የቤተክርስቲያንን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት በዘመናዊ መንገድ ለማጠናከር የሚያስችል የምክክርና የሥልጠና መርሐ ግብር የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሔደ።
ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.፣ አዲስ አበባበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አዘጋጅነት ለአህጎረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተዘጋጀው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ላይ «የቤተ ክርስቲያን ትርክት» በሚል ርዕስ ልዩ ሥልጠና ተሰጠ።
ሥልጠናው በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በሐምሌ ፱ እና ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. በተካሄደው የሁለት ቀን መርሐ ግብር ውስጥ የተካተተ ሲሆን፣ በሁለተኛው ቀን ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የግማሽ ቀን ሥልጠና አቅርበዋል።
በሥልጠናው ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ተቋም ብቻ ሳትሆን፣ በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተች፣ ሰማያዊ ጥሪና ዘላለማዊ ተልእኮ ያላት ቅድስት ተቋም መሆኗ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በትውፊትና በታሪክ መሠረት ተብራርቷል።
እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ትርክት በጊዜያዊ ክስተቶች የሚወሰን ሳይሆን፣ በወንጌል፣ በመስቀልና በትንሣኤ ምሥጢር ላይ የተመሠረተ ዘላለማዊ መልእክት መሆኑ ተገልጿል።
በሥልጠናው ዘመናችን በተለያዩ የመገናኛ መድረኮች ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚሰራጩ የተሳሳቱ ትርክቶች፣ የሐሰት መረጃዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች በምእመናን አንድነትና በቤተ ክርስቲያኒቱ ገጽታ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ተዳሷል።
የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ትርክት ለማስጠበቅ በእውነት፣ በትውፊትና በሙያዊ የመገናኛ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ተቋማዊ የመረጃ አሠራር መገንባት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የመረጃ አስተላላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛ ትርክት፣ እምነት፣ ትውፊትና መንፈሳዊ እሴቶች ለትውልድ የሚያስተላልፉ አደራ የተሰጣቸው አገልጋዮች መሆናቸው ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ መጠናቀቂያ ላይ ተሳታፊዎቹ የተማሩትን ዕውቀት በየአህጎረ ስብከቶቻቸው ተግባራዊ ለማድረግ እና የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ትርክት ለምእመናን በተአማኒነት ለማቅረብ የሚያስችል የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
በአቋም መግለጫው፦
1. በሥልጠናው የተገኘውን ዕውቀትና ልምድ በየአህጎረ ስብከቶቻቸው ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
2. በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና መምህራን ላይ የሚሰነዘሩ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ለመመከት፣ ለምእመናንም ትክክለኛና ተአማኒ መረጃዎችን ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።
3. የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩ እንዲጠናከር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስፈላጊ ውሳኔ እንዲያሳልፍ በትህትና ጠይቀዋል። በየአህጎረ ስብከቶቻቸውም መዋቅሩን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
4. የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊትና ሥርዓት በመጠበቅ፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መንፈሳዊ አገልግሎቶቿን ለምእመናን ተደራሽ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
5. ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ የመገናኛ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት መልካምና ውጤታማ ግንኙነት ለመፍጠር ቃል ገብተዋል።
የሥልጠናውና የአቋም መግለጫው የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የመረጃ ማሰራጫ ብቻ ሳይሆን፣ የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ትርክት፣ እምነትና መንፈሳዊ እሴቶች ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ መሆኑን አረጋግጧል።