የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት እየተገነባ ያለውን ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የግንባታ ሂደትን ጎበኙ።
ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.| ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ“የሕዝብ ግንኙነት ስኬት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል ለአገር አቀፍ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የተዘጋጀው ፫ኛው ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለትም ተሰጥቶ የዋለ ሲሆን፤ ሠልጣኞቹ የዕለቱን መርሐ ግብር ካጠናቀቁ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለውን ሁለገብ ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽን የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።
ይህ ጉብኝት የተከናወነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስኪያጅና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን፤ ከብፁዕነታቸው ጋር በመሆን ሠልጣኞቹን ያስጎበኙት ኢንጂነር ሔኖክ ልዑልሰገድ ናቸው። ኢንጂነር ሔኖክ በጉብኝቱ ወቅት በዋናነት ትኩረት ስለተሰጠውና ዘመናዊ መገልገያዎችን ስላካተተው ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ሂደት፣ እንዲሁም ስለ ሕንጻው አጠቃላይ ይዘትና ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ለሰልጣኞቹ በሰፊው አቅርበዋል።
በማብራሪያው ላይ እንደተገለጸው፤ ይህ በ2,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ግዙፍና ዘመናዊ ሕንጻ በአንድ ጊዜ 2,500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አዳራሽ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ አዳራሽ፣ በ282 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ አነስተኛ የበታች ኮሚቴዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የክብር እንግዶች ማረፊያ፣ ዘመናዊ ምግብ ቤት እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ በርካታ ቢሮዎችን ያካተተ ነው። ሕንጻው ከመደበኛ የግንባታ ጥበቡ ባሻገር እስከ 30 ቋንቋዎችን በቅጽበት መተርጎም የሚችል የትርጉም ክፍል፣ ዘመናዊ ዲጂታል መጻሕፍት ማከማቻ፣ የጋዜጣዊ መግለጫ መስጫ ክፍል፣ ከውጭ የሚመጣን ድምፅ ሙሉ በሙሉ መከላከል የሚችል አሠራር፣ ዘመናዊ የሙቀትና ቅዝቃዜ ማስተካከያ አየር መቆጣጠሪያ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የዕይታ ስክሪኖች የተገጠሙለት በመሆኑ የዘመኑ ግብዓቶች የተሟሉለት መሆኑ ተገልጿል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም 16 ሰዎችን በአንዴ መጫን የሚችሉ ሁለት የሰው ማደያ ሊፍቶች፣ ለ90 ሰዎች የሚሆኑ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች፣ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃን ያማከለ ሀገር በቀል ዕፅዋት ልማት፣ የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት እና ከ300 በላይ መኪናዎችን በአንዴ ማቆም የሚችል ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራ ተዘጋጅቶለታል።
የዕለቱ ከፍተኛ መርሐ ግብር የተከናወነው ከጉብኝቱ መልስ ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ለሥልጠናው ተሳታፊዎች እጅግ ታሪካዊና አባታዊ የሆነ ቃለ ምዕዳንና መመሪያ አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው፤ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተሠማሩበት አገልግሎት ሁሉ ሳይታክቱና ሳይሰለቹ በርትተው እንዲሠሩና ቤተ ክርስቲያናቸውን በጽናት እንዲያገለግሉ አጥብቀው አሳስበዋል። በተለይም የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ዋነኛ ዓላማ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ መልእክት፣ ታሪክና ሥርዓት ለምዕመናን ያለምንም መቆራረጥና ሳይዛባ በትክክል ማድረስ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው፤ ኃላፊዎቹ በዕውቀትና በታማኝነት ተጋድሏቸውን እንዲወጡ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል። በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለአህጉረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች ለቀጣይ የሥራ ዘመናቸው ስኬትና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚሆን ሰፊ ጸሎትና መንፈሳዊ ቡራኬ በመስጠት መርሐ ግብሩን በታላቅ ክብር አጠናቀዋል።