ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የቢሮ ዕድሳት ሥራ ያለበትን ደረጃ ተመለከቱ
መጋቢት 20ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሚያከናውነውን የቢሮ ዕድሳት ሥራ አፈጻጸምን ከጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ዛሬ ረፋዱ ላይ ተዘዋውረው ተመለከቱ።
ብፅዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ድርጁቱ የሚያከናውነው የቢሮ ዕድሳት ሥራ የደንበኛችን ምቹ አገልግሎት የማግኘት ዕድልን የሚያሰፋውንና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክትና በሰጡት የሥራ መሠሪያ ገልጸዋል። አያይዘውም የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት አሰራሩን ለማዘመንና ተደራሽነቱን በማስፋት አሰራሩን ከደንበኛ ተኮር የአገልግሎት ዐይነት ጋር በማቀናጀት ለመፈጸም የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ይህንን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም ከቤተክርስቲያን ምንም አይነት ወጪ ሳይጠይቅ በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር ቢሮውን በዘመናዊ መልኩ ማደስና ማደራጀት መጀመሩ የሚደነቅና የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል።
ድርጅቱ በፍጥነት በመለወጥና በማደግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ይህንን በመምራትና በማስተባበር በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት የድሮጅቱ ዋና ሦራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ ምስጋናና አድናቆት ይገባቸዋል። ካሉ በኋላ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የቢሮ ዕድሳት ሥራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ከእድሳት ሥራ አፈጻጸሙ መቀላጠፍ የተረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዜና ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች በአካባቢው የተጋረጠውን የእሳት አደጋ የመፈጠርን ዕድል ተከትሎ በአስቸኳይ እንዲነሱ
የሚደረጉ ነዋሪዎች በጊዜየያዊነት የሚያርፉበት ቦታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት አማካኝነት በልደታ አካባቢ እየተሰራ መሆኑን ተከትሎ የጊዜያዊ ማረፊያ ቤት የግንባታ ሂደትን በትላንትናው ዕለት የተመለከቱ ሲሆን ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰለ ማረፊያ ቤት በመስራት ዝግጁ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።
በመጨረሻም የተጀመረውን የጊዚያዊ ማረፊያ ቤቶችን ግንባታ
በአስቸኳይና በጥራት በማጠናቀቅ ነዋረመዎችን የማዘዋወሩን ሥራ በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ ገልጸው ነዋሪዎቹ በሚያርፉበት ቦታ ላይ መብራት፣ውኃ፣መጸዳጃና ማብሰያ ቦታውች በአስቸኳይ ተሟልተው እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተዋል።በአሁኑ ጊዜ በልደታ አካባቢ የሚከናወነው የግንባታ ሥራ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ሲሆን በሦስት ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አልቆ ነዋሪዎችን የማዘዋወሩ ሥራ እንደሚጀመርና በፒያሳ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቶቹ ተሰርተው ነዋሪዎችን የማዘዋወሩ ሥራ እንደሚከናወን የድርጅቱ የዕቅድና ልማት ክፍል ኃላፊ መምህር ታዲዮስ ሽፈራሁ ገልጸዋል።