የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት የውል እድሳት አገልግሎትን በዘመናዊና ቀልጣፋ ሲስተም መስጠት ጀመረ።

ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም |የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት፣ ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል አሠራርና የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት በመዘርጋት የ፳፻፲፱ ዓ.ም. የደንበኞች ውል እድሳትን በታላቅ እመርታ መጀመሩን ይፋ አደረገ። ድርጅቱ የሚያስተዳድራቸውን የንግድ እና የመኖሪያ ቤት ተከራይ ደንበኞቹን የውል እድሳት አገልግሎት ከሐምሌ ፩ ቀን ጀምሮ በይፋ መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ ሂደቱ እስከ ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል።
ድርጅቱ ተገልጋዮችን ማዕከል ያደረገ ሥር ነቀል የአሠራርና የቴክኖሎጂ ሽግግር (Digital Transformation) በማድረጉ ምክንያት፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል። ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር በተንዛዙ ሂደቶች የተሞላ በመሆኑ፣ ደንበኞች የኪራይ ውል ለማደስ ብቻ በትንሹ ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት (ከ15 እስከ 30 ቀናት) የሚወስድባቸው ከመሆኑም በላይ ለተደጋጋሚ መጉላላትና እንግልት ይዳረጉ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ቢሮክራሲ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ዘመናዊ የዲጂታል ሲስተም በመዘርጋቱ፣ ባለጉዳዮች የሚጠበቁባቸውን መሠረታዊ ሰነዶች ብቻ አሟልተው ሲገኙ፣ ምንም ዓይነት ወረፋና መደርደር ሳይኖርባቸው ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ባለው እጅግ አጭር ጊዜ ውስጥ ውላቸው ተሻሽሎ፣ ታትሞና ተፈርሞላቸዉ በታላቅ አክብሮት እንዲሸኙ እየተደረገ ይገኛል።
ይህንን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግም፣ ተቋማዊ አሠራሩ ከባንክ የክፍያ ሥርዓት ጋር በቀጥታ እንዲተሳሰር ተደርጓል። ይህም በመሆኑ ምክንያት ደንበኞች ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው ገንዘብ ለመክፈልና ደረሰኝ ለማስመታት ወደ ድርጅቱ መምጣትና በየቢሮው መንከራተት ሳይኖርባቸው፣ ባሉበት ሆነው በባንክ አማካኝነት ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ተደርጓል። ይህ ቴክኖሎጂን ያቀናጀ አሠራር የምዕመናንንና የደንበኞችን ውድ ጊዜና ጉልበት በከፍተኛ ደረጃ ከመቆጠቡም በላይ፣ ተቋሙ ለተገልጋዮቹ የሰጠውን የላቀ የክብር ደረጃ የሚያሳይ ሕያው ማረጋገጫ ሆኗል።
ቀደም ሲል በተቋሙ ውስጥ የተደራጀ የእንግዳ መቀበያና መረጃ ሰጪ (Reception) ክፍል ባለመኖሩ ምክንያት፣ ባለጉዳዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት በየትኛው ቢሮና በየትኛው የሥራ ክፍል እንደሚያገኙ ግልጽ መረጃ ባለማግኘት ለከፍተኛ መጉላላትና ግራ መጋባት ይዳረጉ ነበር። ይህንን ክፍተት በዘላቂነት ለመቅረፍ ተቋሙ ባደረገው አዲስ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ የእንግዳ መቀበያ ማዕከል ያቋቋመ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ተገልጋዮች ገና ወደ ሕንፃው መግቢያ ሲደርሱ በሰለጠኑ ባለሙያዎች በታላቅ አክብሮትና ቀናነት አቀባበል ይደረግላቸዋል።
ማዕከሉ ወደ ቢሮው ለሚመጡ እንግዶች በሙሉ ወዴት መሄድ እንዳለባቸውና ምን ምን ሰነዶችን ማቅረብ እንደሚገባቸው ፈጣን ኦረንቴሽንና ግልጽ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን እጅግ ያቀላጠፈውና ተንዛዛውን አሠራር ያስቀረ ሆኗል። ይህንን ሥር ነቀል የባህልና የሥራ አካባቢ ለውጥ (Organizational Culture Shift) ተከትሎ፣ በተቋሙ ተገኝተው የተስተናገዱ ደንበኞች በሙሉ ካለፈው ዓመታት መጉላላት በመላቀቃቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታና የላቀ የዕርካታ (Customer Satisfaction) አስተያየታቸውን በከፍተኛ አድናቆት እየገለጹ ይገኛሉ።
በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የተቋሙ የመኖሪያ ቤት ተከራይ የሆኑት አቶ አውላቸው አሰፋ ሲናገሩ፦ “ከዚህ በፊት ከ6 እስከ 7 ጊዜ በላይ ውል ሞልቼ አውቃለሁ፤ በዚህ ፍጥነት ግን ተስተናግጄ አላቅም። ዛሬ በመጣሁ በ10 ደቂቃ ውስጥ ብቻ ሁሉንም ነገር ጨርሼ ወጥቻለሁ። የቢሮው ሁኔታ በጣም የሚገርም ነው፤ ከበር ጀምሮ ያለው የእንግዳ አቀባበል የተለየና ቢሮው እጅግ ዘመናዊ ሆኖ የታደሰ ነው። አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ከመጡ በኋላ በፊት በአእምሯችን ላይ የነበረውን መጥፎ አሠራር የሚያስቀር ትልቅ ለውጥ እያየን ነው” ብለዋል።
ሌላኛው የተቋሙ ደንበኛ መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ በበኩላቸው ድርጅቱ የሚገኝበት የ4 ኪሎ አካባቢ የከተማዋ እንብርት መሆኑን ጠቅሰው፦ “ቢሮዎቹ የአካባቢውን ስታንዳርድ በጠበቀ መልኩ ታድሰውና ዘመናዊ በሆነ አሠራር ደንበኛን እያስተናገዱ ይገኛሉ። እኔ ዛሬ ውል ለመውሰድ መጥቼ በ30 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የታደሰውን ውል ተቀብያለሁ። ይህ ዘመኑን የዋጀና በቤተ ክርስቲያናችን ልማት ላይ እንደ ማሳያ የሚወሰድ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት ስለሆነ እጅግ ደስ ብሎኛል፤ ለዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ስዩማን እስክንድርና ለሥራ ባልደረቦቻቸው መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በተቋሙ ቀደም ሲል ያገለግሉ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ደንበኛ የሆኑት መልአከ ሕይወት ቀለመወርቅ በበኩላቸው በተደረገው ለውጥ መደመማቸውን ገልጸው፦ “አመታዊ የኪራይ ውል አሰጣጡ በአጭር ደቂቃ ውስጥ መጠናቀቁ ደንበኞች ይማረሩበት የነበረውን ማንዛዛት አስቀርቷል። ጥያቄ ስንጠይቅ ወዲያውኑ መፍትሔ ማግኘታችን በተቋሙ ውስጥ ያለውን የተለየ ለውጥ ያሳያል። ሌላው ትልቁ ስኬት የሕንፃው እድሳት ከድርጅቱ ወጪ ሳይወጣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከናወኑ ነው። ሠራተኛው በጥሩ መሪ ሥር ተናቦ እየሠራ ነው፤ ሥራ አስኪያጁን ስንጠይቅ ሥራን ለነገ አያሳድሩም፤ በዚህም ሥራ አስኪያጁንና ሠራተኞቹን በሙሉ አደንቃለሁ” ብለዋል።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት በአሁኑ ወቅት እያሳየ ያለው ሥር ነቀል የአሠራር ለውጥ፤ ተቋሙ ካለበት አሮጌና የተንዛዛ ቢሮክራሲ ወጥቶ ወደ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ዲጂታላይዝድ ወደሆነ አሠራር መሸጋገሩን በተግባር ያሳየበት ሆኗል። ከአራት ሳምንታት እንግልት ወደ 20 ደቂቃዎች መስተንግዶ የተደረገው የጊዜ ቅነሳ፣ ደረጃውን የጠበቀ የእንግዳ መቀበያ (Reception) ማቋቋም መቻሉ እና ከባንክ የክፍያ ሥርዓት ጋር የተገነባው ትስስር ተቋሙ ለደንበኞቹ የሰጠውን የላቀ የክብር ደረጃ የሚያረጋግጡ አበይት ማሳያዎች ናቸው።
ይህ በድርጅቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው ደንበኛ ተኮር አገልግሎትና የቢሮዎች መታደስ፤ በአዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ መሪነትና በሥራ ባልደረቦቻቸው ቁርጠኝነት የመጣ መሆኑን ተገልጋዮች በታላቅ ዕርካታ መስክረዋል። ለውጡ ከድርጅቱ ካፒታል ላይ ምንም ዓይነት ወጪ ሳይደረግ፣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር የተከናወነ መሆኑ ደግሞ የአመራሩን ስልታዊና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሥራ መሪነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል።
የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት ይህንን የተጀመረውን የልማት፣ የማዘመንና የቀናነት ጉዞ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ያረጋገጠ ሲሆን፤ ይህ ስኬታማ ተሞክሮ በሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ ተቋማትና መዋቅሮች ዘንድ እንደ መልካም ተሞክሮ (Best Practice) የሚወሰድና የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት ይበልጥ የሚያፋጥን መሆኑ ታምኖበታል።

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት የምስክር ጉባኤ ቤት 19 ደቀመዛሙርትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስመረቀ።

ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
ባሕርዳር-ኢትዮጵያ
በምርቃት መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስካንዲቪያንስ እና የግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስክር ጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ሓላፊዎች ፣ የምስክር ጉባኤ ቤቶች መምህራን ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ተመራቂዎችና የተመራቂ ደቀመዛሙርት ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ጥሪ የተረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመርሐ ግብሩ ላይ ለተመራቂ ደቀመዛሙርት እና ለቤተክርስቲያን የእንኳን ደስ ያለን መልእክታቸው አስተላልፈው “የዛሬ ተመራቂ ደቀመዛሙርት የነገ መምህራን የቅድስት ቤተክርስቲያን ሉዓላዊነትነት ተከብሮ እንዲዘልቅ ፣ ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ የቅዱስ ሲኖዶስ የተዘረጋው የቤተክርስቲያን ሰንሰለት ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ለሐዋርያዊ አገልግሎት በምትጓዙበት ሁሉ በርትታችሁ ልትሠሩ ይገባል” ብለዋል።
የብፁዕነታቸው አክለውም “በማያስፈልገው መልኩ የጥንቱን እውቀታችሁን አታዘምኑት” የአባቶቻችን ትርጓሜም ወደ ቀጣይ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ ተግታችሁ ሥሩ ፣ ከእውቀት ባሻገር ለመንፈሳዊነትም ልዩ ትኩረት እንድትሰጡ ደግሞም የምታስተምሩትን በተግባር መኖር ከተመራቂ ደቀመዛሙርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በበኩላቸው ተመራቂ ደቀመዛሙርት ለፍሬ እንዲበቁ ምኞታቸውን በመግለፅ ሊቃውንት በዚህ መልኩ መመረቃቸው ጥንት ያልነበረ አሁን ግን የተለመደ ታላቅ ተግባር ነውና “ትልቅ ዕድል” ነው ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ብፁዕነታቸው የብፁዕ አቡነ አብርሃምን መልእክት በሚያጠናክር መልኩ “ሊቃውንቱ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት ፣ ከቀድሞው በበለጠ በጋራ ሊቆሙ ፣ አንድ ድምፅ ሁነውም ሊመክሩ ፣ ምክረ ሐሳባቸውንም ለቅዱስ ሲኖዶስ በትጋት ሊያቀርቡ” እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተመራቂ ደቀመዛሙርት መምህር የሆኑት ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ ደግሞ ተማሪዎቻቸው ለዚህ ደረጃ በመብቃታቸው መደስታቸውን ገልጸው በቀጣይም በምስክር ጉባኤ ቤቱ በነበራቸው ቆይታ የቀሰሙትን ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዕውቀት ተግባር ላይ በማዋል ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅም አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ከዚህ በመለስ የምስክር ጉባኤ ቤቱ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በዛሬው የደቀመዛሙርት የምርቃት በዓል ላይ ለመምህራን ማረፊያ እንዲሁም ወደ ምስክር ጉባኤ ቤቱ ለሚመጡ እንግዶች መቀበያ የሚሆን ሕንጻ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ይህ አዲስ ሕንጻ የጉባኤ ቤቱን የትምህርት ሥርዓት ለማጠናከር፣ ለተማሪዎችም የተሻለ የአስተዳደርና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።©ፈለገ ገነት ሚዲያ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ለሁለተኛ ዙር አስመረቀ።

ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም
‎ሀዋሳ-ኢትዮጵያ
‎በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የምዕራብ ሽዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣መጋቤ ጥበባት አባ ዘሚካኤል የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ተመራቂ ደቀ መዛሙርትና የተመራቂ ደቀ መዛሙርት ቤተ ሰቦች ተገኝተዋል።
‎በእለቱ ለብፁዓን አባቶችና ለእንግዶች የእንኳን ደና መጣችሁና ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት ‎ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ‎”ወናሁ አነ እፌንዎክሙ ከመ አባግዕ ማዕከለ ተኩላት” / ማቴ 10፥16 /
‎ ያለውን በማንሳት ሰፊ መልእከት አስተለላፈዋል።
‎በመቀጠል በኮሌጁ ዲን በመጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ነጻነት አክለወግ ሪፖርት ቀርቧል። ‎በሪፖርታቸው የምናቀርበው የታማሪዎችን ውጤት ብቻ ሳይሆን የአባቶቻችን የሊቃነ ጳጳሳት የወደ ፊት ራዕይና የአመራር ብቃት፣የመምህራን ጥረት ነው።
‎ ዛሬ ለሁለተኛ ዙር እያስመረቀ ያለው ኮሌጅ ለረዥም ጊዜ በካህናት ማስለጠኛነት የቆየ ሲሆን በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ከፍተኛ ጥረትና በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በ2015 ዓ/ም ሥራውን የጀመረ ሲሆን ዛሬ በመደበኛው ለሁለተኛ ዙር 12 ፣ በማታ ለመጀመሪያ ጊዜ 20 ፣በቅዳሜና እሑድ ለመጀመሪያ ጊዜ 45 በድምሩ 77 ከእነዚህ መካከል ስድስት ሴቶች ይገኙበታል።
‎ይህ የሚያሳየው ለመደበኛ ደቀ መዛሙርት የሚሰጠው ትምህርት እንዳለ ሆኖ በማታና በእረፍት ቀናት ከቤተሰብ ሳይለዩ የሚማሩበት እድል መፈጠሩን ማሳያ ነው ብለዋል።
‎በመቀጠል ለሁሉም ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ባይንደር በብፁዓን አባቶች ተሰጥቶ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ደቀ መዛሙርት ሽልማት ከተሰጠ በኋላ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሊቀ ጳጳስ “መከሩ ብዙ ነው ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው” /ማቴ 9፥37/ ዛሬ የተመራቃችሁ ደቀ መዛሙርት ዛሬም መከሩ ብዙ ሠራተኛች ጥቂት በመሆናቸው ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ጉልበት ናችሁ። ዓለምን ያጣፈጡት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሦስት ዓመት ከክርስቶስ ሥር ቁጭ ብለው ተመረው በጆሯቸው የሰሙትን በዓይናቸው ያዩትን መስክረዋል።
‎ ዛሬም እናንተ በቆያችሁባቸው ሦስት ዓመታት በጆሯችሁ የሰማችሁትን በዓይናችሁ ያያችሁትን እንድትመሠክሩ ነው።
‎ ዛሬ እንደ እናንተ በዓላማዊ የሚመረቁ አሉ ለምን ሥጋዊውን ዓለም ለማገልገል ነው እናንተ ደግሞ በዓለማዊው ዓለም ለመንፈሳዊው ዓለም እንድታገለግሉ ነው።
‎ስለዚህ አሁንም ክርስቶስ በዚያን ጊዜ እንደተናገረው በዓለም ካለው ሕዝብ አንጻር የሠራተኛው ቁጥር ጥቂት ነው።
‎በአጠቃላይ የእናንተ ጥሪ ለሹመት ለሽልማት ባለመሆኑ የተጣለባችሁን እንድትወጡ አደራ ብለዋል።
‎በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጸሎትና ቡራኬ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል።
© ኢዮር ሚዲያ ሲዳማ ሀገረ ስብከት

ላይፍ አዲስ ሆስፒታል ከቤተክርስቲያን ተከራይቶ በዘመናዊ መንገድ የሚያሳድሰውን ሆስፒታል በብፁዓን አባቶች አስጎበኘ።

ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የላይፍ አዲስ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት
የተከራየውን ሕንጻና የሕክምና ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማዘመንና ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ወደሚያሟላ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር የጀመረውን ሰፊ የእድሳትና የማስፋፊያ ሥራ አሁናዊ አፈጻጸም ለመገምገም የሚያስችል የሱፐርቪዥን ጉብኝት ተካሂዷል።
በዚህ መርሐ-ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሸገር ከተማና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ የሐድያና ስልጤ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቀ ሥዩማን እስክንድ ገብረ ክርስቶስ የቤቶችና ሕንጻዎች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ኀላፊ የመንበረ ፓትርያርክ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የሆስፒታሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰፊ ምልከታ ተደርጓል።
የላይፍ አዲስ ሆስፒታል ከተከራየው የቤተክርስቲያኗ ይዞታ ላይ የመሠረተ-ልማት አደረጃጀቱን ለመለወጥና ተቋሙን በዘመናዊ መልክ ለመቅረጽ እያከናወነ ያለው አጠቃላይ የእድሳት እንቅስቃሴ አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተመልክቷል። በተደረገው ምልከታ፣ ብፁዓን አባቶችና የሥራ ኃላፊዎቹ አጠቃላይ የሆስፒታሉን የውስጥ ክፍሎች ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፣ ክፍሎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው ሙሉ የላቦራቶሪና የሕክምና አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት መልኩ ሰፊ የብርሃንና የቦታ አጠቃቀምን ታሳቢ አድርገው እየተገነቡ መሆኑ በማብራሪያው ላይ ተገልጿል።
በተጨማሪም ሆስፒታሉ ለብፁዓን አባቶችና ለክቡራን እንግዶች የሚመጥን ልዩ የቪአይፒ (VIP) የእንግዳ መቀበያና ማረፊያ ቦታዎችንም ጭምር ያካተተ ዘመናዊ አደረጃጀት ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
በመቀጠልም በሆስፒታሉ ውስጥ ለተለያዩ የሕክምና ዘርፎችና ለታካሚዎች ማቆያነት የተዘጋጁትን የውስጥ መተላለፊያ ኮሪደሮች፣ የሕክምና መስጫዎችና የክፍል አደረጃጀቶች በዝርዝር ተጎብኝቷል ። ይህ ሰፊ የእድሳት ሥራ ሆስፒታሉ ከቤተክርስቲያን በተከራየው በዚህ ተቋም ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን የሕክምና ጥራት፣ ደኅንነትና ምቾት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ተመላክቷል።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ብፁዓን አባቶች ሆስፒታሉ የቤተክርስቲያንን ንብረት ይዞታ ይበልጥ በሚያሳምርና የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ በተሟላ መልኩ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እያከናወነ ያለውን ይህንን ዘመናዊ የልማትና የእድሳት እንቅስቃሴ በላቀ ሁኔታ አድንቀዋል።

የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ትርጓሜ ምስክር ት/ቤት በባሕር ዳር ከተማ ለሚያስገነባው “የሕክምና መንደር” የመሠረት ድንጋይ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተቀመጠ።

ሰኔ ፲፱ቀን ፳፲፰ ዓ.ም
የገዳሙ ጉባኤ ቤት “ሰንፔር” ሲል ለሰየመው “የሕክምና መንደር” ግንባታ 30,000 ካሬ ቦታ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሰኔ ፲፱ቀን ፳፲፰ ዓ.ም መረከቡም ይታወቃል።
“የሕክምና መንደሩ” የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐ ግብር ላይ እንደተገለፀው የሕክምና መንደሩ ዋና ዓላማ ለሁሉም የሰው ልጆች በምሕረት፡ እምነትን፣ ዘርንና ማንነትን ሳይለይ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚታዘንበት የምሕረት ማረፊያ እንዲሆንና ሁለንተናዊ ፈውስ ለመስጠት ነው ተብሏል።
ከዚህ በመለስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራችን የነበራትን የጥበብ ታሪክ በዘመናዊ የምርምር ዐቅም ለማስቀጠል “የሕክምና መንደሩ” ከፍ ያለ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ሌላው ቤተ ጉባኤው “የሕክምና መንደር” የሚያስገነባው የቅድመ ጋብቻ ትምህርት ለመስጠት የባለትዳሮች ደግሞ የልጅ አስተዳደግ ሥልጠና ለመስጠት እንዲሁም በሱስ የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመንከባከብና እንደገና አዲስ ሰውነት እንዲያገኙ በማድረግ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገራችን በጎና ባለ አእምሮ ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን ቆሞስ አባ ገብረ ኪዳን ግርማ የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአባቶች እና የእናቶች አንድነት ገዳም የ ፬ቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ምስክር መምህር ተናግረዋል።
ቆሞስ አባ ገብረ ኪዳን አክለውም “የሕክምና መንደሩ” ሀገር በቀል የሕክምና ማዕከል እንዲሁም የሕክምና ኮሌጅና የምርምር ማዕከል ያካተተ ይሆናልም ብለዋል።
የሕክምና መንደሩ ወደ መሬት እንዲወርድ ለተባበሩት ሁሉ ቆሞስ አባ ገብረ ኪዳን ግርማ “የጉባኤ አምላክ ይጠብቅልን” ሲሉ አመስግነዋል።
