የመቱ ፈለገ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጀመሪያውን ዙር እጩ መምህራን በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመረቀ

ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.| ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
​ከተቋቋመ ገና ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው የመቱ ፈለገ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ፤ ከተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ተቀብሎ ሲያሰለጥናቸው እና ሲያስተምራቸው የቆያቸውን ፲፰ እጩ መምህራን ደቀ መዛሙርት በሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. በደመቀ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።
ይህ ታሪካዊ የምረቃ በዓል የመቱ ፈለገ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ፣ ፕሬዚዳንትና የኢሉ አባ ቦር እና የምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከቶች ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ዶ/ር)፣ የቡኖ በደሌ እና የቄለም ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ብርሃኑ መንገሻ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ተካሂዷል።
​በመርሐ ግብሩ ላይ በረከታቸው ይደርብንና ታላቁና ጸሎተኛው የቀድሞው የሀገረስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ኮሌጁ በአፋጣኝ እንዲከፈት መመሪያ በመስጠትና ጥብቅ ክትትል በማድረግ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት መንሳዊ ኮሌጁ እንዲመሠረት ያደረጉት ጥረትና የነበራቸው አባታዊና መምህራዊ ምክር በታላቅ አክብሮት ተዘክሯል።
የኮሌጁ የበላይ ኃላፊና ፕሬዚዳንት ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ዶ/ር) ለአዲሶቹ እጩ መምህራን ባስተላለፉት አባታዊ አደራና ቃለ ቡራኬ፤ “ዛሬ የተሰበሰብነው ትምህርት ያበቃበትን ቀን ለማክበር ወይም የዲፕሎማና የዲግሪ ወረቀት ለመስጠት ሳይሆን፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ቀዳሚ ዓላማና የወንጌል አገልግሎት አደራ ለመቀበል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎችም ተመራቂዎቹ በሄዱበት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ፣ የተማሩትን በሥራ እንዲገልጡና የተዘጉትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያስከፍቱ ጥብቅ አደራ አስተላልፈዋል።
​ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱም በበኩላቸው ባስተላለፉት የጋራ መልእክት፤ በኮሌጁ የቆይታ ጊዜያቸው በመንፈሳዊ ዕውቀትና በሥነ ምግባር ታንጸው፣ በሚያምኑትና በማያምኑት ዘንድ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመሆን በሕይወታቸው ተነባቢ መጽሐፍ ሆነው መኖርንና ሐዋርያዊ ግዴታቸውን መወጣትን እንደተረዱ ገልጸዋል። አያይዘውም “ከዚህ በኋላ የፍጥረት ሁሉ መዳኛ የሆነውን ወንጌል ይዘን የምናስተምርበት፣ ጨለማውን ዓለም የምናበራበት፣ የታመመውን የምናክምበት እንዲሁም በቃልም ሆነ በሥራ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ የምንፈጽምበት ጊዜ ነው፤ ትምህርት አላለቀም፣ በማስተማር ውስጥ መማር በመማር ውስጥ ማስተማር ይቀጥላል፤ በቀጣይ ሕይወታችን በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ፣ እንደ እባብ ልባም እንደ እርግብም የዋህ ሆነን አገልግሎታችንን እንፈጽማለን” ሲሉ ቃላቸውን አድሰዋል።
​በዕለቱ መርሐ ግብር ላይ በኮሌጁ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀችው “መጽሔተ ጥበብ ቁጥር ፩” የተሰኘችው መጽሔት ተመርቃ ለአገልግሎት የበቃች ሲሆን፤ በኮሌጁ የሚገኙ የአስተዳደር፣ የመምህራንና የድጋፍ ሰጪ አካላት ደቀ መዛሙርቱ በውጤታማነት እንዲመረቁ ላደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጥቷል። በሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይም ለኮሌጁ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት፣ ለደቀ መዛሙርቱና በከፍተኛ ውጤት ለተመረቁ ተመራቂዎች የምስክር ወረቀትና የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
​ዘገባው፦ የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሚዲያ

