የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ ኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • መሠረታዊ መረጃዎች
      • ርእይ፣ ተልእኮ እና እሴቶች
      • ታሪክ
      • የአደባባይ በዓላት
      • ህግጋት
    • መዋቅር
      • ቅዱስ ሲኖዶስ
      • ሊቃነ ጳጳሳት
      • መምሪያዎች
      • አህጉረ ስብከት
      • ትምህርት ቤቶች
  • አስተምህሮ
    • አእማደ ምሥጢር
      • ምሥጢረ ሥላሴ
      • ምሥጢረ ስጋዌ
      • ምሥጢረ ጥምቀት
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን
    • ምሥጢራተ ቤተክርስትያን
      • ምሥጢር ጥምቀት
      • ምሥጢረ ሜሮን
      • ምሥጢረ ቁርባን
      • ምሥጢረ ንስሐ
      • ምሥጢረ ተክሊል
      • ምሥጢረ ክህነት
      • ምሥጢረ ቀንዲል
    • ልዩ ልዩ
      • ነገረ ድኅነት
      • ነገረ ማርያም
      • ነገረ ቅዱሳን
      • ነገረ መስቀል
      • ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው
  • አገልግሎቶች
    • ሐዋርያዊ ተልእኮ
    • ማኅበራዊ አገልግሎት
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • ምግባረ ሰናይ
  • መካናት
    • ቅዱሳት መካናት
      • አክሱም ጽዮን
      • ላሊበላ
      • ደብረ ሊባኖስ
      • ማውጫ
    • ቤተ መዛክርት
      • መንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ቤተ መዘክር
      • የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገስት በአታ ለማርያም ቤተ መዘክር
      • ማውጫ
    • የጉብኝት መረጃዎች
      • የጉዞ መረጃዎች
      • የሚጠበቅ ሥርዓት
  • ያግኙን
  • English Site
  • Menu Menu

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

March 30, 2023

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥር 14 ቀን 2015ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሕገወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር 18 ቀን 2015ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተከናወነው ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖና አስተዳደራዊ መዋቅር የጣሰ ሕገወጥ አድራጎት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በመወያየት ሕገወጡን ሹመት ያከናወኑትና ተሿሚዎችን በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት ከዲቁና ጀምሮ የነበራቸውን ማዕረገ ክህነት በሙሉ በመሻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባልነት አውግዞ መለየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በውሳኔው ውግዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በድርጊታቸው ተጸጽተው እና ከስህተታቸው ተመልሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት የሚሰጣቸውን ቀኖና ተቀብሎ ለመመለስ ዝግጁ ከሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የይቅርታ በር ክፍት መሆኑን በማሳወቅ መግለጫ የሰጠ ቢሆንም ግለሰቦቹ ከስህተታቸው ተምረው በይቅርታ እድሉ ከመጠቀም ይልቅ በሕገወጥ መንገዱ ቀጥለውና ውግዘቱን ጥሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው በሚያገለግሉባቸው አህጉረ ስብከት ላይ እርስ በርሳቸው በመመዳደብ እያደረጉት የነበረውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ መንግስት በሕግ የተጠላበትን ሕግን የማስከበር ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያናችንን ተቋማዊ ልዕልና እንዲያስከብርልን ከመግለጫም አልፎ በደብዳቤ ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አጥቶ በሕገወጥ መንገድ የተሾሙት ግለሰቦች በመንግሥታዊ የፀጥታ አካላት ታጅበው በኦሮምያ ክልል የሚገኙትን አህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በኃይል ሰብረው ተቋማቱን በመውረር ሀብትና ንብረት የተዘረፈ ሲሆን ይህም ሕገወጥ ድርጊት በሚከናወንበት ወቅት ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን አይጣስም፣ ሲኖዶሳችን አይከፈልም፣ ቀኖናችን አይደፈርም በማለት በጽናትና በአንድነት ድርጊቱን የተቃወሙት ምዕመናን፣ ወጣቶችና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ የሥራ ኃፊዎች በተለይም የሻሸመኔና አካባቢው ምእመናንና አገልጋይ ካህናት ለሞት፣ ለአካልና የሞራል ጉዳት፣ ለእስራትና እንግልት ተዳርገዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን እና ፈተናውን የማሳለፍ ሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በምሕረት አይኑ ተመልክቶ የመጣውን ፈተና ያስወግድልን ዘንድ በጾመ ነነዌ ለ3 ቀናት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ተከታዮች ማቅ ለብሰው በጸሎትና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እንዲያመለክቱ በወሰነው መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ተፈጽሞ በማያውቅ ሁኔታ እንኳንስ ልጆቿ ምእመናን ይቅርና እራሷ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የሀዘን መገለጫ የሆነውን ጥቁር ማቅ ለብሳ ከሀገር አቀፍም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀዘኗን ገልጣለች፡፡
የእናት ቤተ ክርስቲያንና የልጆቿ ምዕመናን እንባና ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ለውይይት ዝግ የነበረው የመንግስታችን በር ለውይይት ተከፍቷል፡፡ የደረሠብን የጉዳት ከፍተኛነት በሀገራችን መንግስታዊ ሚዲያዎች ዘንድ ቦታ ቢያጣም አለም አቀፍ ሚዲያዎችና የቤተ ክርስቲያናችን የሚዲያ ተቋማት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲደርስ በማድረጋቸው ችግሩን ከእኛም አልፎ በሁሉም አኃት አብያተ ክርስቲያናት፣ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች ሲቢክ ማህበራት ድርጊቱን በማውገዝ ለእናት ቤተ ክርስቲያናችን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ በዚህም በችግራችን ወቅት ከጎናችን ለቆሙት አካላት በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም በድጋሚ ከፍ ያለ ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡

በመጠቀልም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባመቻቹት የውይይት መድረክ በተወከሉ ብፁዓን አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በኩል በተደረገው መጠነ ሰፊ ውይይት መሠረት ባለ10 ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት በተደረሰው መሠረት ሦስቱ የቀድሞ አባቶች የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ መጥተው በቀድሞ በዓታቸው ተወስነው እስካሁን የቆዩ ሲሆን 20ዎቹ ተሿሟዎች ደግሞ በስምምነቱ መሠረት ለውሳኔው ተገዥ መሆናቸውን በመግለጽ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባቀረቡት መሠረት ውግዘቱ እንዴት ሊፈታ እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱን የቀኖና ቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢ በማድረግ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን እንደሚከተለው በአጭሩ ተገልጿል፡፡

ሀ. “ኢይክል ሰብእ ነሢአ ፀጋ ለሊሁ ወኢምንተኒ እመ ኢተውህበ ሎቱ እምሰማይ” ሰው ከእግዚአብሔር ካልተሰጠው በስተቀር እርሱ ራሱ ጸጋን ገንዘብ ማድረግ አይችልም” (ዮሐ. 3፣27) በማለት በቅዱስ ወንጌል እንደተነገረው የእግዚአብሔር ጸጋ ከላይ የሚሰጠው በቅንነት፣ በትሕትና፣ በትዕግሥትና በጸሎት በመሳሰለው እንጅ በሥርዓተ አልበኝነትና በሕገወጥ የድፍረት መንገድ የሚገኝ የእግዚአብሔር ጸጋ የለም፤ አልኖርም፤ አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡

ለ. ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር በከመ አሮን” እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብርን ለራሱ የሚወስድ የለም ሲል ክብረ ክህነትን በሚገባ ገልጿል፡፡ (ዕብ.5፡4) እንዲህም በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭና ቅዱስ ፓትርያርኩ በሌሉበት በድብቅ የተፈጸመው ሕገወጥ ሢመተ ክህነት ለሿሚውም ሆነ ለተሿሚው የእግዚአብሔርን ጸጋ በራስ ፈቃድ እንደመውሰድ ስለሚቆጠር ከፍተኛ የሆነ የዶግማ ጥሰት ተግባር ነው፡፡

ሐ. ከቅዱስ ቃሉ እንደተማርነው “ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሀ እግዚአብሔር – የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (መዝ.109፣10 ምሳ.1፣7) ይህንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት በማድረግ ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሀት – ለእግዚአብሔር በፍርሀት ስገዱ (መዝ.28፣2)

ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሀት – ለእግዚአብሔር በፍርሀት ተገዙ (መዝ.2፣11)

ንትነሣእ በፍርሀተ እግዚአብሔር – እግዚአብሔርን በመፍራት እንነሣ (ቅዳ.ማ) በማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እስከ እስትንፋሰ ደኃሪት መልእክቷን ዘወትር ታስተላልፋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመው ድርጊት ግን በከፍተኛ ድፍረትና በሕገወጥ መንገድ ከመፈጸሙና የሥልጣነ ክህነትን ክብር ከማጉደፉም በላይ ከውግዘትም በኋላ ከጥፋቱ ባለመማር ሕገወጥነትን እንደ ሕጋዊነት፣ ጥፋትን እንደ ልማት፣ ሐሰትን እንደ እውነት፣ የነፍስ ጥፋትን እንደ ነፍስ ማዳን ተቆጥሮ በልበሙሉነት የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አበያተ ክርስቲያናት በር በኃይል ተሰብሮ የመውረር ሕገወጥ ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ይህም ድርጊት ከውግዘት በኋላ በመሆኑ ሕገ እግዚአብሔርን እያወቁ ወደጎን በመተው የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ የዶግማ ጥሰት ነው፡፡

መ. ቅዱሳን ሐዋርያት ከወሰኗቸው የሕግጋት መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ 1 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ “ወአዘዝነ ከመዝ መዓርገ ሢመታት ለቤተ ክርስቲያን በአርአያ ዘበሰማያት የቤተ ክርስቲያናችን የሹመቶች መዓርግ በሰማያት ባለው አምሳል እንዲሆን አዘዝን” በማለት በንዑስ አንቀጽ 3 ላይ “ወንሕነ ንጌሥጽክሙ ከመ ይንበር ኲሉ ለለ አሐዱ አሐዱ እምኔክሙ ውስተ ዘተጸውዐ እምኀበ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ – ከእናንተ ሁሉ እያንዳንዱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በተጠራበት ተልእኮ ጸንቶ ይኖር ዘንድ እኛ እንመክራችኋለን በማለት እያንዳንዱ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ፀጋና ተልእኮ ጸንቶ ከሚኖር በቀር ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ባልተሰጠውና ባልተፈቀደለት በሕገወጥ መንገድ ሊሾምም ሆነ ሊሾም እንደማይገባው የሚያስተምረን አምላካዊ ቃል ነው፡፡

ሠ. ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ 20 ላይ “በእንተ ዘይሰየም በህልያን እመሂ ኤጲስ ቆጶስ አው ቀሲስ አው ዲያቆን ዘይእኀዝ መዓርገ ሢመት በሕልያን ይሰአር፤ ወይሰዐር ዘሤሞሂ ወይትመተር ለዝሉፉ እምሥርዐተ ክህነት፤ ወኢይሳተፍዎ ወኢበምንትኒ በከመ ረሰይክዎ ለሲሞን መሠርይ እምኀቤየ አነ ጴጥሮስ – መማለጃ በመስጠት ስለሚሾም ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሹመት መዓርግ ቢይዝ ይሻር፣ የሾመውም ይሻር ከክህነት ሥርዓትም እስከ መጨረሻው ይባረር፡፡ እኔ ጴጥሮስ ጠንቋዩ ሊሞንን እንዳደረግሁት በምንም ነገር አያሳትፉት (ሲኖ.ዘሐዋ.ክፍል 3 ቁጥር 20) በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ሥልጣነ ክህነትን ያለአግባብ የሰጠም ሆነ የተቀበለ አካል እስከመጨረሻው ድረስ ከሥርዓተ ክህነት ውጭ እንዲሆን አውግዟል፡፡ በማለትና ሌሎችንም ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዋቢ በማድረግ በሊቃውንት ጉባኤ የቀረበውን የውሳኔ ምክረ ሐሳብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአድናቆትና በአክብሮት ተቀብሎ ተወያይቶበታል፡፡

