ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሱማሌ ክልል ጅግጅጋ እና የምስራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በምሥራቅ አርሲ አሰላ ከተማ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም
የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሱማሌ ክልል ጅግጅጋ እና የምሥራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዚህ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ሀገረ ስብከቱን እንዲመሩ መድቧቸዋል።
በዚሁም መሠረት ብፁዕነታቸው በም0ሥራቅ አርሲ አሰላ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ።
በአቀባበሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የደቡብ ምስራቅ ትግራይና ራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ እና የድርጅት ኃላፊዎች ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣የሀገረ ስብከቱ የልዩ ልዩ የክፍል ኃላፊዎች ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባ ገዳዎችና በጣም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸውና ብፁዓን አበው ሊቀነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያኑ ሲደርሱም ጸሎተ ወንጌልና ኪዳን ከተደረሰ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለብፁዕነታቸው የተዘጋጀ ደብዳቤ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦምና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ከተነበበ በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ በእልልታና በደስታ ብፁዕነታቸውን ተቀብሏል።
የደብሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ ያሬድ ዜማ ያቀረቡ ሲሆን በመቀጠልም ቅኔያት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቀርበዋል፡፡
የመታሰቢያ ስጦታዎችም ለብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ለብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተሰጥተዋል።
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦምና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት የዕለቱን ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የደቡብ ምሥራቅ የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባታዊ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ሥራንና ሠራተኛን ማገናኘት የሚችሉና ጠንካራ አባት በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገረ ስብከቱ የነበረውን ችግር በማየት ሀገረ ስብከቱን እንዲያሳድጉ መመደባቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም በእምነታችን ከጸናን ሁሉም ስለሚያልፍ መጸለይ አለብን ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ አለበን በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና አባታዊ ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ እንደ ቀደምትነቱ ብዙ ያልተሠራበት በመሆኑ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እንደሚሰሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሕዝቡ በቋንቋው መማር እንዳለበትና ሀገሩ እንዲለማ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ከታች ጀምሮ የተሰጣቸውን ሥራ ሁሉ በመሥራት የሚታወቁ በመሆናቸው አብሮ መሥራት ያሰጥተዋል።
በብፁዕነታቸው አባታዊ ቡራኬና ጸሎት መርሐ ግብሩ የተጠናቀቀ ሲሆን ለመንበረ ጵጵስናው ለሚሠራ ሕንጻ ፣ በጥምቀተ ባህር ግቢ ውስጥ G+6 ሁለ ገብ የሕንጻ የገበያ ማዕከል እንዲሁም ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ መሠረተ ድንጋይ ተቀምጠዋል ።
በተጨማሪም የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግና የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ታስቦ የተገነባ ሁለገብ ሕንጻ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳተ ቡራኬ ተመርቋል።