የጋርመንት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አዲስ የሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፤ ከ5.7 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የልማት ሥራዎች ተመረቁ።

ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም.
የጋርመንት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአዲስ ለሚገነባው የሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተገኝተው የመሠረት ድንጋዩን የባረኩ ሲሆን፣ የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችንም መርቀዋል።
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ባቀረበው ልማታዊ ሪፖርት መሠረት፣ ቤተ ክርስቲያኑ በ1997 ዓ.ም. በአነስተኛ መቃኞ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 1.34 ሚሊዮን ብር ክፍያ በመፈጸም 1,350 ካሬ ሜትር ተጨማሪ ቦታ ወደ ደብሩ ይዞታ እንዲካተት አድርጓል።
በዕለቱ በብፁዕነታቸው የተመረቀውና ቀደም ሲል በአፈርና በገረጋንቲ ተራራ ተሸፍኖ ለጎርፍ አደጋ ተጋልጦ የነበረው የቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት፣ በባለሙያ በተጠናው መሠረት ምዕራባዊ አቅጣጫውን የጠበቀና ደረጃውን የጠበቀ የመጠለያ፣ የቴራዞ፣ የኮብልስቶን ንጣፍና የውኃ ፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎች ተከናውነውለታል። ለነዚህ የዐውደ ምሕረት ማሻሻያና መጠለያ ሥራዎች በሰበካ ጉባኤውና አዲስ በተዋቀረው የልማት ኮሚቴ አማካኝነት፣ ከምዕመናን በዓይነት ከተገኘው ድጋፍ ጋር ተደምሮ በአጠቃላይ 5,788,538.92 (አምስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰማንያ ስምንት ሺሕ አምስት መቶ ሠላሳ ስምንት ብር ከዘጠና ሁለት ሳንቲም) ወጪ መደረጉ ታውቋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፤ የመጀመሪያውና ዋናው ልማት ወንጌል እንደሆነ ዐፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። አክለውም “ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቁጥር መጨመር ምላሽ የሚሰጥና ለትውልድ የሚተላለፍ አዲስ ሕንጻ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ባርከን አስቀምጠናል፤ ነገር ግን አዲስ ሕንጻ ሲታነጽ በዲዛይንና በጥራት ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል። ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት ከተሠራ በኋላ የዲዛይን ችግርና የቦታ መጥበብ እንዳያጋጥም ሥራውን በቶሎ በመጀመር በጥራት እንዲያጠናቅቁ መመሪያ የሰጡት ብፁዕነታቸው፣ ቤተ መቅደስ ማነጽ የሚቻለው እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው ብቻ በመሆኑ ምዕመናኑ የተሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው ጊዜ ሳያባክኑ እንዲረባረቡ አሳስበዋል።
የዕለቱን ትምህርተ ወንጌል የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “እግዚአብሔር በእውነት በዚህ ስፍራ አለ” (ዘፍ 28፥16) የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ዓለማየሁ ተፈራ በበኩላቸው፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጧቸውን በርካታ አብያተ ክርስቲያናት መመሪያ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በቅርበት ክትትል ስለሚያደርጉ፣ በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ግንባታቸው ዘግይቶ የነበሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተጠናቀው መመረቃቸውን አስታውሰዋል።
በዕለቱ በደብሩ ለተሠሩ የልማት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምዕመናን የሽልማትና የምስጋና ሰርተፍኬት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ተስፋዬ ለሜቻ፣ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ መጋቤ ወንጌል ሄኖክ ታዬ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ጳውሎስ ከበደ፣ የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩም አክሊሉ፣ የደብሩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ማኅበረ ካህናትና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቅቋል።
Miidiyaa Biyya Lallabaa Shaggar/የሸገር ሀገረ ስብከት ሚዲያ/

