ሰኔ ፪ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
+++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሸገር ከተማ እና የምዕብራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም የበላይ ጠባቂ የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ሥር በሚገኙ መምሪያዎችንና ድርጅቶችን ይፋዊ ጉብኝት አደረጉ።
የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በጽሕፈት ቤቱ ሥር የሚተዳደሩ የመምሪያና የድርጀት ቢሮዎች አደረጃጀትን እና አሰራርን በመመልከት ቀጣይ የሥራ መመሪያን ለመስጠት ነው።
በዚህ ጉብኝትም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የቤተክርስቲያና ችንን አሰራር በሚገባ ለማዘመን የሚያስችል አደረጃጀት ያላቸው ቢሮዎች መኖራቸውን እንደተመለከቱ የጠቆሙ ሲሆን በአግባቡ መደራጀት የሚያስፈልጋቸው ቢሮች መኖራቸውንም የታዘቡ መሆኑን ገልጸው በተቻለ አቅም የቢሮዎችን አደረጃጀት በማስተካከልና በግብዓት በማሟላት በቀጣይ የሚከናወኑ ተቋማዊ አሰራሮችን እንዲሸከሙ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የተሳካ ለማድረግ የዛሬው ጉብኝን መሰረታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ዛሬ ከቀትር በኋላ በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት እንዲሁም ቤተክርስቲያናችን በምታስተዳድራቸው ቤቶችና ሕንጻዎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ የወጣው መርሐ ግብር ያስረዳል።