የደብረ ታቦር በዓል በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ምየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ከምታከብራቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዓበይት በዓላት አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በተለምዶ ቡሄ በመባል ይታወቃል፡፡
በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የገዳሙ አገልጋዮችና እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የደብረ ታቦር በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል /ማቴ. ፲፯፥፩፤ ማር.፱፥፩፤ ሉቃ.፱፥፳፰/፡፡ በዚህ በዓል መለኮታዊ ክብሩ፣ የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት ይተረጎምበታል፡፡
የገዳሙ የደብረ ታቦር በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት በዓሉ ሲከበር ዘንድሮ ለ53ኛ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “የተሰባሰብንበት ዋና ዓላማው የደብረ ታቦርን በዓል ለማክበር ሲሆን የበዓሉ አከባበር ቀደም ባሉት ጊዜያት በገዳሙ ይኖሩ በነበሩ ጥቂት ዲያቆናትና የመነኮሳት አርድእት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በየዓመቱ በዳቦና ሻይ ከማክበር ተነሥቶ ፈቃደ እግዚአብሔር ተጨምሮበት ለበርካታ ዓመታት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህ ታላቅ በዓል መከበር ከጀመረ 53ኛ ዓመቱን” ይዟል፡፡
ሪፖርቱ አያይዞም በገዳማችን ይህ በዓል ሲከበር ተመሳሳይ ዓላማ ቢኖረውም ነገር ግን ከዚህም ባለፈ በገዳሙ የነበሩ አባቶችና ወንድሞች በተለያየ የሕይወት አጋጣሚ ከገዳሙ ሲወጡ በዚያው ርቀው እንዳይቀሩ ይህንን ገዳም እንደራሳቸው ቤት እንዲመለከቱ ለማድረግም ጭምር ሲሆን በፍቅር ይህን በዓል ሲታደሙ ከአዲሱ ትውልድ ጋር ለመተዋወቅና ለመቀራረብ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “ይህ በዓል በቤተክርስቲያናችን ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው የከፍታ በዓል ነው፤ ከፍ ያሉ ዝቅ፣ ዝቅ ያሉ ከፍ ያሉበት በዓል ነው፡፡ ሕያዋን ሙታን የተገናኙበት፣ ሙሴና ኤልያስ በመካከላቸው ሰፊ ዘመናት ያላቸውን እግዚአብሔር ያገናኘበት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ ያዕቆብና በዓል ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ሰውን እንደሚያገናኝ እናያለን፡፡ ይህም ቤተክርስቲያን የተለያዩ ሰዎችን በአንድነት እንደምታገናኝ የሚያሳይ ነውና በሌላ በኩል ይህ በዓል በአብነት ትምህርት ቤት የተማሪ በዓል ይባላል፤ ተማሪዎች ለምነው ስኮላርሺፕ የሰጣቸውን ሕዝብ የሚመግቡበት፣ የራሳቸውን ፍቅር ያሳዩበት በዓል ነው፡፡” ሲሉ ገልጻዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ባስተላለፉት መልእክት “በዛሬው በገዳማችን በሚከበረው በዓል ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ስለተገኙ አመሰግናለሁ፡፡ በዚህ ገዳም በቀደሙት ዓመትት በየዓመቱ ተማሪዎች የደብረ ታቦር በዓል ያከብሩ ነበር፡፡ ዛሬም የገዳሙ ዲያቆናት የቀደሙትን መሠረት በማድረግ ሰው አስተባብረው በጋራ የሚያከብሩት፡፡ እግዚአብሔር ሰላሙን ሰጥቶ በሰላም እንድናከብር ያደረገ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ የሰለላም በዓል ያድርግልን” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ለመግለጽ የታቦር ተራራን የመረጠው፤ ትንቢትና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱ፡- “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ወይሴብሑ ለስምከ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” /መዝ. ፹፰፥፲፪/ በማለት ነቢዩ ዳዊት ትንቢት ተናግሮ ነበርና ጌታም ብርሃነ መለኮቱን በታቦር ተራራ በመግለጹ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ ምሳሌው፡- ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ይኸውም መስፍኑ ባርቅ ሲሣራን በታቦር ተራራ ድል ነስቶታል /መሳ. ፬፥፬—፳፬/፡፡
የደብረ ታቦር በዓል በቤተክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ማሕሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው “በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርኩልህ” የሚለው መዝሙር በመዘመር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ተሰጥቶት ይውላል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት ሃይማኖትን የሚማሩ ናቸውና ለሐዋርያት ነገረ መለኮቱን የገለጠ አምላክ እንዲገልጥላቸው በዓለ ደብረ ታቦርን በተለየ ድምቀት ያከብሩታል፡፡ በዚህም መሠረት በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳምም በዓሉ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/