የሲኤምሲ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ካቴድራል ተብሎ ተሰየመ።

ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም
‎በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር የሚገኘው ታላቁ ደብረ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ዕለት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ካቴድራል ተብሎ ተሰይሟል።
‎ቤተ ክርስቲያኑ ላለፉት ዓመታት ለአካባቢው ምዕመናን ታላቅ የመንፈሳዊ አገልግሎት ማእከል በመሆን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ስፋት፣ የማኅበረሰቡ ቁጥር ማደግ፣ እንዲሁም የሕንጻውና የአደረጃጀቱ ታላቅነት አሁን ላይ የካቴድራልነት ማዕረግን ለመቀናጀት አብቅቶታል።
‎ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሥፍራው ተገኝተው ሕዝበ ክርስቲያኑን የባረኩ ሲሆን፣ የደብሩን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ልዩ መመሪያና ቡራኬ ሰጥተዋል ።
‎በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስበከት ሊቀ ጳጳስ ሀዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፤ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስበከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ምህርት አባ ገብረመድኅን ንጉሤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መልአከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ የካቴድራሉ አስተዳዳሪን ጨምሮ የገዳማት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና ምዕመናን ተገኝተዋል።
‎ይህ የካቴድራልነት ስም መጠሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የአገልግሎት ስፋትንና ለወጣቱ እንዲሁም ለታዳጊው ትውልድ የሚሰጠውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ኃላፊነት የሚጥል ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።
‎ይህ ታሪካዊ ዕለት በደብሩ መዝገበ ታሪክ ላይ በደማቅ ቀለም የሚጻፍም ይሆናል ሲሉ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ ገልጸዋል።
‎በዕለቱ አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡት ዶክተር ቀሲስ ኢንጂነር ጌታቸዉ ፈለቀ የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ሲሆን ቤተክርስቲያኑ አሁን ያለበት ደርጃ ላይ ለማድረስ 300 ሚሊዮን ብር መውጣቱን ጠቁመው ፤ ደብሩ ሰፊ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል ።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

ልዩ ምስጋና

በየዓመቱ የሕዝብ ግንኙነት ሥራችንን ክፍተቶች ለይተን አቅማችንን የምናጎለብትበትን ሥልጠና በመምሪያችን አዘጋጅነት እንደምንሰጥ ይታወቃል።በዚህ ዓመትም ያዘጋጀነውን ሥልጠና በውጤታማነት አከናውነናል።
ከሥልጠናው ያገኘናቸውን ግብዓትች አሰባስበን፣በአቋም መግለጫችን ያካተትናቸውን ነጥቦች ቀምረን፤ የቀጣዩ ዓመት ሥራችንን የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይተንና ባዘጋጀነው ዕቅድ አካተን የመጪውን አዲስ ዓመት ሥራችንን በስኬትና በድል ለመቋጨት በብርቱ እንደምንሰራ የሥልጠናችን ውጤት አመላክቶናል።
ሥራዎቻችንን ለባረከልን፣በስኬት እንድንጓዝ ላደረገን የቤተክርስቲያን አምላክ ዘወትር ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ለሥራዎቻችን ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉልን ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያለንን ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና እናቀርባለን።
በየዓመቱ በምናካሒደው የአቅም ግንባታ ሥስልና ላይ ዕውቀታችሁን ያለ ስስት በመለገስ ሁሌም ከጎናችን ለምትቆሙ ውድ አሰልጣኞቻችን፣እግዚአብሔር አምላክ ረጅም ዕድሜና መልካም ጤንነትን ይሰጣችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎትና ምኞታችን መሆኑን በአክብሮት ስንገልጽላችሁ ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል።
አሃዱ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የሥልጠናችንን ሙሉ ወጪ ባይሸፍንልን ኖሮ ይሄን የመሰለ ሥልጠና ለማሳካት አንችልም ነበርና ለአሃዱ ባንክ አመራሮችና ሰራተኞች ከፍ ባለ ትህትና ምስጋናችን ይድረሳችሁ እንላለን።
እኛ ያለንን አቅም ተጠቅመን ቤተክርስቲያንን የሚጠቅም ሥራ መሥራትና በውጤት መገለጥን ተቀዳሚ መርሐችን አድርገን አገልግሎታችንን እናሳልጣለን።የቤተክርስቲያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሥራችንን ስለሚባርክልንና ውጤታማ ስለሚያደርገን ዘወትር እናመሰግነዋለን።በስልጠናው ላይ በትጋት የተሳተፋችሁ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በሙሉ በሰላም ወደየ አህጉረ ስብከታችሁ እንድትመለሱ መልካም ምኞታችንን እንገልጣለን።
ሊቀ ሥዩምን እስክንድር ገብረክርስቶስ
የጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ኃላፊ
ሐምሌ፲፪ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም

የሀገር አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ሥልጠና በወንጪ ሐይቅ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ታሪካዊ ጉብኝት በማድረግ ተጠናቀቀ።

ሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
“የሕዝብ ግንኙነት ስኬት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል ለሀገር አቀፍ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በከፍተኛ ዝግጅት ሲሰጥ የሰነበተው ፫ኛው ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት በወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ጉብኝት ተጠናቋል።
የዚሁ ታሪካዊ ሥልጠና ማጠቃለያ ይሆን ዘንድ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በወንጪ ወረዳ በሚገኘው ታዋቂው የወንጪ ሐይቅ ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም ልዩ የጉብኝት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
ይህ ታላቅ የጉብኝት እና የመስክ ውይይት መርሐ ግብር በወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሊከናወን የቻለበት ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሀገረ ስብከት በመሆኑና መርሐ ግብሩን በዚህ ታሪካዊ ሥፍራ ቢከናወን የሥልጠናውን ማጠቃለያ ይበልጥ ልዩና ታሪካዊ መርሐ ግብር ስለሚደርገው በልዩ ሁኔታ መመረጡ ተገልጧል።
ሠልጣኞቹ በጉብኝቱ ወቅት የወንጪ ሐይቅ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሠረተና የታላቅ መንፈሳዊ ታሪክ ባለቤት መሆኑን የተረዱ ሲሆን አካባቢው በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር የቱሪስት መስህብ ሆኖ መሠራቱን ተከትሎ ወደ ሥፍራው ለጉብኝት የሚጓዙ ጎብኚዎች ጥንታዊውን የቅዱስ ቂርቆስ ገዳምን እንዲጎበኙ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ጥንታዊ መሠረቱን ሳይለቅ በአዲስ መልክ እንዲሠራ ክቡር የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚሠራ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
በገዳሙ የሚከናወኑትን የልማት ሥራዎች በርካታ ብፁዓን አባቶች የጎበኙትና ለግንባታ ሥራው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን በገዳሙ ውስጥ በርካታ አህጉራዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ታላላቅ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎቹ ተመልክተዋል።
ሠልጣኞቹ በገዳሙ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ፣ የሙዚየም ግንባታ፣ የቤተ መቅደስ ግንባታ፣ የቤተልሔም ሕንጻ እንዲሁም አጠቃላይ የቅጥርና የመሠረተ ልማት ግንባታ ሂደቶች በፍጥነት በመገንባት ላይ መሆናቸውን ተመልክተዋል። በጉብኝቱ ወቅት ስለ ገዳሙ ጥንታዊ አመሠራረት፣ ስለ ነበረው ታሪክና አሁን ስላለው ሁለንተናዊ የዕድሳት ሂደት ሰፊና ጥልቅ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ ሠልጣኞቹም ካዩት ታላቅ መንፈሳዊ ቅርስና የልማት እንቅሰቃሴ በመነሳት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታና አበረታች አስተያየት በስፋት ገልጸዋል።
ከዚሁ መንፈሳዊ የጉብኝት መርሐ ግብር ማጠቃለያ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ በሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ አማካኝነት ለሠልጣኞቹ የተሳትፎ የምስክር ወረቀት በታላቅ ሥነ ሥርዓት ተበርክቶላቸዋል።
የመምሪያው ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ለሠልጣኞቹ ባስተላለፉት ጥብቅ መመሪያ፤ ኃላፊዎቹ በሥልጠናው ወቅት ያገኙትን ከፍተኛ ዕውቀትና ክህሎት ወደየአህጉረ ስብከታቸው በሚመለሱበት ወቅት ያለምንም መዘግየት ወደ ተግባር እንዲቀይሩት አሳስበዋል። አያይዘውም ተሳታፊዎቹ የእውነት ጠበቃ በመሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ድምፅ እንዲሆኑ፣ በተመደቡበት የኃላፊነት ቦታና አገልግሎት ሁሉ ሳይታክቱና ሳይሰለቹ በርትተው እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ለሃይማኖታቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው በጽናት እንዲቆሙ በብርቱ ቃል አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የመምሪያው ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ይህ አገር አቀፍ የሥልጠናና የጉብኝት መርሐ ግብር እጅግ የተሳካ፣ ፍሬያማና ውጤታማ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ ሙሉ የገንዘብ ወጪውን በመሸፈን የላቀ ክርስቲያናዊ አጋርነቱንና ታሪካዊ ድጋፉን ላሳየው ለአሐዱ ባንክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ከፍተኛ ምስጋናቸውንና አድናቆታቸውን አቅርበው መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል።
ፎቶ Eotc tv

በቡራዩ ከተማ የተገነባው “ፈለገ ጥበብ (ቡርቃ ኡጉማ)” አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ተመረቀ።

በቡራዩ፣ ገፈርሳ ጉጄ እና መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማ በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ሙሉ ወጪ የተገነባውና “ፈለገ ጥበብ (ቡርቃ ኡጉማ)” የተሰኘው አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በይፋ ተመርቋል ።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ
አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተገኝተው ትምህርት ቤቱን መርቀዋል።
በተጨማሪም የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ዓለማየሁ ተፈራ፣ የቡራዩ ገፈርሳ ጉጄ እና መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የቡራዩ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ
አቶ ዓሥራት አባተ እንዲሁም ሌሎች የሸገር ከተማ እና የቡራዩ ክፍለ ከተማ የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎች፣
አገልጋዮችና ምዕመናን በምረቃው ላይ ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና የተለያዩ የሥራ
ኃላፊዎች የገቡትን የገንዘብ ቃል ኪዳን ከሠራተኞችና ከምዕመናን ጋር በመተባበር ገቢ በማድረጋቸው ግንባታው በተሳካ ሁኔታ
ሊጠናቀቅ ችሏል። የከታ ወረዳ ነዋሪዎችና የትምህርት ማኅበረሰቡም ትምህርት ቤቱ ለአገር ተረካቢ ትውልድ መፍለቂያ ምንጭ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
ይህ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት የተገነባበት ዋነኛ ዓላማ በአገራችን የመንግሥት ዘመናዊ ትምህርት የሚጀምረው ከአንደኛ (1ኛ)
ክፍል በመሆኑና ቅድመ መደበኛ (መዋዕለ ሕፃናት) ትምህርት በከፍተኛ ክፍያ በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ስለሚሰጥ የሚፈጠረውን
የትምህርት ተደራሽነት ልዩነት ለመቅረፍ እንደሆነ ተጠቅሷል። አቅም የሌላቸው ሕፃናት ያለ ቅድመ መደበኛ ዝግጅት አንደኛ (1ኛ)
ክፍል ሲገቡ ከሌሎች ጋር እኩል ለመራመድ የሚገጥማቸውን የአቅም ውስንነት ለመሙላት ትምህርት ቤቱ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው
ተገልጿል።
በምረቃው ወቅት ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን በየዛፉ ሥርና
በየአድባራቱ የጀመረች፣ ፊደል ቀርጻና ቀለም በጥብጣ በርካታ መጻሕፍትን የጻፈች መሆኗን አስታውሰዋል። ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ
ሕይወት ውስጥ የምታበረክተውን ሰላም የማውረድ ሥራና ታቦት ይዛ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እስከ ጦር ግንባር ድረስ ያደረገችውን ጉዞም ጠቅሰዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም “ትምህርት ቤት ዜጎች የሚቀረጹበት በመሆኑ ከሁሉ የላቀ ትልቅ ሥራ ነው” ካሉ በኋላ፣ ትምህርት ቤቱ
ሁሉንም በጋራ የሚያገለግልና ለሕዝብ ጥቅም የተሠራ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
አጠቃላይ ግንባታው በአምስት መቶ ዘጠና ሰባት ነጥብ ስምንት ስድስት (597.86) ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣
እያንዳንዳቸው ከአርባ እስከ አምሳ (40 እስከ 50) ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ክፍሎችን ይዟል። ትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ አሥራ ስድስት (16) ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፣ የሚከተሉትን ዝርዝሮች ያጠቃልላል።
1. ስምንት (😎 መማሪያ ክፍሎች
2. አንድ (1) የርዕሰ መምህር አስተዳደር ቢሮ
3. አንድ (1) የተማሪዎች መመገቢያ ክፍል
4. ሁለት (2) የሕፃናት ተማሪዎች ማረፊያ (መኝታ) ክፍሎች
5. አንድ (1) የጽዳት ዕቃ ማስቀመጫና ልብስ መቀየሪያ ክፍል
6. አንድ (1) የመምህራን ማረፊያና ጋዎን መቀየሪያ ክፍል
7. ሁለት (2) የመምህራን መጸዳጃ ክፍሎች በተጨማሪም አምስት በአምስት (5 በ 5) ሜትር የሆነ የመጸዳጃ ሴፍቲ ታንከር፣ ባለ ስድስት (6) ክፍል የተማሪዎች መጸዳጃ
ቤት፣ በሰማንያ (80) ቆርቆሮ የተሠራ የተማሪዎች ምግብ ማብሰያ ክፍልና ባለ አንድ (1) ክፍል የጥበቃ መኖሪያ ቤት ተገንብቶለታል።
ለግንባታው በጥሬ ገንዘብና በማቴሪያል በድምሩ ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ ሦስት መቶ አሥራ ስድስት ብር
ከሃምሳ ሳንቲም (6,586,316.50) የተገኘ ሲሆን፣ ለግንባታው ሥራ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሰባት ሺህ አሥራ ሰባት ብር ከሃምሳ ሁለት ሳንቲም (5,537,017.52) ወጪ ተደርጓል።
በሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ የትምህርት ቤቱ ቁልፍ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አማካኝነት ለቡራዩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ለአቶ ፀጋዬ አመና የተላለፈ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚገልጽ ስያሜ ይሰጠው በሚለው ጥያቄ መሠረት፣ ቀደም ሲል “ቡኡራ ቦሩ” ተብሎ ይጠራ የነበረው ይህ ትምህርት ቤት በብፁዕነታቸው “ፈለገ ጥበብ አፀደ ሕፃናት (ቡርቃ ኡጉማ)” ተብሎ ተሰይሟል።
©Eotc tv

የቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዲግሪ መርሐ ግብር እና በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ያስተማሯቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም
የቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የዲግሪ መርሐ ግብራት በጤና ሳይንስ እና ሌሎች ዘርፎች ያስተማራቸውን ተማሪዎቹን ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ስብሐት አባ ገብረ ሥላሴ በተገኙበት አስመርቋል።
ኮሌጁ በዲግሪ 460 ፤ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና 343 በጠቅላላው 803 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
​ኮሌጁ እስካሁን ለ18 ጊዜ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ፤ በጤናና በቴክኒክ ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዲን ዶክተር እስጢፋኖስ ዮሐንስ ገልጸዋል ። ኮሌጁ ለተመራቂዎቹ ሥራ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱ ነው የተገለጸው።
የኮሌጁ ዲን ዶክተር እስጢፋኖስ ዮሐንስ ኮሌጁ አሁንም በሚሰጠው ጥራት ያለው ትምህርት፣ የምርምር ሥራዎችንና የማኅበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ በዘርፉ ተወዳዳሪና ተመራጭ ኮሌጅ በመሆን እየሠራ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ በሬሚዲያል የትምህርት መርሐ ግብር ተማሪዎችን በማብቃት እና ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ እና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ በማስቻል የበኩሉን ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ተመራቂዎች ቃለ መሐላ የፈጸሙ ሲሆን ሌሎች መርሐ ግብራት ተከናውነዋል።
በመጨረሻም በ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተመራቂዎች በተማሩት ትምሕርት ወገናቸውን በትጋት እንዲያገለግሉ አደራ በማለት በጸሎተ ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል።
የቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ በ1997 ዓ.ም በመቋቋመ የቤተክርስቲያናችን የትምሕርት ተቋም ነው።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም መንፈሳዊ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች የምርቃት ሥነ-ሥርዓት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።

ሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
በርካታ እውቅ ሊቃውንትን ያፈራውና በታሪክ ታላቅ ስፍራ ያለው የጥንታዊው የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርት የምርቃት ሥነ-ሥርዓት በአሁኑ ሰዓት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ታላቅ መርሐ-ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የገዳሙ የበላይ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ታድመዋል።
ተመራቂዎቹ በገዳሙ የነበራቸውን የመንፈሳዊና የቀለም ትምህርት አጠናቀው ለዚህ ማዕረግ የበቁ ሲሆን፣ በዚህ ታላቅ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መርሐ ግብሩን በፀሎት ከፍተዋል።በመቀጠልም በገዳሙ አስተዳደር በሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ተ/ኃይማኖት ወልዱ ሪፖርት ቀርቧል።
በሪፖርቱም እንደተጠቀሰው ገዳሙ ከ1995 ጀምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርት ማፍራቱ ተገልጿል። በዚህም የማስተማር ሥራው በዓለማዊውም መድረክ ቢሆን ሀገር ከመምራት ጀምሮ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ደቀ መዛሙርትን ያፈራ የሀገር ባለ ውለታ መሆኑን አንስተዋል።ገዳሙ በዛሬው የምረቃ መርሐ ግብርም 263 ተማሪዎችን ለምርቃት ያበቃ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 79 የአብነት ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ በቅዳሜና እሑድ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሚመረቁ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
አክለውም የገዳሙ ትምሕርት ቤት በኮሪደር ልማት ምክንያት የፈረሰ በመሆኑ አዲስ ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተመራቂ ደቀመዛሙርት ወረብ ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የሠርተፊኬት አሳጣጥ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚከናወን እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት ይከወኑበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የሥነ-ሥርዓቱን አጠቃላይ ሂደትና ማጠቃለያ ዝርዝር መረጃ መርሐ-ግብሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ለመንበረ ፓትርያርክና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዘመናዊ ኮምፒውተር በስጦታ አበረከተ።

ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ሰባት ደራጃቸውን የጠበቁ ኮምፒወተሮች በስጦታ አበርክተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው እንደተናገሩት መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ ለዚያ የሚያግዙ አምስት ኮምፒውተሮች፣ለቅዱስ ሲኖዶስ ሁለት ኮምፒውተር በአጠቃላይ ሰባት ኮምፒውተሮች በስጦታ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት “በጠቅላይ ቤተክህነት ብዙ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከልማት ሥራዎች በተጓዳኝ መጻሕፍቱ፣ የተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ዲጂታል እየተደረጉ ነው፤ ሥራ ሲሠራ መተጋገዝ የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ስላደረጉልን እገዛ እናመሰግናለን በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ባለሙያ ዲያቆን ሙሉዓለም ዐሥራት እነዳብራሩት “ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተለያዩ ዘርፎች ትኩረት በመስጠት ልማቶችን ያከናውኑ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የቤተክርስቲያን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚያጠናክሩ ከዚህም በተጨማሪ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ዲጂታል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት፡፡” ብለዋል፡፡ ባለሙያው አክለውም “ቤተክርስቲያን በርካታ የመረጃ ሀብት ያላት መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ መረጃዎቿና ዕውቀቶቿ በአግባቡ ተደራጅተው ያሰተቀመጡ በመሆናቸው፤ እነዚህን መረጃዎች ማስተዳደር የሚቻልባቸው አሠራር ለመዘርጋት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የዲጂታል ሥራዎች ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ አቋቁሞ በሥራ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
እነዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የዲጂታል ሥራዎች ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ በመሆናቸው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ደረጃቸውን የጠበቁ ኮምፒውተሮችን ድጋፍ አድርገውልናል፤ልማት ኮሚሽን ያደረገው ትብብርና እገዛ በጣም ትልቅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድጋፎች ማግኘታችን የጀመርነውን ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ለማምጣት የሚያግዙ ስለሆኑ ሌሎችም አካላት ይህን ዓላማ ቢያግዙ ቤተክርስቲያን አሁን ያለችበትን መንፈሳዊ አገልግሎት በተሻለና ዘመኑ በሚጠይቀው ደረጃ ለማገልገል ዕድል ይሰጣታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

የቤተክርስቲያንን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት በዘመናዊ መንገድ ለማጠናከር የሚያስችል የምክክርና የሥልጠና መርሐ ግብር የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሔደ።

ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አዘጋጅነት ለአህጎረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተዘጋጀው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ላይ «የቤተ ክርስቲያን ትርክት» በሚል ርዕስ ልዩ ሥልጠና ተሰጠ።
ሥልጠናው በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በሐምሌ ፱ እና ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. በተካሄደው የሁለት ቀን መርሐ ግብር ውስጥ የተካተተ ሲሆን፣ በሁለተኛው ቀን ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የግማሽ ቀን ሥልጠና አቅርበዋል።
በሥልጠናው ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ተቋም ብቻ ሳትሆን፣ በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተች፣ ሰማያዊ ጥሪና ዘላለማዊ ተልእኮ ያላት ቅድስት ተቋም መሆኗ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በትውፊትና በታሪክ መሠረት ተብራርቷል።
እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ትርክት በጊዜያዊ ክስተቶች የሚወሰን ሳይሆን፣ በወንጌል፣ በመስቀልና በትንሣኤ ምሥጢር ላይ የተመሠረተ ዘላለማዊ መልእክት መሆኑ ተገልጿል።
በሥልጠናው ዘመናችን በተለያዩ የመገናኛ መድረኮች ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚሰራጩ የተሳሳቱ ትርክቶች፣ የሐሰት መረጃዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች በምእመናን አንድነትና በቤተ ክርስቲያኒቱ ገጽታ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ተዳሷል።
የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ትርክት ለማስጠበቅ በእውነት፣ በትውፊትና በሙያዊ የመገናኛ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ተቋማዊ የመረጃ አሠራር መገንባት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የመረጃ አስተላላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛ ትርክት፣ እምነት፣ ትውፊትና መንፈሳዊ እሴቶች ለትውልድ የሚያስተላልፉ አደራ የተሰጣቸው አገልጋዮች መሆናቸው ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ መጠናቀቂያ ላይ ተሳታፊዎቹ የተማሩትን ዕውቀት በየአህጎረ ስብከቶቻቸው ተግባራዊ ለማድረግ እና የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ትርክት ለምእመናን በተአማኒነት ለማቅረብ የሚያስችል የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
በአቋም መግለጫው፦
1. በሥልጠናው የተገኘውን ዕውቀትና ልምድ በየአህጎረ ስብከቶቻቸው ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
2. በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና መምህራን ላይ የሚሰነዘሩ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ለመመከት፣ ለምእመናንም ትክክለኛና ተአማኒ መረጃዎችን ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።
3. የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩ እንዲጠናከር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስፈላጊ ውሳኔ እንዲያሳልፍ በትህትና ጠይቀዋል። በየአህጎረ ስብከቶቻቸውም መዋቅሩን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
4. የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊትና ሥርዓት በመጠበቅ፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መንፈሳዊ አገልግሎቶቿን ለምእመናን ተደራሽ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
5. ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ የመገናኛ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት መልካምና ውጤታማ ግንኙነት ለመፍጠር ቃል ገብተዋል።
የሥልጠናውና የአቋም መግለጫው የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የመረጃ ማሰራጫ ብቻ ሳይሆን፣ የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ትርክት፣ እምነትና መንፈሳዊ እሴቶች ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ መሆኑን አረጋግጧል።