የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ለሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለአገልግሎት የሚሆን ፕራዶ መኪና ገዝቶ በስጦታ አበረከተ
ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመኪናውን ቁልፍ ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሸካ ቤንች ማጂ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ የበላይ ኃላፊ አበርክተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት “ሥራ የሚሠራ ሰው ዋጋ ይገባዋል፡፡ ለአገልግሎት የሚሆን መኪና አስፈላጊ ነው፡፡ ብፁዕነትዎ እርስዎ ብዙ ጊዜ ሲጠይቁ ቆይተው አሁን ማግኘትዎ በጣም ደስ ብሎናል፤ ለአገልግሎት የሚሆን መኪና ስላገኙ ሁላችንም ደስ ብሎናል፤ እግዚአብሔር የተባረከ ያድርግልዎት” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት “ቀደም ሲል ለቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተያዘው በጀት ዓመት ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ አባታችን መመሪያ ሰጪነትና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ፕራዶ መኪና እንዲገዛ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በጠየቁት መሠረት ጥሩ መኪና ተገዝቶላቸዋል፡፡ ብለውል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልም እንደተናገሩት “እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜና ሰዓት ጥሩ መኪና ተገዝቶልናል፤ ለዚህም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አስተዋጽኦ መሠረት ሲሆን፤ ይህን ያደረገ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፣ እግዚአብሔር ይስጥልን ስለተደረገልኝ በጣም አመሰግናለው” ብለዋል፡፡
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት ከተመሠረተበት ከ1935 ዓም ጀምሮ መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ትምህርት ጎን ለጎን በማስተማር አያሌ ሊቃውንትን፣ ጳጳሳትንና ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራት የታወቀ አንጋፋ ትምህርት ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡በአሁኑ ወቅትም የትምህርት አድማሱን በማስፋት የትምህርት አገልግሎቱን አጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑ ይታወቃል፡፡
©Eotc tv