የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከመላው አህጉረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የምክክር መርሐ ግብር አካሄደ
ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ ከመላው አህጉረ ስብከት ከተሰበሰቡ ዋና ሥራ አስኪያጆችና የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች ጋር በሶር አምባ ሆቴል የምክክር መርሐ ግብር አካሄደ።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎና የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የሥራቅ ሐረርጌ ፣ የምሥራቅ ወለጋና የሖሮ ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ እና የመምሪያው ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋወልደ ትንሳኤ ተገኝተዋል።
መርሐ ግብሩ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ መሪነት በጸሎት ከተከፈተ በኋላ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ባስተላለፉት መልእክት ወንጌል የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮ መሆኑንና ሁሉም አገልግሎቶቿ ይህንኑ ተልእኮ በሚያጠናክር መልኩ መከናወን እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል። ምዕመናንን በቃለ እግዚአብሔር ማነጽ፣ በእምነት ማጽናትና በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድጉ ማገዝ፣ እንዲሁም ካህናትና ወንጌላውያን በጸሎትና በትምህርተ ወንጌል ራሳቸውን እያጠናከሩ በትጋት እንዲያገለግሉ አስፈላጊነቱ ተገልጿል።
በምክክሩ «ስብከተ ወንጌል፡ ትናንት፣ ዛሬና ነገ» በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። ጥናቱም የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት ለማጠናከር ገዳማትን መደገፍ፣ ብቁ ሰባኪያንን ማፍራት፣ የአገልጋዮችን አቅም መገንባት፣ ፍትሐዊ የምደባና የድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን፣ ፖድካስቶችንና አፕሊኬሽኖችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አመልክቷል። አገልግሎቱን ከማኅበራዊ፣ ከምግባረ ሠናይና ከልማት ሥራዎች ጋር ማስተሳሰርም ከቀረቡት ምክረ ሐሳቦች መካከል ይገኝበታል።
በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ በቡድን ተከፋፍለው የአገልግሎቱን ወቅታዊ ሁኔታና ስትራቴጂ፣ የአመራር ቅንጅትና ድጋፍ፣ የወጣቶችንና የዘመኑን ትውልድ ተደራሽነት፣ የአቅም ግንባታና ሥልጠና፣ የአገልጋዮችን ሥነ ምግባርና የስምሪት ሥርዓት በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። የቡድን ውይይቶቹ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ከተገመገሙ በኋላ፣ አገልግሎቱን ይበልጥ ውጤታማ፣ ተደራሽና ከዘመኑ ጋር የተጣጣመ ለማድረግ በሚያስችሉ የወደፊት የሥራ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት በመድረስ እንዲሁም ቀለ ጉባኤውና የአቋም መግለጫ በማንበብ የምክክር መርሐ ግብሩ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ጸሎተ ቡራኬ ተጠናቋል።