የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ለመንበረ ፓትርያርክና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዘመናዊ ኮምፒውተር በስጦታ አበረከተ።
ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ምብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ሰባት ደራጃቸውን የጠበቁ ኮምፒወተሮች በስጦታ አበርክተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው እንደተናገሩት መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ ለዚያ የሚያግዙ አምስት ኮምፒውተሮች፣ለቅዱስ ሲኖዶስ ሁለት ኮምፒውተር በአጠቃላይ ሰባት ኮምፒውተሮች በስጦታ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት “በጠቅላይ ቤተክህነት ብዙ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከልማት ሥራዎች በተጓዳኝ መጻሕፍቱ፣ የተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ዲጂታል እየተደረጉ ነው፤ ሥራ ሲሠራ መተጋገዝ የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ስላደረጉልን እገዛ እናመሰግናለን በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ባለሙያ ዲያቆን ሙሉዓለም ዐሥራት እነዳብራሩት “ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተለያዩ ዘርፎች ትኩረት በመስጠት ልማቶችን ያከናውኑ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የቤተክርስቲያን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚያጠናክሩ ከዚህም በተጨማሪ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ዲጂታል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት፡፡” ብለዋል፡፡ ባለሙያው አክለውም “ቤተክርስቲያን በርካታ የመረጃ ሀብት ያላት መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ መረጃዎቿና ዕውቀቶቿ በአግባቡ ተደራጅተው ያሰተቀመጡ በመሆናቸው፤ እነዚህን መረጃዎች ማስተዳደር የሚቻልባቸው አሠራር ለመዘርጋት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የዲጂታል ሥራዎች ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ አቋቁሞ በሥራ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
እነዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የዲጂታል ሥራዎች ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ በመሆናቸው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ደረጃቸውን የጠበቁ ኮምፒውተሮችን ድጋፍ አድርገውልናል፤ልማት ኮሚሽን ያደረገው ትብብርና እገዛ በጣም ትልቅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድጋፎች ማግኘታችን የጀመርነውን ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ለማምጣት የሚያግዙ ስለሆኑ ሌሎችም አካላት ይህን ዓላማ ቢያግዙ ቤተክርስቲያን አሁን ያለችበትን መንፈሳዊ አገልግሎት በተሻለና ዘመኑ በሚጠይቀው ደረጃ ለማገልገል ዕድል ይሰጣታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/