የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ ለቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ መሪዎች «የእንኳን አደረሳችሁ» ስጦታ አበረከተ።
ጳጉሜ ፪ ቀን ፪፻ ፲ወ፰
አዲስ-አበባ-ኢትዮጵያ
ስጦታው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፣ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሸገር ከተማና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅርሳ ቅርስ ወመዘክርና የማኅበራት ክትትል መምሪያዎች የበላይ ኃላፊ ለብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማት ኮምሽንና የድርጅቱ የበላይ ሊቀ ጳጳስ የቀረበ ሲሆን፤ ተቋሙ ለቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ መሪዎችና አባቶች ያለውን ጥልቅ አክብሮት፣ ፍቅርና የመታዘዝ መንፈስ የሚያንጸባርቅ ነው ተብሏል።
ስጦታው ድርጅቱ የቤተ ክርስቲያኗን ሀብትና ንብረት በጥንቃቄ የመጠበቅና የማልማት ኃላፊነቱን በሚወጣበት እንቅስቃሴ ውስጥ አባቶች ላደረጉለት ያልተለየ ድጋፍ፣ አባታዊ መመሪያና ጸሎት የታላቅ ምስጋና መግለጫ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ የበዓል እንኳን አደረሳችሁ ስጦታ የማበርከትና ከአባቶች ቡራኬ የመቀበል ሥነ ሥርዓት ድርጅቱ አምናም ሲፈጽመው የቆየና እንደ መልካም ተቋማዊ ባህል አጠናክሮ የያዘው ተግባር ነው። በየዓመቱ በበዓላት ወቅት አባቶችን ማሰብ፣ ማክበርና መንፈሳዊ ቡራኬያቸውን መቀበል የተቋሙ ጽኑ እምነት እንደሆነና ይህ በጎ ልማድ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል።
በስጦታ ማበርከቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እስከአሁን ድርጅቱ ያደረገውን በጎ አፈጻጸም አድንቀው አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው አዲስ ነገር ሲሠራበትና ቤተክርስቲያንን ከፍከፍ ስናደርግበት ነውና በአዲሱ ዓመት ይህንኑ አድርገን እስከ አሁን ከምናውቀው በተሻለ አፈጻጸም እንደምትመጡ አምናለሁ ብለዋል።
በመቀጠልም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራአስኪያጁ ባለፈው አንድ ዓመት ድርጅቱ ያሳየው ትጋት እጅግ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጸው ወደፊትም ቢሆን እኛን ያሰባሰበችን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ማስቀደም ግድ ስለሆን እርሷን አስቀድመን ጠንክረን መሥራት ይገባናል ብለዋል።
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው በበኩላቸው የድርጅቱ መነቃቃትና ትጋት በዚሁ እንዲቀጥል አሳስበው ለተደረገው የመልካም ምኞት ስጦታን አመስግነዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሸማኔ መወርወሪያ በሚፈጥነው ጊዜ ውስጥ እየኖርን ለሥራ አለመፍጠን አይቻልምና ልክ እንደ 2018ዓ.ም ቀጣዩን ዓመትም በዚሁ ልክ እየሠራን ልናሳልፍ ይገባል ያሉት ደግሞ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የድርጅቱ የበላይ ሊቀ ጳጳስ ናቸው።
በመጨረሻም አባቶች በደርጅቱ የተበረከተላቸውን ስጦታ በደስታ የተቀበሉ ሲሆን፤ ድርጅቱ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረቶች በማልማትና ገቢዋን በማሳደግ በኩል እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል። አባቶች አክለውም ተቋሙ በቀጣይ በዘመናዊ አሠራርና በግልጽነት የታገዘ የልማት ሥራ በማከናወን የድርሻውን እንዲወጣ አባታዊ መመሪያና ቡራኬያቸውን አስተላልፈዋል።
© ኢኦተቤክ_ቤሕአልድ