“የሕክምና መንደሩ” መሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስካንዲቪያን እና የኖርዲክ አገራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ሓላፊዎች ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ካህናት አባቶች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሥራ ሓላፊዎች ተገኝተዋል።የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ትርጓሜ ምስክር ት/ቤት በባሕር ዳር ከተማ ለሚያስገነባ “የሕክምና መንደር” የመሰረት ድንጋይ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተቀመጠ።
የገዳሙ ጉባኤ ቤት “ሰንፔር” ሲል ለሰየመው “የሕክምና መንደር” ግንባታ 30,000 ካሬ ቦታ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሰኔ ፲፱-፳፲፰ ዓ.ም መረከቡም ይታወቃል።
“የሕክምና መንደሩ” የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐ ግብር ላይ እንደተገለፀው የሕክምና መንደሩ ዋና ዓላማ ለሁሉም የሰው ልጆች በምሕረት፡ እምነትን፣ ዘርንና ማንነትን ሳይለይ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚታዘንበት የምሕረት ማረፊያ እንዲሆንና ሁለንተናዊ ፈውስ ለመስጠት ነው ተብሏል።
ከዚህ በመለስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራችን የነበራትን የጥበብ ታሪክ በዘመናዊ የምርምር ዐቅም ለማስቀጠል “የሕክምና መንደሩ” ከፍ ያለ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ሌላው ቤተ ጉባኤው “የሕክምና መንደር” የሚያስገነባው የቅድመ ጋብቻ ትምህርት ለመስጠት የባለትዳሮች ደግሞ የልጅ አስተዳደግ ሥልጠና ለመስጠት እንዲሁም በሱስ የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመንከባከብና እንደገና አዲስ ሰውነት እንዲያገኙ በማድረግ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገራችን በጎና ባለ አእምሮ ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን ቆሞስ አባ ገብረ ኪዳን ግርማ የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአባቶች እና የእናቶች አንድነት ገዳም የ ፬ቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ምስክር መምህር ተናግረዋል።
ቆሞስ አባ ገብረ ኪዳን አክለውም “የሕክምና መንደሩ” ሀገር በቀል የሕክምና ማዕከል እንዲሁም የሕክምና ኮሌጅና የምርምር ማዕከል ያካተተ ይሆናልም ብለዋል።
የሕክምና መንደሩ ወደ መሬት እንዲወርድ ለተባበሩት ሁሉ ቆሞስ አባ ገብረ ኪዳን ግርማ “የጉባኤ አምላክ ይጠብቅልን” ሲሉ አመስግነዋል።
“የሕክምና መንደሩ” መሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስካንዲቪያን እና የኖርዲክ አገራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ሓላፊዎች ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ካህናት አባቶች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሥራ ሓላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት
©EOTC tv

የላሊበላ ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ውይይት ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።

የ40 ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ቅዱስ ላሊበላ ከተማ መግባታቸው ይታወቃል።
በዚህ ጉብኝት ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን ውቅር አብያተክርስቲያናት ድንቅ የታሪክና የጥበብ ሥራዎች ከመመልከት ባለፈ፣ ከቤተክርስቲያን አባቶችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።
እንደ ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ ዘገባ ከሆነ ከ”ዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት” ተወካዮች እንዲሁም ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመሆን ቅርሶቹን ከተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ እንዲሁም በዘላቂ ልማት ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ቅዱስ ላሊበላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በተጓዙ አካላት በተደረገ ጥናትና በዩሮኒውስ በተዘገበው መረጃ መሠረት፣ በዓለም ካሉ የዓለም ቅርስ መዳረሻዎች መካከል ቀዳሚ ከሆኑ አምስት ምርጥ መዳረሻዎች አንዱ ሆኖ መመረጡ ይታወሳል።
©የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እና የዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ለአስተዳደር ጉባኤው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ እየሠራ ያለውን የተለያዩ የጥናት ሰነዶች አቀረበ፡፡

ሰኔ 24 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እና ዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ በዘመናዊ የዲጂታል ዓለም ውስጥ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ማድረግ የምትችልባቸውንና አስተዳደራዊ አቅሟን ለማሳደግ የሚረዱ ሙያዊ ምክረ ሐሳቦችንና ስልታዊ ጥናቶችን በማቅረብ እንዲሠራ የተቋቋመ ኮሚቴ ነው፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ ለአስተዳደር ጉባኤ ባቀረቡት ጥናት “ቤተክርስቲያን በቴክኖሎጂ የዳበረ ዘመናዊ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሥርዐትን ለመገንባት ከመንፈሳዊ እሴቶች ጋር የተጣጣመ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ለቀጣይ ትውልድ አገልግሎት መስጠት የሚችል የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚያስፈልጋት አስረድተዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ለማስፋፋት፣ አስተዳደሯን ለማዘመን፣ የፋይናንስ ሥራዎቿን ለማቀላጠፍ፣ የቤተክርስቲያን ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን ለማስጠበቅና ለማስተዳደር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስቀድሞ ለአገልግሎት ትጠቀምባቸው የነበሩ ሀርድ ኮፒዎች ዲጂታይዝ ለማድረግ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እና ዲጂታል ሽግግር አማካሪ ስትራቴጂክ ሰነድ መዘጋጀቱን ሰብሳቢው ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያን ለዘመናት የቆዩ የብራና መጻሕፍት፣ የቅኔ፣ የያሬዳዊ ዜማዎችና የቅዱሳት ሥዕላት ባለቤት መሆኖከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ካህናትና ምእመናንን የምትመራ ቢሆንም እነዚህ ሁሉ ትላልቅ መረጃዎችና መዛግብት ግን በአንድ ላይ ተሰንደው ከመቀመጥ ይልቅ በተበታታነ ሁኔታ እንደሚገኙ ተገልጿል። በመሆኑም የቤተክርስቲያን ቅርስና ሀብት ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም በአንድ ማዕከል ሠንዶ ማስቀመጥ እንደሚገባ ሰብሳቢው አስገንዝበዋል ፡፡
የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አመራር ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረትና የተከናወኑ ተግባራትን በማድነቅ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ እነዚህ ትላልቅ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ተጠናቀው በአዲሱ በጀት ዓመት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥናቱን በማዘጋጀት ያቀረቡ የኮሚቴ አባላትን አመስግነው፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በግንቦት ፳፻፲፰ ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጀንዳው መቅረቡን ጠቅሰዋል። ምልዓተ ጉባኤውም በአጀንዳውና የቀረቡለት የተለያዩ ሥራዎችን በመገምገም የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መመሪያ መስጠቱን አውስተዋል።ዛሬ የቀረቡትም የተለያዩ የጥናት ሰነዶችም ይህንኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በብፁነታቸው የተመራው የአስተዳደር ጉባኤ አባላት በመንበረ ፓትርያተርክ ቅጽር ግቢ የሚሠራውን የልማት ሥራ ተመልክተውዋል፤ በተለይም ለብፁዓን አባቶች ማረፊያ ቤት አጠገብ የሚሠራውን ግንባታ በልዩ ትኩረት በአፋጣኝ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡©Eotc tv