የለገጣፎ ደብረ ብፁዓን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም እና አቡነ ሐራ ድንግል ዘመናዊ የፀበል ቤት በብፁዕ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተባርኮ ተመረቀ
ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት፣ በለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የደብረ ብፁዓን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም ወአቡነ ሐራ ድንግል በዘመናዊ መልክ ያስገነባው የፀበል ቤት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ተባርኮ ተመረቀ።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ፣ የቡራዩ ገፈርሳ፣ የጉጄ መልካ ኖኖ ክፍላተ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የክፍለ ከተማው ዋና ጸሐፊ መጋቤ አእላፍ ስዩም ብዙአየሁ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ሐዲስ ሙሴ በለጠ፣ አባቶች ካህናት እና በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።
በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ሐዲስ ሙሴ በለጠ የደብሩን አጠቃላይ የሥራ ሪፖርት ለብፁዕነታቸው አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው በእለቱ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፤ “በጌጠኛ ቤትህ ልማት ይሁን” በሚል ኃይለ ቃል ሰፊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ልማቶችን እንደምታከናውን አብራርተዋል።
የመጀመሪያውና ዋናው ልማት የክርስቶስ ሕንጻ የሆነውን የሰውን ልጅ አእምሮ በወንጌል ማልማትና የጠፉትን በጎች ፈልጎ ወደ በረቱ መመለስ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ምዕመናን የሚፈወሱበትን የፀበል ቤት ማዘጋጀትና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎችን በመገንባት ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል ማድረግ ነው ብለዋል። አክለውም ፀበሉ ለሕሙማንና ለድውያን ትልቅ የፈውስ ቦታ መሆኑን ገልጸዋል።
በመቀጠልም የፀበል ቤቱን ግንባታ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ያሠሩትን ለኃይለ ሚካኤል እና ለባለቤታቸው ለወይዘሮ ሥርጉተ ገብርኤል ብፁዕነታቸው የላቀ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተውላቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በሐሳባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምዕመናን የሽልማትና የምስጋና መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል።© ሸገር ሀገረ ስብከት ሚዲያ