የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ ኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • መሠረታዊ መረጃዎች
      • ርእይ፣ ተልእኮ እና እሴቶች
      • ታሪክ
      • የአደባባይ በዓላት
      • ህግጋት
    • መዋቅር
      • ቅዱስ ሲኖዶስ
      • ሊቃነ ጳጳሳት
      • መምሪያዎች
      • አህጉረ ስብከት
      • ትምህርት ቤቶች
  • አስተምህሮ
    • አእማደ ምሥጢር
      • ምሥጢረ ሥላሴ
      • ምሥጢረ ስጋዌ
      • ምሥጢረ ጥምቀት
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን
    • ምሥጢራተ ቤተክርስትያን
      • ምሥጢር ጥምቀት
      • ምሥጢረ ሜሮን
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ንስሐ
      • ምሥጢረ ተክሊል
      • ምሥጢረ ክህነት
      • ምሥጢረ ቀንዲል
    • ልዩ ልዩ
      • ነገረ ድኅነት
      • ነገረ ማርያም
      • ነገረ ቅዱሳን
      • ነገረ መስቀል
      • ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው
  • አገልግሎቶች
    • ሐዋርያዊ ተልእኮ
    • ማኅበራዊ አገልግሎት
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • ምግባረ ሰናይ
  • መካናት
    • ቅዱሳት መካናት
      • አክሱም ጽዮን
      • ላሊበላ
      • ደብረ ሊባኖስ
      • ማውጫ
    • ቤተ መዛክርት
      • መንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ቤተ መዘክር
      • የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገስት በአታ ለማርያም ቤተ መዘክር
      • ማውጫ
    • የጉብኝት መረጃዎች
      • የጉዞ መረጃዎች
      • የሚጠበቅ ሥርዓት
  • ያግኙን
  • English Site
  • Menu Menu

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

January 26, 2023

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ እንዲሁም በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 3 አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያደርግ በተደነገገው መሠረት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ሕዝብና አሕዛብን፣ ሰውና መላእክትን፣ ፍጡራን እና ፈጣሪን ይልቁንም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ልዩነት አጥፍቶ የሰው ልጅ ሁሉ በቋንቋ፣ በቀለምና በጐሣ ሳይከፋፈሉ በአንድነት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ የተወለዱ በማየ ገቦ የተጠመቁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑ ልዩነት የሌለባትን ዘለዓለማዊት መንግሥተ እግዚአብሔር እንዲወርሱ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የተነሣባትን ፈተና ሁሉ አልፋ ከእኛ ዘመን ደርሳለች፤

ምንም እንኳ ከቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ከኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በጐሣና በቋንቋ የመለየት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንግዳ ክስተት ቢሆንም ቤተ ክርስቲየን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጠባይዋ በተለየ፣ ታሪኳንና ሥርዓቷን በማይመጥን፣ ከሕግ መንፈሳዊ፣ ከሕግ ጠባይአዊ እና ከሕገ አእምሮ በወጣ መልኩ የደረሰባት ጥቃት፣ እና የመፈንቅለ ሲኖዶስን ተግባር ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ አሳዝኖታል፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ውስጥ ለሀገር አንድነት፣ ለፍትሕ፣ ለጥበብ፣ ለሕዝብ ትስስር፣ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለጤና፣ ለሥነ-ምግባር መሠረት እና ዐምድ፤ ምሰሶ እና ማገር ሆና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈራች፣ የተከበረች እና የተወደደች፤ ዕሴቷ እና ዕምቅ የዕውቀት ሀብቷ በምሁራን የታወቀ፣ በትምህርተ ዓለም ሳይቀር የተቀረጸ፤ በእውነተኛ ሊቃውንት የተመሠከረ፣ ቅርሶቿ የተመዘገቡላት ስትሆን፤

በቅርቡ ራስዋ በሾመቻቸው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ከፍተኛውና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲወጡ አደራ በተሰጣቸው ሊቃነ ጳጳሳት መሠረተ እምነትን፣ ሃይማኖታዊ ቀኖናን፣ የአስተዳደር ሥርዓት ሁሉ በጣሰ፣ መንገድ በማኅበረሰብ ዕድገትና አስተዳደር ውስጥ ከሕዝብ ጋር የቆመች፣ ከፖለቲካ የጸዳች መንፈሳዊና ሕዝባዊት ተቋምነቷን በመካድ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊት፣ ተቋምን የመናድና መዋቅሯን የማፍረስ ተግባር ተከናውኗል፡-

