ደንበኛ ተኮር ስርዓት የወለደው የነዋሪዎች አንድነት ከድርጅቱ አልፎ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋርም እያስተሳሰረ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የተጀመረው ደንበኛ ተኮር ስርዓት ደንበኞችን ከድርጅቱ ጋር ከማቆራኘት አልፎ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጋር መናበብን የፈጠረ ሲሆን ይህንኑ በሚገልጽና ተባባሪነትን በሚያሳይ መልኩ በዛሬው እለት የጽዳት ዘመቻ አካሂዷል።
የጽዳት ዘመቻው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ፤ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅርሳቅርስ ፣ ቤተመጻሕፍትና ወመዘክር ፣ የማኅበራት ፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያዎች የበላይ ኀላፊ፣ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊና የመንትዮች ሕንፃ ነዋሪዎች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን ወደፊት በሁሉም ሕንፃዎች እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ይህ የጽዳት ዘመቻ ከአከራይና ተከራይ ትስስር ባለፈ በባለቤትነት ስሜት እንዲገለገሉ የሚያቀራርብና ወደፊትም በትብብር ቤተክርስቲያንን ለማገልገል የሚረዳ እንዲሁም ነዋሪዎች ለኑሮ የሚመርጡት ሥፍራ ምቹ ፣ ጽዱና ማራኪ ሕንጻዎች እንዲሆኑ የሚያደርግና የሚያግዝ በመሆኑ በየወሩ መካሄድ እንዳለበት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
የብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊምው በበኩላቸዉ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት በዋናው መሥሪያ ቤት እየተከናወነ የሚገኘው ቅጥር ጊቢውን የማስዋብ ሥራ ወደ ውጭ ወጥቶ የድርጅቱ ደንበኞች በሚገኙበት ሁሉ መቀጠል እንዳለበት ሲያሳስቡ ቤተክርስቲያን የንጽሕና አዳራሽ ናት ። ንጽሕና የክርስትና ዋና መገለጫ ነው። ይህንን ማድረግ ክርስትናን መግለጽ ሲሆን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የፈነጠቀው የልማት ጀምበር በሁሉም ሕንጻዎች መካሄድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በተለይም የድርጅቱ ደንበኞች እስካለሁ እኖራለሁ በሚል ጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ እንዳይገቡና በባለቤትነት ስሜት የተከራዩትን ቤት በአግባቡ በመጠቀም ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የሁሉም ሕንፃ ነዋሪ ኮሚቴዎች በየጊዜው ይህንን የጽዳት ዘመቻ ለመካሄድ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በዘሬው እለትም የጽዳት ዘመቻ ያደረጉት የመንትዮች ሕንፃ ነዋሪዎችና ኮሚቴዎች ባደረጉት ሥራ ፈር ቀዳጅ በመሆናቸው ተመስግነው በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል።