ከግንቦት እስከ ግንቦት ክፍል ሦስት
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በከፍተኛ ድምጽ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ደረጃውን
በጠበቀና የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲደራጅ ፣ እንዲጸዳና እንዲዋብ በማድረግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንም ዓይነት ወጪ ሳይጠይቁ በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ያማረና ግሩም እንዲሆን አድርገውታል።
ይህም በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ አገልግሎቱን በተደራጀና በተቀላጠፈ አግባብ ማከናወን የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ከመቻላቸውም በላይ መደበኛና ከመደበኛ ውጪ በሆነ መልኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ሥራ የሚያግዙ ምሁራን የሥራ ኃላፊዎችን በማሳተፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ በአግባቡ እንዲጻፍ፣የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጅና ወጥነት ያለው የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች ተከትሎ ግልጽነት እንዲፈጠር በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር የሚመጥኑ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል።
ብፁዕነታቸው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ጊዜ ተቋማዊ መሰረታቸውን የበለጠ አጠናክረው የሚከናወኑበትን ሥርዓት በመከተል፣ቅዱስነታቸው በጤና እክል ምክንያት የቋሚ ሲኖዶስን ስብሰባ በማይመሩበት ጊዜ ቅዱስነታቸውን በመወከል የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባን በአግባቡ በመምራት ወቅታዊ መረጃዎችን ለቅዱስ ፓትርያርኩ በማስረዳትና ከቅዱስነታቸው መመሪያን ተቀብለው በአፋጣኝ በመተግበር የተዋጣለት ሥራን ሠርተዋል።በእነዚህ ጊዜያትም የቅድስት ቤተክርስቲያንንና የብፁዓን አባቶችን ክብር በማስጠበቅ ተቋማዊ ውሳኔዎችን በማስወሰንና አፈጻጸማቸውን በየወቅቱ በመከታተል አርዓያነት ያለው ሥራን ሠርተዋል።
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው በዘመነ ሢመታቸው የተከናወኑ ሁለት ጉባኤያትን በአግባቡ በማስተባበር፣በመምራትና ሲኖዶሳዊ ክብርን የሚያስጠብቅ ማጠቃለያን በማቅረብ፣እጅግ የተረጋጋ፣ፍጹም መደማመጥ የታየበት ውጤታማ ጉባኤ እንዲካሔድ በማድረጋቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተሰማቸውን ደስታ በምስጋና ገልጸውላቸዋል።ለዚህ ውጤታማነታቸው ትልቁ ምክንያትም ብፁዕነታቸው ያላቸው የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ፣ብልሃት የተሞላበት የመሪነት ክህሎት፣አርቆ የማሰብ ብቃት፣መጠነ ሰፊ ተቋማዊ አመለካከት፣ ለቤተክርስቲያን ሉዓላዊነት እና ክብር በቆራጥነት የመሥራት የዳበረ ልምድና ፍጹም የሆነ የሁለንተናዊ ብቃት ባለቤት መሆናቸው እንደሆነ የሚጠራጠር አይደለም።
ከፍ ሲል በተጠቀሱት ዋናዋና ምክንያቶችም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም እጅግ ስኬታማና የተዋጣለት መሆን ችሏል።
