የሲኤምሲ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ካቴድራል ተብሎ ተሰየመ።
ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ምበአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር የሚገኘው ታላቁ ደብረ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ዕለት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ካቴድራል ተብሎ ተሰይሟል።
ቤተ ክርስቲያኑ ላለፉት ዓመታት ለአካባቢው ምዕመናን ታላቅ የመንፈሳዊ አገልግሎት ማእከል በመሆን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ስፋት፣ የማኅበረሰቡ ቁጥር ማደግ፣ እንዲሁም የሕንጻውና የአደረጃጀቱ ታላቅነት አሁን ላይ የካቴድራልነት ማዕረግን ለመቀናጀት አብቅቶታል።
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሥፍራው ተገኝተው ሕዝበ ክርስቲያኑን የባረኩ ሲሆን፣ የደብሩን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ልዩ መመሪያና ቡራኬ ሰጥተዋል ።
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስበከት ሊቀ ጳጳስ ሀዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፤ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስበከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ምህርት አባ ገብረመድኅን ንጉሤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መልአከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ የካቴድራሉ አስተዳዳሪን ጨምሮ የገዳማት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና ምዕመናን ተገኝተዋል።
ይህ የካቴድራልነት ስም መጠሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የአገልግሎት ስፋትንና ለወጣቱ እንዲሁም ለታዳጊው ትውልድ የሚሰጠውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ኃላፊነት የሚጥል ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።
ይህ ታሪካዊ ዕለት በደብሩ መዝገበ ታሪክ ላይ በደማቅ ቀለም የሚጻፍም ይሆናል ሲሉ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ ገልጸዋል።
በዕለቱ አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡት ዶክተር ቀሲስ ኢንጂነር ጌታቸዉ ፈለቀ የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ሲሆን ቤተክርስቲያኑ አሁን ያለበት ደርጃ ላይ ለማድረስ 300 ሚሊዮን ብር መውጣቱን ጠቁመው ፤ ደብሩ ሰፊ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል ።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/