ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ወገን እናት እንጂ የቡድኖች መጠቀሚያ ልትሆን አይገባም ይበቃልን እንበል!” ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕነታቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከገዳማትና አድባራት የአገልግሎት መሪዎች ጋር ባደረጉት የትውውቅ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው አባታዊ ቡራኬና የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ይነበባል።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች
ክቡር መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች
የሁሉም ክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በሙሉ፦
ከሁሉ አስቀድሜ የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ሁላችንንም በያለንበት ጠብቆና አቆይቶ የእመቤታችን ሱባዔ በሰላምና በፍጹም ፍቅር መንፈሳዊ አገልግሎታችን አቀን የዛሬውን ዕለት ያሳየንና ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በቸርነቱ የሚጠብቃት የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተባረከ ይሁን።
አልቦ ጻድቅ ወአልቦ ጠቢብ ወአልቦ ዘየኃሥሦ ለእግዚአብሔር ሮሜ 3፥11 የሰው ልጆች ሁሉ ከተለያየ ሀገርና ቋንቋ ከተለያየ የሰው ዝርያ (ነገድ) የተገኘን እንደመሆናችን መጠን በቋንቋ፣ በቀለም፣ በአመጋገብ፣ በአለባበስ፣ በባህል፣ በአስተሳሰብ ጭምር ልዩነት እንዳለን ከሁላችሁም የሚሰወር አይደለም፡፡
ይሁን እንጂ ከልዩነታችን ይልቅ አንድ የምንሆንበትና የምንመሳሰልበት ነገር ጉልህ ሆኖ እንደሚታይ ከቅዱሳት መጻሕፍት ገለጻ መረዳት እንችላለን።
በመግቢያው በግዕዝ ቃል የተናገርኩት የሐዋርያው ቃል በአማርኛ ስናዳምጠው እንዲህ ይላል “ጻድቅ የለም፤ አንድ ስንኳ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል” ሮሜ ምዕራፍ 3 ቁጥር 11። “በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል ቸርነት የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም” ብሎ መዝግቦልናል ሮሜ ምዕራፍ 3 ቁጥር 12። ምክንያቱም ከአዳምና ከሔዋን ዘር
በመወለድና በሠራነው ኃጢአት ሁላችንም እኩል በአንድነት በአንድ አንቀጽ ተከሰናል።
በሌላም መልኩ ስናየው እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ለመላክ የተገደደበት ኃጢአታችን እንጂ ቅድስናችን አይደለም። ከዚህም መረዳት ያለብን ሁላችንም ያስፈለገን አንድ መድኃኒት እንጂ የተለያየ አለመሆኑን ገላጭ ነው።
ይህን እውነታ በጥልቀት የተረዳው ሌላው ሐዋርያ “ኃጢአት የለብንም ብንል ግን ራሳችንን እናስታለን የቀና ነገርም በኛ ዘንድ የለም ኃጢአታችንን አምነን ብንናገር ግን ኃጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ የታመነ ነው ቸርም ነው ከበደላችንም ሁሉ ያነጻናል” (1ኛ ዮሐ ምዕራፍ 1 ቁጥር 9) አሁን እንግዲህ ከነዚህ ኃይለቃሎች ይቅር መባል፣ ትላንትን መርሳት ከውድቀት መነሣት ወደ ክብር መመለስ እንደሚቻል በመጽሐፍ ከተመዘገበው እውነታ መማርና መረዳት እንችላለን፡፡
ለመልዕክቴና ለዕለቱ ተስማሚ ይሆናል በማለት ለመግቢያ ይህን ካልኩ ለዛሬ መሰባሰባችን ምክንያት የሆነችን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የጥንታውያንና የታሪካውያን አበው እምነት ማኅደር፤ የሀገራችን ኢትዮጵያ መንፈሳዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊነት መሠረት እንዲሁም የቅርሶቿ ባለቤትና ቀደምት ተጠሪ ናት።
ለዘመናት የሀገራችንን አንድነት ጠብቃ የትምህርትና የስልጣኔ ብርሃንን አብርታ የሕዝብን ግብረገብነትና ፍቅር ኮትኩታ ዛሬ ላይ ያደረሰች ታላቅና ብሔራዊ ተቋም በመሆኗ የልባችን ኩራት ናት፡፡
ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎቷን
እያሰፋችና እያሳደገች ያለችበት ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ከዘመኑ ሥልጣኔ ጋር የበቀሉ የቴክኖሎጂ መስፋፋቱን ተንተርሰው የመጡ በርካታ መልዕክት ማስተላለፊያዎች ከፊቷ ተደቅነው ፈተና ሆነውባታል፡፡
