የወጨ አንቀጸ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ሕንጻ በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት፣ በለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የወጨ አንቀጸ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲስ ሕንጻ ግንባታው ተጠናቆ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
የምረቃ መርሐ ግብር ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ፣ የኩራ ጂዳ፣ የቡራዩ፣ የገፈርሳ፣ የጉጄ እና የመልካም ኖኖ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣የክፍለ ከተማው ዋና ጸሐፊ መጋቤ አእላፍ ስዩም ብዙአየሁ፣የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዕለቱ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፤ የቤተ ክርስቲያኑን ሕንጻ በአንድ ዓመት አጭር ጊዜ ውስጥ ሠርቶ ማጠናቀቅ መቻሉ ትልቅ በረከት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም “የመጀመሪያው ልማት እናንተ ናችሁ፤ እናንተ የክርስቶስ ሕንጻዎች ናችሁ። ስለዚህ ትውልድና ወጣቱ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤ ሕፃናትንና ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት ሰብስባችሁ በቅንነት ማስተማርና ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆኑ አድርጎ ማነጽ ይገባል” በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የደብሩ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለብፁዕነታቸው የቀረበ ሲሆን፤ የሕንጻ ቤተ መቅደሱን ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በማጠቃለያውም ቤተ ክርስቲያኑ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ፍጻሜ ሆኗል።