ልዩ ምስጋና
በየዓመቱ የሕዝብ ግንኙነት ሥራችንን ክፍተቶች ለይተን አቅማችንን የምናጎለብትበትን ሥልጠና በመምሪያችን አዘጋጅነት እንደምንሰጥ ይታወቃል።በዚህ ዓመትም ያዘጋጀነውን ሥልጠና በውጤታማነት አከናውነናል።ከሥልጠናው ያገኘናቸውን ግብዓትች አሰባስበን፣በአቋም መግለጫችን ያካተትናቸውን ነጥቦች ቀምረን፤ የቀጣዩ ዓመት ሥራችንን የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይተንና ባዘጋጀነው ዕቅድ አካተን የመጪውን አዲስ ዓመት ሥራችንን በስኬትና በድል ለመቋጨት በብርቱ እንደምንሰራ የሥልጠናችን ውጤት አመላክቶናል።
ሥራዎቻችንን ለባረከልን፣በስኬት እንድንጓዝ ላደረገን የቤተክርስቲያን አምላክ ዘወትር ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ለሥራዎቻችን ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉልን ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያለንን ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና እናቀርባለን።
በየዓመቱ በምናካሒደው የአቅም ግንባታ ሥስልና ላይ ዕውቀታችሁን ያለ ስስት በመለገስ ሁሌም ከጎናችን ለምትቆሙ ውድ አሰልጣኞቻችን፣እግዚአብሔር አምላክ ረጅም ዕድሜና መልካም ጤንነትን ይሰጣችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎትና ምኞታችን መሆኑን በአክብሮት ስንገልጽላችሁ ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል።
አሃዱ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የሥልጠናችንን ሙሉ ወጪ ባይሸፍንልን ኖሮ ይሄን የመሰለ ሥልጠና ለማሳካት አንችልም ነበርና ለአሃዱ ባንክ አመራሮችና ሰራተኞች ከፍ ባለ ትህትና ምስጋናችን ይድረሳችሁ እንላለን።
እኛ ያለንን አቅም ተጠቅመን ቤተክርስቲያንን የሚጠቅም ሥራ መሥራትና በውጤት መገለጥን ተቀዳሚ መርሐችን አድርገን አገልግሎታችንን እናሳልጣለን።የቤተክርስቲያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሥራችንን ስለሚባርክልንና ውጤታማ ስለሚያደርገን ዘወትር እናመሰግነዋለን።በስልጠናው ላይ በትጋት የተሳተፋችሁ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በሙሉ በሰላም ወደየ አህጉረ ስብከታችሁ እንድትመለሱ መልካም ምኞታችንን እንገልጣለን።
ሊቀ ሥዩምን እስክንድር ገብረክርስቶስ
የጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ኃላፊ
ሐምሌ፲፪ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም