የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት የምስክር ጉባኤ ቤት 19 ደቀመዛሙርትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስመረቀ።
ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ምባሕርዳር-ኢትዮጵያ
በምርቃት መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስካንዲቪያንስ እና የግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስክር ጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ሓላፊዎች ፣ የምስክር ጉባኤ ቤቶች መምህራን ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ተመራቂዎችና የተመራቂ ደቀመዛሙርት ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ጥሪ የተረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመርሐ ግብሩ ላይ ለተመራቂ ደቀመዛሙርት እና ለቤተክርስቲያን የእንኳን ደስ ያለን መልእክታቸው አስተላልፈው “የዛሬ ተመራቂ ደቀመዛሙርት የነገ መምህራን የቅድስት ቤተክርስቲያን ሉዓላዊነትነት ተከብሮ እንዲዘልቅ ፣ ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ የቅዱስ ሲኖዶስ የተዘረጋው የቤተክርስቲያን ሰንሰለት ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ለሐዋርያዊ አገልግሎት በምትጓዙበት ሁሉ በርትታችሁ ልትሠሩ ይገባል” ብለዋል።
የብፁዕነታቸው አክለውም “በማያስፈልገው መልኩ የጥንቱን እውቀታችሁን አታዘምኑት” የአባቶቻችን ትርጓሜም ወደ ቀጣይ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ ተግታችሁ ሥሩ ፣ ከእውቀት ባሻገር ለመንፈሳዊነትም ልዩ ትኩረት እንድትሰጡ ደግሞም የምታስተምሩትን በተግባር መኖር ከተመራቂ ደቀመዛሙርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በበኩላቸው ተመራቂ ደቀመዛሙርት ለፍሬ እንዲበቁ ምኞታቸውን በመግለፅ ሊቃውንት በዚህ መልኩ መመረቃቸው ጥንት ያልነበረ አሁን ግን የተለመደ ታላቅ ተግባር ነውና “ትልቅ ዕድል” ነው ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ብፁዕነታቸው የብፁዕ አቡነ አብርሃምን መልእክት በሚያጠናክር መልኩ “ሊቃውንቱ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት ፣ ከቀድሞው በበለጠ በጋራ ሊቆሙ ፣ አንድ ድምፅ ሁነውም ሊመክሩ ፣ ምክረ ሐሳባቸውንም ለቅዱስ ሲኖዶስ በትጋት ሊያቀርቡ” እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተመራቂ ደቀመዛሙርት መምህር የሆኑት ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ ደግሞ ተማሪዎቻቸው ለዚህ ደረጃ በመብቃታቸው መደስታቸውን ገልጸው በቀጣይም በምስክር ጉባኤ ቤቱ በነበራቸው ቆይታ የቀሰሙትን ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዕውቀት ተግባር ላይ በማዋል ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅም አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ከዚህ በመለስ የምስክር ጉባኤ ቤቱ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በዛሬው የደቀመዛሙርት የምርቃት በዓል ላይ ለመምህራን ማረፊያ እንዲሁም ወደ ምስክር ጉባኤ ቤቱ ለሚመጡ እንግዶች መቀበያ የሚሆን ሕንጻ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ይህ አዲስ ሕንጻ የጉባኤ ቤቱን የትምህርት ሥርዓት ለማጠናከር፣ ለተማሪዎችም የተሻለ የአስተዳደርና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።©ፈለገ ገነት ሚዲያ