የአንድ ክፍለ ዘመን ጽናትን በታላቅ የወንጌል ፍሬ የመለሰው የጅማ ሀገረ ስብከት 81 ወገኖችን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን መለሰ
ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም| ሕዝብ ግንኙነት መምሪያበጅማ ሀገረ ስብከት፣ በኖኖ ቤንጃ ወረዳ በአልጋ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በታላቅ ድል ተጠናቀቀ። በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ቀደም ሲል የተለያዩ እምነቶችን ይከተሉ የነበሩ 81 ወገኖች ወደ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ የሥላሴን ልጅነት (የክርስትና ጥምቀትን) ማግኘታቸውን የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት አስታውቋል።
የኖኖ ቤንጃ ወረዳ ሕዝበ ክርስቲያን ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት (አንድ ክፍለ ዘመን) ያህል በታሪካቸው ውስጥ እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ የነበረውን የመንፈሳዊ እረኛ እጥረት በጽናት ተጋፍጠውታል። በዚህ ረዥም ዘመን ውስጥ ቋሚ ካህን ሳይመደብላቸው፣ ሕፃናትን አጥምቆና ሥጋ ወደሙን አክብሮ የሚያቀብል መንፈሳዊ አገልጋይ ሳይኖራቸው፣ እንዲሁም የማዕደ ቃል ኪዳኑን ወንጌል የሚመግብ ሰባኪ ሳያገኙ በከፍተኛ መንፈሳዊ ጥም ውስጥ ለመቆየት ተገደው ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ይህ ሁሉ መገለልና የእረኛ እጥረት ሳይበግራቸው፣ ከቀደሙት አባቶቻቸውና እናቶቻቸው የተቀበሉትን የእምነት ቀንዲል ሳያጠፉ፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን ክብርና ማንነት በልባቸው ጽላት ላይ ቀርጸው የኖሩ እውነተኛ የሃይማኖት ጠበቆችና የጽናት ተምሳሌት መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል። ይህ የአንድ ክፍለ ዘመን ታሪካዊ ተጋድሎና የውስጥ ጽናት ነው ዛሬ ለታየው ታላቅ መንፈሳዊ ፍሬና የወገኖቻችን መመለስ ማዕዘን የሆነው።
በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሚስዮናውያን “ዘመቻ ፊልጶስ” በሚል ስያሜ ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ ምዕመናኑን ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነታቸው ለመለየት ከፍተኛ ግፊት ቢያደርጉም፣ የአካባቢው ጽኑዓን አባቶችና እናቶች ግን፦
“እምነታችን አንዲት ናት፤ እሷም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት!”
በማለት የአባቶቻቸውን አደራና የሃይማኖት ርስት ሳያስደፍሩ በጽናት መቆየታቸው በጉባኤው ላይ ተንጸባርቋል።
ማዕደ ቃል ኪዳኗን ናፍቀው ቆይተው ዛሬ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እቅፍ ከተመለሱት ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ በዕለቱ ባስተላለፉት ልብ የሚነካና ጥልቅ ምስክርነት፤ ከተዋሕዶ እምነታቸው ርቀው ለዓመታት እንዲንከራተቱ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት “የቋንቋ ተደራሽነት ክፍተት” እንደነበር በቁጭት አውስተዋል። በተለይም ማኅበረሰቡን ከተኩላ ለመጠበቅ የሚደረገውን መንፈሳዊ ጉዞ ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱ አካላት “በገዛ ቋንቋችሁ ካልተማራችሁና ካልጸለያችሁ ከእግዚአብሔር ጋር መንገድ ላይ ተላልፋችኋል፤ ጸሎታችሁም አይሰማም” በሚል የተቀነባበረ የሐሰት ፕሮፓጋንዳና የተሳሳተ ትምህርት ታጥረው፣ በከፍተኛ መንፈሳዊ መደናገር ውስጥ ቆይተው እንደነበር በግልጽ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ወቅት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት የማኅበረሰቡን ቋንቋና ባህል ማዕከል ባደረገ መልኩ በአካባቢው በስፋትና በጥራት በመዘርጋቱ፣ ያ የነበረው የጨለማ መጋረጃ ሊቀደድ ችሏል። ዛሬ ላይ ያለምንም መጋረጃ በገዛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ፣ ከአምላካቸው ጋርም በልባቸው ቋንቋ መገናኘት በመቻላቸው የተሰማቸውን ቃላት የማይገልጸው ታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ዕርካታ በደማቅ እንባ ታጅበው መስክረዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በማኅበረሰቡ ቋንቋና ባህል መሠረት አድርጋ የጀመረችው የወንጌል አገልግሎት ምን ያህል ውጤታማና ታላቅ ድል እየተቀዳጀበት ያለ መሆኑን የኖኖ ቤንጃ ወረዳ በተግባር አሳይቷል። በዚሁ መሠረት በያዝነው በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከወረዳው በአጠቃላይ 318 ምዕመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው የቅድስት ሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል።
የዜና ምንጭ፦ ጅማ ሀገረ ስብከት
ዘጋቢ ሪፖርተር፦ ላዕከ ወንጌል ኃይሉ አየለ