የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ትምህርት ቤት የ፳፻፲፱ ዓ.ም የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በተገኙበት በይፋ አስጀመረ።
መስከረም ፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፱ ዓ.ምአዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ትምህርት ቤት የ፳፻፲፱ ዓ.ም የመማር መስተማር ተግባሩን ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርርክ ጠቅላይ ቤተክህነታ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት መስከረም ፭ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም በይፋ አስጀመረ።
የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አስተዳዳሪ መጋቤ ኅሩያን ቆሞስ አባ ኤልያስ በልሁ ለብፁዓን አባቶች የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ትምህርት ቤት ከተመሠረተ ዘንድሮ በ፳፻፲፱ ዓ.ም 53ኛ ዓመቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መጋቤ ኅሩያን አያይዘውም በወቅቱ የነበሩ አባቶች ትምህርት ቤት እንዲከፈት ያደረጉበት ሦስት ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ “የመጀመሪያው ተማሪዎች መንፈሳዊውን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አጣምረው እንዲማሩ ለራሳቸው፣ ለወገኖቻቸው ለሀገር ለቤተክርስቲያን ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ታስቦ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከርእሰ መምህሩ ጀምሮ እስከ ታች ያሉ ልዩ ልዩ ሠራተኞች በሙያቸው ሠርተው ደመወዝ እንዲያገኙ ሲሆን፤ በሦስተኛ ደረጃ ገዳሙ በመጠኑም ቢሆን ገቢ ያገኛል ተብሎ ታስቦ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የዛሬ 53 ዓመት ሲመሠረት በ39 ተማሪዎች፣ በ3 መምህራን፣ በ3 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የተመሠረተው ትምህርት ቤታችን በአሁኑ ሰዓት ከሦስት ሺሕ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የ፳፻፲፰ ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደትና አጠቃላይ የትምህርት ቤቱ የሥራ ክንውን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ወርቁ አሸናፊ አቅርበዋል፡፡ ርእሰ መምክሩ አንዳብራሩት “ትምህርት ለሰው ልጅ የተሻለ ኑሮ ለመኖር በሚያደርገው ጥራት የተፈጥሮንና ሰብዓዊ ሀብትን የበለጠ ለማወቅና ለኑሮው ለማመቻቸት የሚስፈልገው ችሎታና አመለካከት ምንጭ ሲሆን ይኸው የሚሰናዳበት ደግሞ ት/ቤት ነው፡፡ አገር ያለመችውን ራዕይ ዕውን ሊያደርግ የሚችለው ወጣቱ የተሟላ ዕውቀት ለራሱ፣ ለወገንና ለሰው ልጅ በጎ አመለካከትና ችሎታ ያለው መሆኑ መረጋገጥ ሲችል ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “ይህንን የአገር፣ የቤተክርስቲያንና፣ የወላጆችን አደራ ለመወጣት የትምህርት ቤታችን ማኅበረሰብ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የገዳማችን አስተዳደርና አጋር አካላት ድጋፍ፣ እገዛና ማበረታታት የተነሣ በዘመኑ ከፍተኛ የሥራ ውጤት ያስመዘገብንበት ሆኖ አልፏል፡፡” ሲሉ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
አቶ ወርቁ ትምህርት ቤቱ አሁን ያለበትን ደረጃ በማወቅና ለረጅም ጊዜ ለማቀድ የሦስት ዓመት (2018 – 2020 ዓ.ም) ዝርዝር ተግባራት የያዘ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማቀድና ከዚህ ውስጥም የ፳፻፲፰ ዓ.ም የትምህርት ቤት መሻሻል ዕቅድ በማውጣት ሥራውን በማካሄድ አሳልፏል በማለት በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
የተማሪዎችን ሁለንተናዊ ብቃት ለማሳደግ ትምህርት ቤቱ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መምህሩ የተማሪዎችን የአካዳሚክ ውጤት ከማሳደግ አንጻርም 6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በ፳፻፲፯ ዓ.ም 99.7 ፐርሰንት ከነበረው በ2018 ዓ.ም 100 ፐርሰንት አድጓል፤ 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በ፳፻፲፯ ዓ.ም ከነበረው 97.6 ፐርሰንት በ2018 ዓ.ም 100 ፐርሰንት፤ 12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ በ፳፻፲፯ ዓ.ም 57.5 ፐርሰንት ከነበረው በ፳፻፲፰ ዓ.ም 86 ፐርሰንት (21 ፐርሰንት) ብልጫ አስመዝግቧል፡፡
