ጳጉሜ የሚለው ስያሜ ‹‹ኤፓጉሜኔ›› ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ጭማሪ›› ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)
ወርኃ ጳጉሜን እንደሌሎቹ ወራት ፴ ቀናት ሳይሆን በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ስድስት ቀናት ሲኖራት በዘመነ ማርቆስ፣ በዘመነ ሉቃስና በዘመነ በማቴዎስ ደግሞ አምስት ቀናት ብቻ ይኖራታል፤ ነገር ግን የዓመቱ ዐሥራ ሦስተኛ ወር ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡
ወርኃ ጳጉሜን ካሳለፍነው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከዘመነ ክረምት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ በመሆኗ የዓለም ፍጻሜ (የዳግም ምፅአት) መታሰቢያ ተደርጋም ትታሰባለች፡፡
ጳጉሜን ከዘመነ ክረምት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ እንደሆነች ሁሉ ዳግም ምጽአት ከምድራዊ ሕይወት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ ናት፡፡ ጳጉሜን የክረምት ማብቂያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም እንዲሁም የዚህ ዓለም ኑሮ ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜን አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃን አዲሲቷን ምድር (መንግሥተ ሰማያትን) ለመውረስ የበቁትን ‹‹እናንተ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ›› የሚባሉባት ዕለት ናት፡፡
በዚህም የተነሣ ብዙ ምእመናን በወርኃ ጳጉሜን በጾምና በጸሎት ይተጋሉ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል በጳጉሜን ሦስት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) በመሆኑ በዚህች በተከበረችው ዕለት ምእመናን ጸሎታቸው ያርግላቸው ዘንድ ከምን ጊዜውም በበለጠ ተግተው ይጸልያሉ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእኛን ጸሎታችንን በምልጃቸው የሚያሳርጉልን ቅዱሳን መላእክትም መሥዋዕቱን የሚያሳርጉበትና የአምላካችንን ምሕረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