በመሆኑም ከላይ ቀኖና ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት አድርጎ ከቀረበው ምክረ ሐሳብና በቤተ ክርስቲያኒቱና በምዕመናን ላይ ከደረሰው ሞት፣ የአካልና የሞራል ጉዳት፣ እስራትና እንግልት አንጻር ውግዘቱ ሊነሣ የማይገባውና በሕግም የሚያስጠይቅ ሕገወጥ አድራጎት ቢሆንም አሁን በተከሰተው ድርጊት በአጭር ጊዜ ውስጥ በእናት ቤተ ክርስቲያን ላይ እና በተከታዮቿ ምዕመናንና አገልጋዮቿ ላይ ከደረሰው ከፍተኛ ጉዳት አንጻር ችግሩን በሆደ ሰፊነትና በይቅርባይነት መፍታት ካልተቻለ አሁን ያለው መከራና ችግር ይቀጥል ቢባል በቀጣይ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ እንዲሁም በምዕመናንና አገልጋዮቿ ሰላማዊ ጉሮ ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ የሆነ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ካሁን ቀደም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተገኙበትና በመቀጠልም ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት በተገኙበት በተደረገው ውይይት በተደረሰው 10ሩ የስምምነት ነጥቦች መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በስፋት ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

1. የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ በመምጣት እስካሁን ድረስ በበዓታቸው ጸንተው የቆዩት 3ቱም የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ላይ አስቀድሞ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፈው ውግዘት ከዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ ተነስቷል፡፡

2. ውግዘቱ የተነሣላቸው 3ቱም ሊቃነ ጳጳሳት ከዛሬ መጋቢት 21 ቀነ 2015ዓ.ም. ጀምሮ በቀድሞ የሊቀ ጳጳስነት ማዕረጋቸውና ስማቸው ማለትም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሊቀጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ሊቀጳጳስ ተብለው እንዲጠሩና አስቀድሞ ተመድበው ይሰሩበት በነበረው የሥራ ኃላፊነታቸው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

3. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በተደረገው ውይይት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ጥሪውን ተቀብለው ለስምምነቱ ተገዥ በመሆን በጽሑፍ ጥያቄያቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት 20ዎቹ የቀድሞ መነኮሳት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ የተላለፈው ውግዘት ከዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተነስቷል፡፡ ቀሪዎቹ 5ቱ ባለው ጊዜ ተጠቅመው ወደቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ እያሳሰበ ውግዘቱን በሚመለከት በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ታይቶ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

4. ውግዘቱ የተነሣላቸው 20ዎቹም የቀድሞ መነኮሳት አስቀድሞ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከዲቁና እስከ ቁምስና ባለው ማዕረገ ክህነታቸው እንዲያገለግሉ እና በምንኩስና ስማቸውም እንዲጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

5. 20ዎቹ የቀድሞ መነኮሳት የሥራ ምደባን በተመለከተ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በቀድሞው የሥራ መደብ ደረጃቸው እንዲመደቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመወሰን ዝርዝር ጉዳዩ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ አዟል፡

6. በተከሰተው ሕገወጥ ድርጊት መነሻነት ለቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ልዕልና ሲሉ ለሞት፣ ለአካልና የሞራል ጉዳት፣ ለእስራትና እንግልት እንዲሁም ለስደት የተዳረጉትን ምዕመናን፣ ወጣቶች፣ አገልጋይ ካህትና ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ያሉ የሥራ ኃላፊዎችን ጉዳትና መከራ እንዲሁም ችግሩን በሕግ አግባብ እንዲፈታና የቤተ ክርስቲያኒቱ መብትና ጥቅም እንዲከበር ሌሊት ከቀን በማገልገል ላይ የሚገኙትን የሕግ ባለሙያዎች ማህበር የሰጡትን ሙያዊ አገልግሎት ቅዱስ ሲኖዶስ ዘወትር በከባድ ሐዘንና ጸሎት ሲያስታውሰው የሚኖርና በቀጣይ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዛግብት ተመዘግቦ ለቀጣዩ ትውልድ መማሪያነት እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

7. ውግዘቱ የተነሣላችሁ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ አባቶችም በቀጣይ በፈጸማችሁት ድርጊት የተጎዳውን መላው ሕዝበ ክርስቲያን እና ክብሯ የተደፈረውን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁን ሊክስ በሚችል የትሕትና መንፈስ በማገልገልና ዳግመኛ ከእንዲህ ዓይነቱ ሕገወጥ አድራጎት በመራቅ የተጣለባችሁን ከፍተኛ ኃላፊነት በታማኝነት እንድትወጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

8. በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰውን ፈተና እንዲወገድና የቤተ ክርስቲያኒቱ መብትና ክብር እንዲጠበቅ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክላችሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት የውይይት መድረክ ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከታችሁ ሦስቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ እና ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል እና አቀራራቢ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በፍትሕ አደባባይ ክስ በመመስረት የደከማችሁ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር እና ችግሩን ለመላው ዓለም በማዳረስ ሰፊ ሥራ የሠራችሁ የሚዲያ ተቋማትን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰጣችሁት ታሪክ የማይረሳው አገልግሎት በእጅጉ ያመሰግናል፡፡

9. ምንም እንኳን አስቀድሞ ከክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ጋር በተደረገው ውይይትና ስምምነት መሠረት የታሰሩት ግለሰቦች በሙሉ እንደሚፈቱ ቃል የተገባ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎች በእስር ላይ የሚገኙ ስለሆነ መንግስት አስቀድሞ በገባው ቃል መሠረት ሁሉንም እስረኞች እንዲፈታልን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

10. በተከሰተው ችግር ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ላይ በኃላፊነት ተመድበው ሲሰሩ ቆይተው በችግሩ ምክንያት ተፈናቅለው የቆዩት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ያለምንም የፀጥታ ስጋት በምድብ ሥራቸው ላይ እንዲቀጥሉ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/favicon.png 169 151 tc https://eotceth.org/a/wp-content/uploads/eotceth-logo2.svg tc2023-03-30 15:19:012023-03-30 15:19:14ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አዲስ የተሠራውን የለገዳዲ አንቀጸ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን መረቁ፡፡
  • የወጨ አንቀጸ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ሕንጻ በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
  • በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ምዕራፈ ሰማዕታት ወደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የተከናወነው የወንዝ ማስቀየስ ሥራ ተጠናቆ በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ተመረቀ።
  • በሸገር ሀገረ ስብከት የታነጸው የደብረ ሣህል ቅዱስ ገብርኤል አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጸሎተ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
  • ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሱማሌ ክልል ጅግጅጋ እና የምስራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በምሥራቅ አርሲ አሰላ ከተማ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • January 2026
  • December 2025
  • August 2025
  • July 2025
  • June 2025
  • March 2025
  • February 2025
  • January 2025
  • December 2024
  • November 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • July 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • April 2024
  • March 2024
  • February 2024
  • January 2024
  • December 2023
  • November 2023
  • October 2023
  • September 2023
  • August 2023
  • July 2023
  • June 2023
  • May 2023
  • April 2023
  • March 2023
  • February 2023
  • January 2023
  • December 2022
  • October 2022
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ላለፉት ፯ ዓመታት ግንባታቸው የተጓተቱ ሁለት ህንጻዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሚያደርግ የውል ስምምነት ተፈረመ። Link to: ላለፉት ፯ ዓመታት ግንባታቸው የተጓተቱ ሁለት ህንጻዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሚያደርግ የውል ስምምነት ተፈረመ። ላለፉት ፯ ዓመታት ግንባታቸው የተጓተቱ ሁለት ህንጻዎች... Link to: በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተዋቀረው የትምህርትና ስልጠና ግብረ ኃይል ዐቢይ ኮሚቴ የሰባክያነ ወንጌል ስምሪት አከናወነ፡ Link to: በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተዋቀረው የትምህርትና ስልጠና ግብረ ኃይል ዐቢይ ኮሚቴ የሰባክያነ ወንጌል ስምሪት አከናወነ፡ በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተዋቀረው...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top