ውጫዊ ፈተናዎች የወንጌልን ትምህርት ለማዳከም የሚደረጉ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጫናዎች የሰላም እጦትና የምዕመናን መበታተን ሲሆን፣ ውስጣዊ ፈተናዎች ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ዘመኑን የዋጀ የሥራ አመራር
ሥርዓት ማነስ፣ የንብረትና የሀብት ማኔጅመንት ክፍተቶች እንዲሁም የአገልጋዮች አቅም ግንባታ ማነስ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በጊዜ ሂደት በተከሰቱ የአስተዳደር ብልሹነቶች በሙስና፣ በብሔርተኝነትና ሕጋዊ አሠራርን ባልተከተሉ አካሄዶች ምክንያት ዛሬ ላይ ታላቋ ቤተክርስቲያናችን በተለይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ሥራ አፈጻጸም ላይ በተለያየ መልኩ የብዙዎች መነቀፍያና የማኅበራዊ ሚዲያ አፍ መፍቻ ሆና መፍትሔ የምትፈልግበት ተቋም ሆናለች።
ይህ ሁኔታ የእያንዳንዳችንን ልብ የሚሰብርና ሊቀጥል የማይገባው የአንድ ወቅት ታሪክ ሆኖ ማለፍ ያለበት አሳዛኝ ምዕራፍ ነው ዛሬ ይሄንን ለሰሚው ግራ የሆነ ደስ የማይል ምዕራፍ በይፋ የምንዘጋበት በመግቢያ ጥቅሴ እንደተገለጸው ማንም ያልበደለ ስለሌለ በንስሐና በአዲስ መንፈስ የምንነሣበት ቀን ነው።
ቤተክርስቲያናችን ከተደቀኑባት ችግሮች አውጥተን የትናንት ታላቅነቷንና ክብሯን የመመለስ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለብን በመሆኑ ይህንን የለውጥ መስመር እንዲመሩልን ክቡር መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርገን ሾመናል፡፡
ተሿሚው ወንድምና ልጃችን ወደፊት በሚያከናውኗቸው ተግባራት ከብሔርና ከቡድን አሠራር ነጻ የሆነ መዋቅር ቤተክርስቲያንን ብቻ ማዕከል ያደረገ አድሏዊ ያልሆነና እውነተኛ የመንፈስ ቅዱስ ሀሳብን በአሠራር በመዘርጋት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና ልዕልና በማክበር የበላይ አካል መመሪያና ለሀገረ ስብከቱ የተሰጠውን ደንብ ጠብቀው በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር የፋይናንስና ንብረት አስተዳደሩን ግልጽ፣ ዘመናዊና ቁጥጥር የሚደረግበት በማድረግ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ፈጽመው እንደሚያጠፉ ትልቅ ተስፋና አደራ ጭምር ጥለንባቸዋል፡፡
ማዕከላዊነት ላይ የተመሠረተ የአሠራር ሲስተም በመዘርጋት አዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅና አመራራቸው ሀገረ ስብከቱን ነጻ በሆነ መንገድ ያለምንም ማማለጃ ማስተዳደር አለባቸው ቤተክርስቲያን የሁሉም ወገን እናት እንጂ የቡድኖች መጠቀሚያ ልትሆን አትችልም ይበቃል ብለን ሀገረስብከቱን ከገባበት የስም መጥፋት አጣብቂኝ ማላቀቅ ጊዜ የሚሰጠው ሆኖ አላገኘነውም፡፡
በሀገረ ስብከቱ በየጊዜው የሚነሣውና የሚስተዋለው ሙስናና ብልሹ አሠራርን ማስወገድ የቤተክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ከብክነት በመጠበቅ የቀደመውን ስም ማደስ ቀደምት አባቶቻችን ቤተክርስቲያንን ከምንም አይነት የአስተዳደርና የሞራል እድፍ ጉድፍ ነጻ አድርገው ቅድስናዋን ከሙሉ ክብሯ ጋር እንዳስረከቡን ሁሉ ዛሬም የታጣብንን ታማኝነት የተበላሸውን ስም አድሰን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ታላቅ አደራ በዛሬው ዕለት ጥለንባችኋል፡፡
ፍትሕና መልካም አስተዳደር በሀገረ ስብከቱ ሰፍኖ የሊቃውንት፣
የካህናትና ሠራተኞች አበሳ የሚያበቃበት የበደል ድምጽ የማይሰማበት እኩልነት የሚሰፍንበት አሠራር እንደሚቀየስ እምነቴ ጽኑ ነው።
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች በየክፍላተ ከተማው የምትገኙ ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የሰበካ ጉባኤ አባላትና መላው ካህናትና ሠራተኞች ተሿሚውን ዋና ሥራ አስኪያጅ በመደገፍ ከጎናቸው በመቆም እና ብልሹ አሠራርን በመታገል ሀገረ ስብከቱ ወደ ቀደመ ክብሩና ስሙ እንዲመለስ የየድርሻችሁን እንድትወጡ አባታዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ለአዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅና ለአመራራቸው ጥበብንና ብርታቱን ይስጣችሁ ቤተክርስቲያናችንን በሰላምና በቅድስና ይጠብቅልን።
“በደመወዛችሁ ኑሩ እንጂ በማንም ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም አትቀሙ፤ አትበድሉ” (ሉቃስ 3:12)
ነሐሴ ፲፱/፳፻፲፰ ዓ/ም
አባ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service