ከግንቦት እስከ ግንቦት በቤተክርስቲያናችን ደረጃ የተመዘገቡት ውጤቶች እጅግ በአጭሩ በሦስት ክፍል የተመለከትናቸው ሲሆኑ የተመዘገቡት ውጤቶች ሊመዘገቡ የቻሉት አልጋ በአልጋ በሆነ የማስፈጸምና የመፈጸም ሂደት አልነበረም።ይልቁኑ በርካታ እሾህና አሜኬላ ታልፎ እንጂ፤በቤተክህነት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውጤት የተመዘገበውም ሁለቱ ብፁዓን አባትች በርካታና እልህ አስጨራሽ ተግዳሮቶችን በድል እድራጊነት ተወጥተው እንደሆነም ብዙ ማሳያዎችን መደርደር ይቻላል።
ከሁሉ የከፋውና አሁን ድረስ ልዩልዩ ሥልቶችን በመቀየር እየተሞከረ የሚገኘው ታላቁ ተግዳሮት ሁለቱን አባቶች ለመለያየት እየተደረገ ያለው ያልተሳካና ሊሳካ የማይችለው ሙከራ ሲሆን መሰረታዊ ምክንያቱ አሁን የተመዘገበውና ወደፊት የሚመዘገበው ውጤት እንዴት በሁለቱ አባቶች ዘመነ ሢመት ይሆናል? ከሚል ቤተክህነታዊ ቅንአት የሚነሳ ሆኖ መዳረሻው ዘረኝነትን በማስፋፋት ቤተክርስቲያንን የፖለቲካዊ ፍላጎቶች ማስፈጸሚያ መድረክ ማድረግን መሰረት ያደረገ ሆኖ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ በተደራጀ መልኩ የሚከወን እኩይ ተግባር እንደሆነም ግልጽ ነው።
ይህ በደንብ የገባቸውና የዚህ እኩይ ዓላማ አስፈጻሚዎች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቀው የሚያውቁት ብፁዓን አባቶቻችን እነዚህ እኩያን በሁለቱ መካከል የሚገቡበት ቀዳዳ እንዳይኖር በማድረግና በዋና ሥራቸው ላይ ብቻ በማተኮር ባደረጉት እንቅስቃሴ የሚታይና የሚዳሰስ ውጤትን ሲያስመዘግቡ በሌላ በኩል ደግሞ የነዚህን እኩያን ፍላጎት ማምከን ችለዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱን ካላለያዩ፣በመካከታቸው መለያየትን ካልፈጠሩ፣ ፓለቲካዊ ዓላማቸውን ማስፈጸም እንደማይችሉ የተገነዘቡት የቤተክህነቱ ተግዳሮት ጠንሳሾች አንድ ጊዜ የፌስቡክ ሰራዊት በማደራጀትና የሐሰት ስም ማጥፋት ላይ በመሰማራት፣ ሌላ ጊዜ የአንደኛው አባት ተቆርቋሪ በመምሰልና የሐሰት ፕፖጋንዳን መሰረት ያደረገ ዘመቻን በመዝመት፣ሲያሻቸው ደግሞ የሚቀርቧቸውን አባቶች በማሳመንና አንዱ በአንዱ ላይ ጥርጣሬን በመፍጠር ወደ ጸብ እንዲገቡ በመጎትጎት፣ሲቀጥሉ ደግሞ የሁለቱ አባቶች ቀራቢ ናቸው የሚባሉ ሰዎችን በጥቅማጥቅም በመደለል እሱ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ በነዚሁ ወገኖች ላይ ጠላቶችን በማደራጀት እንዲነሱባቸውና እንዲወነጀሉ በማድረግ፣ ሲጨንቃቸው የነሱ ተከታዮች በመሆን አባቶችን እንዲክዱ በማግባባት ሲብሰ ደግሞ ሁለቱን አባቶች በንዋይ በመደለል አንድነታቸውን ለማናጋት ብዙ ቢጥሩም የሁለቱ ብፁዓን አባቶች የኖረና ሦስት አሥርታትን የዘለቀ ወንድማማችነትን መናድ ሳይችል በመቅረታቸው እነሆ በፍቅርና በአንድነት ከግንቦት እስከ ግንቦት በስኬት መዝለቅ ችለዋል።
ለወደፊትም አንድነታቸውን አጽንተው፣ወንድማማችነታቸውን አሳድገው፣በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበው ፣የቤተክርስቲያንን
ጥቅም አስከብረው፣ የጠቅላይ ቤተክህነቱን አሰራር አዘምነው፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ጽፈው፣በጥቅሉ ቤተክርስቲያንን ለመበተን መከራ የሚበሉ ሕልመኞችን ፍላጎት አክሽፈው ቀሪ ዘመነ ሢመታቸውን ከአሁን በበለጠ አንድነትና ፍቅር በመፈጸም የቤተክርስቲያንን አስተዳደራዊ ትንሳኤን እንደሚያበስሩ ጥርጥር የለውም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ግንቦት ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