የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ላለፉት ሁለት ዓመታት ያሰተማራቸውን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ !!!
ጷጉሜን 01 ቀን 2018 ዓ/ም
የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ላለፉት ሁለት ዓመታት ያሰተማራቸውን ደቀ መዛሙርት በዛሬው ዕለት አስመረቀ
በመርሐ ግብሩም ላይ መጋቤ ኅሩያን አባ ኤልያስ በልሁ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም አስተዳዳሪ ፣ መልዓከ ብርሃናት ዶ/ር አባ ጴጥሮስ ሰለሞን የገዳሙ ስብከተ ወንጌል እና የአስተዳደር ቦርድ ፀሐፊ ፣የገዳሙ አበው መነኮሳት ፣ የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ነባር አባላት እና የሥራ አስፈጻሚዎች ፣ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት እና የተመራቂ ደቀ መዛሙርት ቤተሰቦች በተገኙበት ተከናውኗል ።
በዕለቱም በመምህር አባ ገብርኤል አያሌው የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ስብከተ ወንጌል አገልጋይ “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር” የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ ዕብራውያን 13፣8 ። በሚል ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ የሚያረጋጋና የሚያጸና ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል ።
ተማራቂ ደቀ መዛሙርት መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርቱ በማዕከላውያን ክፍል ፣ መስማት በተሳናቸው ክፍል ፣ በቅዳሜ እና እሑድ ፣ በእሑድ ብቻ ፣ ሰኞ እና ረቡዕ በማታ መርሐ ግብር ፣ ሰኞ እስከ ሐሙስ በምሳ ሰዓት እንዲሁም በርቀት በአጠቃላይ ከ219 በላይ ትምህርታቸውን ለ12ወራት እንዲሁም ለሁለት ዓመታት የተከታተሉ መሆኑ ተገልጿል ።
ተመራቂዎች በለፉት ዓመታት
፩• ሀልዎተ እግዚአብሔር እና ሥነ ፍጥረት
፪• ኦርቶዶክሳዊ የስብከት ዘዴ
፫• አምሥቱ አእማደ ምሥጢራት
፬ • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
፭ • ነገረ መንፈስ ቅዱስ ፣ ነገረ ማርያም ፣ነገረ ቅዱሳን ነገረ ሃይማኖት ፣ነገረ ድኅነት
፮• ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር
፯ • ዕቅበተ ዕምነት
፰ • ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
፱• የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ እና በዓለም መድረክ
፲•ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን ተምረው አጠናቀዋል ።
የገዳሙ ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት እጅግ አንጋፋ እና ስመጥር ከመሆኑም በላይ ብዙ የቤተ ክርስቲያን እና የሀገር ባለውለታውችን ያፈራ፣ ወንጌልን ለሁሉም ይደርስ ዘንድ መስማት ለተሳናቸው ወገኖች በምልክት ቋንቋ የሚያስተምር እንዲሁም በአርድዕት ጉባኤ የነገ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ሕጻናትን የአብነት ትምህርት በማስተማር ዋነኛ ዓላማ አድርጎ እየሠራ ያለ ባለታሪክ ሰንበት ትምህርት ቤት ነው።
ባለፉት ዓመታት በሰንበት ትምህርት ቤቱ ያሳለፍናቸው ግዚያት ያካበትነው እውቀት ለነገው ህይወታችን ትልቅ መሠረት ነው ለዚህ ቀን ያበቃን ፈጣሪ ይመስገን ሲሉ ተመራቂ ተማሪዎች ተናግረዋል ።
በመርሐ ግብሩ ላይ በተመራቂ ተማሪዎች የወረብ ዝማሬና ስነፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ለመምህራን፣ለደረጃ ተማሪዎች የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተሰጥቷል።
የገዳማችን አስተዳዳሪ መጋቤ ኅሩያን አባ ኤልያስ በልሁ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልዕክት ያስተላለፍ ሲሆን የተመራቂዎች የመመረቅ ዋና ዓላማ የራቁትን ለመሰብሰብና ያልፀኑትን ለማፅናት እንደሆነ በመግለፅ በአገልግሎት እንዲተጉ እና እንዲጠነክሩ አሳስበው በጸሎት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል ።©ምስካየኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም