በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የተመሠረተው “ዝክረ ነዳያን ዘአበዊነ” የበጎ አድራጎት ድርጅት ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የ700,000 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም
ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ /Hamere Tewahedo Media
አዳማ ኢትዮጵያ
በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክና የግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራው የ“ዝክረ ነዳያን ዘአበዊነ” የበጎ አድራጎት ድርጅት በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ለሚመራው ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ ለደቀ መዛሙርቱ ለምግብ የሚሆን ሰባት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል እንዲሁም የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ እንደተናገሩት “ኮሌጁን ወደፊት ወደ ዩኒቨርሲቲ ከፍ ለማድረግ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው ብፁዕነታቸው ላደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናቸውን” አቅርበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክና የግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም “ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ለኮሌጁ በርካታ ሥራ እየሠሩ ናቸው፡፡ የብፁዕነታቸው ድካም በጣም ትልቅ ነው፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጁ ከተለያየ ክፍለ ሀገር የመጡ ደቀ መዛሙርትን የሚማሩበት ታላቅ ቦታ ነው፡፡ ዝዋይ ቀደም ሲልም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ጳጳሳት የተገኙበት ቦታ በመሆኑ እገዛ ሊደረግለት እንደሚገባ” አስረድተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አክለውም ለመጀመሪያ ጊዜ በ“ዝክረ ነዳያን ዘአበዊነ” የበጎ አድራጎት ድርጅት ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው ወደፊትም በቀጣይነት ኮሌጁን እንደሚረዱ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥራ አመራር (Leadership) የትምህርት ዘርፉ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ መልካም ፈቃድ በሥራ አመራር (Leadership) የትምህርት ዘርፉ እንዲያስተምር ባቋቋመው መሠረት ከመላው አህጉረ ስብከት የሚመጡ ደቀመዛሙርትን ከ፳፻፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ሲያስተምርና ሲያስመርቅ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፤ከዚህም በተጨማሪ የአብነት ትምህርትም በስፋት የሚሰጥበት፣ የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎች የሚሰጥበት ቦታ ነው፡፡