በዚሁ መሠረት፡-

ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጡ ወረዳ ከወሊሶ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አሮ ባለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን እጅግ አሳዛኝ እና ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፤ ሕገ ወጥ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አስመልከቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አስቸኳይ የምልዐተ ጉባዔ አድርጓል፤

ቅዱስ ሲኖዶስም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ መላው አህጉረ ስብከት፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ፣ የሊቃውንተ ጉባኤ፤ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፤ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የወጣቶች እና የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፤ የምእመናን እና አገልጋዮች ኅብረት፣ ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በደብዳቤ፣ በሚዲያ እና በአካል ከሰጡት ምክረ ሐሳብ እና የአቋም መግለጫ በመነሣት፤
በሀገር ውስጥ እና በውጪው ዓለም የሚገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወዳጆች፣ በተለይም የግብጽ እስክንድርያ ኮፕቲክ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ፓትርያርክ ውጭ የሚደረግ ሢመትን እንደማይቀበሉና ዕውቅና እንደማይሰጡ በላኩት የአቋም መግለጫ፣ የኤርትራ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን፣ እና የሌሎች አኀት ኦርቶዶከስ አብያተ ክርስያናት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ዓለም አቀፍ መንፈሳዉያን ተቋማት፣ የልማት እና የበጎ አድርጎት አጋር ድርጅቶች፤ ድርጊቱን በማውገዝ የማይቀበሉት መሆኑን የአቋም መግለጫ በመላክ ባሳዩት አጋርነት፤
አስቀድሞ እንደተገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈተና የኖረችበት ጊዜ እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍትና የታሪክ መዛግብት ሲመሰክሩ በዘመነ ሐዋርያት ቢጽ ሐሳውያን፣ በዘመነ ሊቃውንት የተለያዩ መናፍቃን፣… በየጊዜው እየተነሡ ሲፈታተኗት ኑረዋል፡፡ አሁንም በግልጽ እንደሚታየው ከውጭም ከውስጥም በተደራጁ ምንደኞች በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡

ለዚህም ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሶዶ ዳጩ ወረዳ፣ ሀሮ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአባ ሳዊሮስ መሪነት እጅግ አሳዛኝ ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፣ ሕገ-ወጥ፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አንዱ ሲሆን፤ በአባ ሳዊሮስ መሪነት የተፈጸመው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ፳፮ መነኰሳትን ከቀኖና የወጣ ሢመት በመስጠትና ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ በመመደብ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ ሃይማኖትን የሚከፋፍል፤ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት … የሚያጋጭና ደም የሚያፋስስ ፀጥታን የሚያናጋ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝሟል፤ በመሆኑም፤

– ከላይ እንደተገለጸው ሐዋርያት በሦስተኛው ቀሌምንጦስ በሃያ አምስተኛው አንቀጽ “በአውራጃው ሁሉ ያሉ ኤጲስ ቆጶሳት አለቃቸው ማንም እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ አለቃ ያድርጉት፤ ያለ ፍቃዱ ጥቃቅኑንም ደጋጉንም ሥራ ምንም ምን አይሥሩ፤ እርሱም ዳግመኛ ኤጲስ ቆጶሳቱ ሳይፈቅዱ ደጋጉን ሥራ አይሥራ ጥቃቅኑን ቢሠራ እዳ የለበትም፡፡ ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ ሁነው በአንድነት ይኑሩ” ብለው ወስነዋል፡፡ እነዚህ ሕገ ወጥ አካላት ይህን የሐዋርያት ቀኖናን በመሻራቸው፡፡

