በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የሚመራው የቤተክርስቲያን ልዑክ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤልን በዓል በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱሰ ገብርኤል ገዳም አክብሮ በሰላም ተመልሷል።
ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ድሬዳዋ -ኢትዮጵያበብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤልን በዓል በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት በማክበር በሰላም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ተመልሷል።
ሁለቱ ብፁዓን አባቶች በቆይታቸው በድሬዳዋ ሳባ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የተገነባውን ሁለገብ ሕንጻን የመረቁ ሲሆን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት እድሳት ሥራንና የአዳሰፈራሽ ግንባታ ሥራንን እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ወጪ በመገንባት ላይ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የድሬዳዋ መልካጀብዱ አቡነ አረጋዊና ቅድስት አርሴማ ገዳምን የጎበኙ ሲሆን በገዳሙ የሚኖሩ እጓለማውታ ሕጻናትንም ባርከዋል።በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓልን በደማቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ያከበሩት ብፁዓን አባቶቹ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ትውልድ ተኮር የልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል።
በብፁዓን አባትች የሚመራው ልዑክ ዛሬ ከቀትር በኋላ ከድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲነሳ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ፣ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች አሸኛኘት አድርገውለታል።