በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተጀምሮ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ትጋት ለፍጻሜ የበቃው ባለ 480 ካሬ ሜትር ሁለገብ ሕንጻ ተመረቀ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ምዕመናን በተገኙበት፣ በአዲስ አበባ አሮጌ ቄራ አካባቢ የተገነባው ዘመናዊ ሁለገብ ሕንጻ በዛሬው ዕለት በደመቀ ሁኔታ ተመርቋል። ይህ በ480 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውና ባለ 11 ወለል (B+G+10) የሆነው ሕንጻ፣ ግንባታው የተጀመረው በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ዘመነ ሢመት ነበር። ሆኖም ግንባታው በአራት የተለያዩ ኮንትራክተሮች እጅ በማለፉ ምክንያት ከፍተኛ መጓተት አጋጥሞት ቆይቷል።
ይህንን መጓተት ለመቅረፍ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ የአሠራር ሥርዓቱን በማስተካከልና ለሮሃ ኮንስትራክሽን ሙሉ ኃላፊነት በመስጠት፣ ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ማለትም በ40 ቀናት አካባቢ ተጠናቆ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ለምረቃ እንዲበቃ ሆኗል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሕንጻውን ዝርዝር ሁኔታ በሚመለከት የግንባታ አማካሪው ኢንጂነር ቀሲስ ደመቀ አሸናፊ እንዳብራሩት፣ ሕንጻው ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ምቹ የሆኑ ባለ ሦስት መኝታ ቤቶችን የያዘ ሲሆን፣ በውስጡም ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችና ባልኮኒዎች ተካተውለታል። በተጨማሪም ሕንጻው የሚከተሉትን ዘመናዊ የደኅንነት ሥርዓቶች ያካተተ ነው፦
ሙሉ ሕንጻውን የሚቆጣጠር የሴርቨላንስ ካሜራ ተገጥሞለታል።
ሙቀትና ጭስን ለይቶ የሚያውቅና አደጋ ሲከሰት አላርም የሚያደርግ የፋየር ሲስተም ኮንትሮል አለው።
በእያንዳንዱ ወለል ላይ የእሳት አደጋ መከላከያ (ፋየር ሃይድራንት) እና የአደጋ ጊዜ መውጫ (ኢመርጀንሲ ኢግዚት) ተዘጋጅቶለታል።
ይህ ታላቅ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።