– ሁለተኛም በአርባ አራተኛው አንቀጽ “ሊቀጳጳሳት (ፓትርያርክ) ኤጲስ ቆጶሳት በተሾሙባቸው አገሮች የሚሠሩትን ሥራ፣ የሚያዙትን ትእዛዝ ይመርምር፡፡ የማይገባ ሥራ ሠርተው፣ የማይገባ ትእዛዝ አዝዘው፣ ቢያኝ ለውጦ የተገለጸለትን ትእዛዝ ይዘዝ፡፡ እርሱ ለሁሉ የሹመት አባታቸው ነውና፤ እነሱም ልጆቹ ናቸውና…” ብለዋል፡፡ ይህን ኢ-ቀኖናዊ ሥርዐተ ሲመት የፈጸሙት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ በአደባባይ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን እና የቅዱስ ፓትርያርኩን መብት በመጣሳቸው፡፡

– ሢመተ ክህነትን በተመለከተ “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር … እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም” (ዕብ 5፤4) እንደሚለው የእግዚአበሔር ቃል ከዲቁና ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ሹመት ድረስ ያለው ሹመት በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር መጠራቱን የሚጠይቅ ሲሆን እንኳንስ ለተሿሟዎች ለመራጮችና ለአስመራጮች በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስፈርት ያለው፣ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው መልእክቱ በሰፊው ገልጾታል፡፡

(ጢሞ.3፣10፣ ቲቶ፣ 1፣5-7 ፍትሕ መን አንቀጽ 4)

– ይህንም ቅዱሳን ሐዋርያት ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ በ3ኛው ቀሌምንጦስ “ኤጲስ ቆጶስ የሀገሩ ሰዎች፣ የሀገሩ ጳጳስ፣ ፈቅደውለት ይሾም፤ ቢገኙ ሦስት፣ ባይገኙ ሁለት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ሁነው ይሹሙት” ብለዋል፡፡ ይህም ቅዱስ ሲኖዶስ በሌለበት ሀገር፣ ፓትርያርክ በሌለ ጊዜ ምእመናን እንዳይበተኑ ተብሎ የሚደረግ ነው እንጅ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀመንበርነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን በመጋፋት የሚፈጸም ከሆነ ግን ይህን ቀኖና በሕገወጥ መንገድ ለተፈጸመ ድርጊት መጥቀሱ በቅዱስ ወንጌል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል እንደመናገር ተቆጥሮ የማይሠረይ ኃጢአት መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ (ማቴ.12፣30-32 ሉቃስ 12፣10፣ ማርቆስ 3፡28-29 1ኛ ጢሞ 1፣13) የእነዚህ ሰዎች ተግባር በሥራ ላይ ያለውን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ የመፈንቅል፣ የታላቋን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የመናድ፣ ሕጋዊ ተቋምን የማፍረስ ወይም የመናድ ተግባር በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዟል፣

– ሠለስቱ ምዕትም ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ በኒቅያ በጻፉት ቀኖና በዘጠነኛው አንቀጽ አንዱም አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾም ቢሻ፣ የሀገሩ ሰዎች ቢፈቅዱለት፣ የሀገሩ ጳጳስ ካልፈቀደለት ኤጲስ ቆጶስነት መሾም አይገባውም ይህን አፍርሶ ቢገኝ ሲኖዶስ ያወግዘዋል፤ ሹመቱም ይቀራል” ብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ወቅት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲየን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ስልጣን በመጋፋት በድፍረት ተፈጸመ የተባለው ሹመት አስቀድሞ በአበው ቅዱሳን የተወገዘ ነው፤

– ከዚህም ጋር ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት በሚፈጸምበት ጊዜ፣ ያለ ቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ማንም ወደ ቤተ መንግሥት እንዲሔድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይፈቅድም፡፡ ይህንንም የተላለፈ ቢኖር ከጳጳሳና ከኤጲስ ቆጶሳት ማንም ማን ሊቀጳጳሳቱ ሳይፈቅድለት ወደ ንጉሥ ቤት አይሒድ ወለኲሉ ዘዐለወ ዘንተ ሲኖዶስ ያወግዞ ይህን ትእዛዝ ያፈረሰውን ሲኖዶስ ያወግዘዋል” ተብሎ ስለተወሰነ ዛሬም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ውጭ የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ሕገወጥ በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘዋል፤

