢ ኬንያ የነበራቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናቀው ዛሬ መምሻውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።