“ተማሪዎችን በዕውቀትና በሥነ ምግባር አስተምህሮ ማሳደጉ ይህንን ባለብዙ ፈርጅ ያለበትን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ ነው፡፡ በተለይም እንደኛ ያለ ከ3‚070 ተማሪዎችና ከ250 በላይ ሠራተኞችን በመያዝ በጥቂት የአመራር አካላት ውጤቶችን ማሳከላት የሚወስደው የጊዜ፣ የጉልበትና ራስን የመስጠት ጉዳይ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ያሉት ርእሰ መምህሩ ለዚህ ሁሉ ብርታትና ጉልበተው የሆነን ብፁዕ አባታችን በሁለንተናዊ መልኩ የሚሰጡን ማበረታቻና ድጋፍ የገዳማችን አስተዳደር ሙያችንን በተማርነውና ባወቅነው ልክ እንድንሠራ የሚያደርግልን ድጋፍ ወላጆች በእኛ ላይ ያላቸው እምነትና ለምንጠይቀው ሁሉ ለመደገፍ የሚያሳዩት መነሣሣትና የሙያችን የሕዝባችን አደራ ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ሠርተን የተፈለገውን ዓላማ ለማሳካት እንድንችል የአባቶቻችን ጸሎትና ድጋፍ፣ የወላጆች የዕለት ተዕለት ክትትልና ማበረታታት እንዳይለየን በታላቅ አከብሮት እጠይቃለሁ፡፡” ሲሉ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ከ፳፻፲፰ ዓ.ም ዘመነ ማርቆስ ወደ ፳፻፲፱ ዓ.ም ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገራችሁ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዘመናት ታሪክ የትምህርትና የዕውቀት ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ይህን መንፈሳዊ ሀብት ለመጠበቅ እንደ ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የመሳሰሉ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ትውልድን የመጠበቅ አደራ እየተወጣች ትገኛለች፡፡” ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያን በዚህ ተቋሟ ውስጥ ዓላማዋ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሰውን የሚያከብሩ በዕውቀተው የተሞሉ፣ በሥነ ምግባር የታነጹ፣ ሃይማኖት ያላቸው ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ልጆችን ማፍራት ነው፡፡” ሲሉም የትምህርት ቤቱን ዓላማ አብራርተዋል፡፡ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ቡሁለንተናዊ ሕይወታቸው ከቤተክርስቲያናቸው የራቁ እንዳይሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የምስካየ ኅዙናን ት/ቤት ማኅበረሰብ በሙሉ ትምህርት ቤታችን ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ ዕሴትን በመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ባሳለፍናቸው የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ በርካታ ዜጎች ተምረውበት ለከፍተኛ ማዕረግ በቅተውበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙኀኑ በመልካም ስሙ ያወሱታል፡፡ ስለዚህ ጠቢቡ ሰሎሞን ምሳሌ ፯፥፩ መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል እንዳለው በመልካም ሥራ የተገኘ መልካም ስማችንን በጋራ እንድንጠብቅ አደራ እላለሁ፡፡ ትምህርት ቤታችን በቀጣይ የተሻሉ ተግባራት በማከናወን ተውልድን የበለጠ ለመቅረጽ እየሠራ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ወገን ሁሉን አቀፍ ትብብር እየጠየቅን አዲሱን የትምህርት ዘመን እግዚአብሔር አምላካችን ውጤታማ የሥራ ዘመን ያድርግልን ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርዊ ተልዕኮ መምሪያ ባስተላለፉት መልእክት ትምህርት የሰው ሁለተኛ መፈጠረያው ነው፡፡ ሙሉ ሰው የሚኮነው በትምህርት ነው፡፡ ወላጆችና መምህራን ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የ፳፻፲፰ ዓ.ም በ 6ኛ፣ በ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የሰርተፍኬት ሽልማት ተሰጥቷል። ከ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ላመጣው ተማሪ የወርቅ ሜዳሊያ ተበርክቶለታል፡፡ የላቀ የሥራ አፈጻጸም ላሳዩ የትምህርት ክፍሎች መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የማበረታቻ የሽልማት መርሐ ግብር በብፁዓን አባቶች ተከናውኗል።
በተያያዘ ዜናም ለአራት ዓመታት በላይ በገዳሙ የአብነት ትምህርት ቤት ሥር በሚገኘው የቅዳሴ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መምህራን በብፁዓን አባቶች ተመርቀዋል።©Eotc tv