– በቀኖና ቤተ ክርስቲያን … ሰው ሁሉ ማዕርጉን ጠብቆ ይኑር እንጅ፣ አንዱ ወደ አንዱ ማዕርግ አይተላለፍ፤ ይህን የሠራነውን ሥርዐት ያፈረሰውን ሰው ሲኖዶስ ያወግዘዋል ተብሎ በተጻፈው መሰረት እነዚህ ሕገወጥ አካላት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘዋል፤

– በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 30 የአጲስ ቀጶሳት መሾም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ የመወሰን ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን የሚደነግገውን ክፍል በግልጽ የጣሰ በመሆኑ፤

– በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንዑስ ቁ.1 የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚፈጸመው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ብቻ እንደሚፈጸምና መደንገጉ፤

– በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 5 የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ሕግጋትንና ቀኖናን የሚያፋልስ ሊቀ ጳጳስ /ኤጲስ ቆጶስ/ ከአባልነት እንደሚሰረዝ በመደንገጉ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዟቸዋል፡፡
በአጠቃላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር በሕገ ሰብእም ሆነ በሕገ እግዚአብሔር ሚዛን የተወገዘ ከመሠረተ እምነት የተለየ፣ በአበው ቀኖና፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በአጠቃላይ ተቀባይት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ

1ኛ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 138 መሠረት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጩ ወረዳ ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ

፩ኛ. አባ ሳዊሮስ
2ኛ. አባ ኤዎስጣቴዎስ
3ኛ. አባ ዜና ማርቆስ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን 26 ኤጴስ ቆጰሳትን ሾመናል፤ ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለት በማኅህበራዊ እና በብሮድካስት ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ የተረጋገጠ በመሆኑ በዚሁ ድርጊታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ፤ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ ለይቷቸዋል፡፡

በመሆኑም፡-
ሀ. ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ፤

ለ. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡

ሐ. በነዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አውግዞ በለያቸው ግለሰቦች ይመሯቸው በነበሩ አህጉረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት በማከናወን ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ ብፁዐን አባቶችን

፩. ለደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት
፪. ለኬንያ፤ኡጋንዳ፤ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ሀገረ ስብከት
፫. ለኢሉ አባቦራ እና በኖ በደሌ ሀገረ ስብከት
፬. በሰሜን አሜሪካ ለሜኒሶታ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት
፭. ለጉጂ፤ምዕራብ ጉጂ እና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት
፮. ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም

በአባትነት የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመደቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ወስኗል፡፡

ይሁን እንጅ ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል፤

2. የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ ግለሰቦች አማካኝነት የኤጲስ ቆጶስነት ሺመት አግኝተናል፤ ተሸመናል እያሉ የሚገኙ 25 መነኰሳት በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል፡፡

3. ከነዚሁ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ጸጋዘአብ አዱኛን ከቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ ስብሰባ በፊት የቀኖና ጥሰቱንና ሕገ ወጥ አድራጎቱን በመረዳትና በመጸጸት ድርጊቱን በመቃወም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ባቀረቡት የይቅርታ አቤቱታ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታውን የተቀበላቸው ሲሆን እንደሳቸው ሁሉ ከላይ የተወገዙት 25 ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን እንገልጻለን

4. በዚህ ጸረ ቤተ ክርስቲያን እና ኢ-ቀኖናዊ ድርጊት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ እየኖሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወይም በቦታው በመገኘት የጥፋት ድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን በተመለከተ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተገቢውን ክትትልና አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ፤

5. ይህን ታሪክ ይቅር የማይለውን ሕገ ወጥ አድራጎት እና የቀኖና ጥሰት በሐሳብ፤ በገንዘብ እና በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ እና በማድረግ ላይ ያሉ ማናቸውም ተቋማት እና ግለሰቦች ከዚህ ሕገ ወጥ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያሳሰበ ይህ ባይሆን በሕግ አግባብ ተገቢው እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

6. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማህበራት እና ምእመናን እና ምእመናት ይህን ሕገ ወጥ አድራጎት ከመከላከል እና የቤተ ክርስቲያናችሁን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለዚህ ሕገ ወጥ አድራጎት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደረግ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከል ሥራችሁን እንድትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስምን ከፊትም ሆነ ከኃላ በመጨመር እና በመቀነስ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠቀም፤ ዓርማዋን፤ አድራሻዋን፤የአምልኮ እና የሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋያ ቅዱሳትንና አልባሳት እንዲሁም መጻሕፍት መገልገል የማይችሉ መሆኑ ታውቆ ይህንን ጉዳይ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በተጨማሪም ይህን ውሳኔ ተላልፈው በሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ተገቢውን ሕግ አግባብ ተከትሎ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለማት የሚያስፈጽም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች በመመደብ ተገቢውን ሁሉ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

8. አሁን የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ ዝርዝር ጥናት እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ አንድ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲሰየም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

9. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ከክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጀምሮ በየደረጃው ላሉት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲከናወኑ እና ይህ ውሳኔ ከሸኚ ደብዳቤ ጋር እንዲደርሳቸው ተወስኗል፡፡

10. ይህን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ክፍለ ዓለማት ለሚገኙ የቤተ ክርስቲኒቱ አገልጋዮች እና ምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መድረኮች እንዲካሔዱ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በማእከል የአህጉረ ስብከት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ታላቅ የንቅናቄ እና የግንዛቤ መድረክ እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

11. በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ መንግስታዊም ሆነ መነግስታዊ ያልሆነ ተቋማት፤ አኃት አቢያተ ክርስቲያናት፤ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፤ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት ጉባዔ እና ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ጉባኤዎች በሙሉ እነዚህ የተወገዙት ግለሰቦች የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ እና ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ ማናቸውም ግንኙነት በቤተ ክርስቲያኑቱ ስም እንዳያደርጉ በጽሑፍ አንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

12. እነዚህ ግለሰቦች ከሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ አንዱ እኩይ ተግባራቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እንደሆነ ማስመሰል ሲሆን ይኽ ተግባር ሃይማኖቱን የሚወድ፣ አባቶቹን የሚያከብር እና አስተዋይ የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ የማይወክል፣ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ያደረጉት ሕገወጥ የቀኖና ጥሰት መሆኑ እንዲታወቅ፤ በተጨማሪም ለሚያሠራጩት የሐሰት አሉባልታ ወደፊት ተገቢው መልስ እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

እስከ አሁን ድረስ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን በመሆን አጋርነታችሁን ያሳያችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የበኩላችሁን በመወጣት መግለጫ የሰጣችሁ ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም እያመሰገንን ለወደፊቱም በጸሎታችሁ እና በመልካም አጋርነታችሁ ከጎናችን እንድትሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

ጥር 18 ቀን 2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/decision-cover.jpg 332 720 tc https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/eotceth-logo2.svg tc2023-01-26 15:23:472023-01-26 15:54:26ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አዲስ የተሠራውን የለገዳዲ አንቀጸ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን መረቁ፡፡
  • የወጨ አንቀጸ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ሕንጻ በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
  • በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ምዕራፈ ሰማዕታት ወደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የተከናወነው የወንዝ ማስቀየስ ሥራ ተጠናቆ በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ተመረቀ።
  • በሸገር ሀገረ ስብከት የታነጸው የደብረ ሣህል ቅዱስ ገብርኤል አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጸሎተ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
  • ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሱማሌ ክልል ጅግጅጋ እና የምስራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በምሥራቅ አርሲ አሰላ ከተማ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • January 2026
  • December 2025
  • August 2025
  • July 2025
  • June 2025
  • March 2025
  • February 2025
  • January 2025
  • December 2024
  • November 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • July 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • April 2024
  • March 2024
  • February 2024
  • January 2024
  • December 2023
  • November 2023
  • October 2023
  • September 2023
  • August 2023
  • July 2023
  • June 2023
  • May 2023
  • April 2023
  • March 2023
  • February 2023
  • January 2023
  • December 2022
  • October 2022
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ሀገረ ስብከት በወቅታዊ የቤተክርስቲይን ወቅታው ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ Link to: ሀገረ ስብከት በወቅታዊ የቤተክርስቲይን ወቅታው ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ ሀገረ ስብከት በወቅታዊ የቤተክርስቲይን ወቅታው... Link to: የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቶ ባለ ፮ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። Link to: የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቶ ባለ ፮ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top