የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም ሀዋሳ – ኢትዮጵያሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን ያዳነበትን ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚዘክረው የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአባቶች፣ በመንግሥት ኃላፊዎችና ከመላው ኢትዮጵያ በተሰበሰቡ በርካታ ምዕመናን በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከትና የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት አባ ዘሚካኤል መርጊያ፣ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደጊዮርጊስ ታዬ፣ መጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ዳንኤል ጌታቸው፣ መልአከ መንክራት ቆሞስ አባ ገሪማ፣ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ፣ የመንግሥት አመራሮች፣ የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
ክብረ በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ስብሐተ እግዚአብሔር በድምቀት ተከናውኖ፣ በማግስቱ የቅዳሴ ሥርዓት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት ተፈጽሟል። በዚሁ ወቅት መጋቤ ሐዲስ መምህር ወልደ ትንሣኤ የአዲስ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ኪዳን መምህር ቃለ እግዚአብሔር አስተምረው፣ ታቦታቱም በዝማሬና በእልልታ ታጅበው የዑደት ሥርዓት ተከናውኗል።
በመቀጠል የገዳሙ ሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያንና ሊቃውንት ለበዓሉ የሚመጥን ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል።
የሲዳማ ሀገረ ስብከት የሲዳምኛ ትርጉም ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ታረቀኝ እንግዳ በበኩላቸው ሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ አገልግሎትን በሲዳምኛ ቋንቋ ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት መጻሕፍት ወደ ሲዳምኛ ቋንቋ መተርጎማቸውን፣ በቀጣይም ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት እየተተረጎሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ መምህር ቆሞስ አባ ኪዳነማርያም አንዱዓለም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት በማስተላለፍ፣ ገዳሙ ከሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች በተጨማሪ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ ለአቅመ ደካሞችና ለችግረኞች የሚያደርገውን ድጋፍ አብራርተው፣ ለበዓሉ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።
የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት አባ ዘሚካኤል መርጊያ ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ተልኮ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን ከሰማዕትነት ፈተና ያዳነበት ታሪክ በእምነት መጽናትንና ፈተናን በእምነት ማለፍን የሚያስተምር መሆኑን ገልጸዋል።
በመቀጠል የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለመጡ ምዕመናን እንኳን ደህና መጣችሁ፣ እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈው፣ በቀጣይም የቅዱስ ገብርኤልን በዓለ ንግሥ በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ተገኝተው እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍም ከኢሳይያስ 43፥1-3 የተወሰደውን “በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ…” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር መነሻ በማድረግ፣ ስለ በዓሉ መንፈሳዊ ትርጉም፣ ስለ እምነት ጽናትና በዘመናችን እየታዩ ስለሚገኙ የሰው ጭካኔና አረመኔነት ሰፊ ትምህርት አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ለክልሉና ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ለሚያደርጉት ትብብር ምስጋና አቅርበው፣ ገዳሙ በልማትና በማኅበራዊ ድጋፍ ላይ ያለውን አስተዋፅኦ አብራርተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ካስተላለፉ በኋላ፣ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀትና ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል።©ናዛዚ ሚዲያ