የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የመዝጊያ መልዕክት
ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦
“ወትትዐቀቡ በአሐዱ መንፈስ ወበማዕሠረ ሰላም – በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ. ፬፥፫)
በቅድሚያ፡ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ሆኖ የ2019 ዓ.ም.፣ ፵፭ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዚህ መልኩ እንዲናጠናቀቅ ስለረዳን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ አንድነት የቤተ ክርስቲያናችን ህልውና መሠረት መሆኑን ባመለከተበት ቃል ለአንዱ ክርስቶስ አካል የሆንነውን ሁሉ በመንፈስ አንድ እንድንሆን ይመክረናል። አንድነት የቤተ ክርስቲያን የውጭ ጌጥ ሳይሆን የህልውናዋና የውስጥ ማንነቷ ዋና መሠረት ነው። የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ይህ ጉባዔ ነው፡፡ በታሪካችን ውስጥ እንደሚገኝ ጉልህ ምስክር አባቶቻችን ለዚህ ጉባዔ እውንነት የከፈሉት ዋጋ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያስረዳን ነው፡፡ አባቶቻችን “መንፈሳዊ ጉባዔ ዘመንግሥተ ኢትዮጵያ” ብለው የሰየሙትን ጉባዔ ለመመሥረት ያደረጉት ብርቱ ጥረት ፍሬ አፍርቶ እነሆ በእኛ በልጆቻቸው ቀጣዩ ሂደት እየተከናወነ 100ኛ ዓመቱን የምናስብበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
በዚህ ጉባዔ የተሰባሰቡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አህጉረ ስብከት ሁሉ በአንድ የእምነት፣ የሥርዓትና የትውፊት መንፈሳዊ ገመድ የተሳሰሩ ናቸው። በቋንቋ፣ በባህልና በመልክአ ምድር መለያየት በሰው ልጆች ዘንድ የሚኖር ነባር እውነታ ነው፡፡ በክርስቶስ ደም በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያለን ኅብረት ግን ከነዚያ የልዩነት ምክንያች በላይ ሁላችንን አንድ ያደርገናል። ዛሬ ከመላው ዓለም ተሰባስበን በአንድነት መምከራችን የቤተ ክርስቲያናችንን ጥንካሬና ሐዋርያዊነት ለዓለም የሚያሳይ ትልቅ ምስክር ነው።
አንድነታችን የመንፈሳዊ ኃይላችን ምሥጢር ነው፣ በአንድነታችን ልማታችንና ወንጌልን የማስፋፋት አቅማችን ይጠናከራል፡፡ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ አህጉረ ስብከት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሠሩ የማያልፉት መሰናክል አይኖርም። ትውልድን የመጠበቅ ሓላፊነታችን ይሳካል፣ በስደት የሚኖሩ ወጣቶችንና ሕፃናትን ከባህልና ሃይማኖት መጣረስ ለመጠበቅ የአንድነት አቋም ወሳኝ ነው።
ስለሆነም፣ በዚህ ጉባዔ ያደረግነው እያንዳንዱ ውይይት፣ የምናሳልፈው ውሳኔና የምናቀርበው ሐሳብ ይበልጥ አንድነታችንን የሚያጠናክርና በሰላም ማሰሪያ የሚያስር እንጂ መለያየትን የሚያመጣ እንዳይሆን መሥራት ያስፈልጋል።
በሰበካ ጉባዔ አወቃቀር ውስጥ የምናገለግል ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባ ታላቅ እውነት ቢኖር አገልግሎታችን ዓለማዊ ጥበብ ሳይሆን መንፈሳዊ አደራ መሆኑ ነው!
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረግ ማናቸውም የሥራ እንቅስቃሴ፡ ከስበከተ ወንጌል እስከ ሂሳብና በጀት አስተዳደር፣ ከሕንፃ ግንባታ እስከ ማኅበራዊ ልማትና ሌሎችም በሙሉ መንፈሳዊ ዓላማና ውጤት ያላቸው ናቸው። ስለዚህ አገልግሎታችን ትሕትናና መሰጠትን የያዘ ሥነ ልቡና ያስፈልገዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ሕይወቱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማቴ. 20፥28) እንዳለው፣ የዚህ ጉባዔ ተሳታፊዎች የሆንን አገልጋዮች ሁሉ የአገልጋይነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል።
የመልካም አገልጋይነት ሌላው ምሥጢር ታማኝነት ነው፡፡ ስለሆነም ለአምላካችንና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታማኝ ልንሆን ይገባል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሓላፊነት፣ ጊዜና ዕውቀት ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ ልናውለው ይገባል።
የዚህ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዋና ዓላማ ባለፈው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎችን መገምገምና የቀጣይ መንገድ መተለም ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ “እውነተኛና ታማኝ ሪፖርት” ማቅረብና መገምገም የመልካም አስተዳደርና የመንፈሳዊነት መለኪያችን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን አባላት ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” (ኤፌ. 4፥25) ይላል። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሚቀርብ ሪፖርት የተጋነነ የቁጥር ስብስብ ብቻ ሳይሆን የአገልግሎታችን መስተዋት ሊሆን ይገባል።
እውነተኛና ግልጽ ሪፖርት ለእውነተኛ ምዘናና እርማት ይጠቅማል፡፡ ያለፉትን ድክመቶቻችንን በግልጽ ካላየንና ማረሚያ ካልተቀበልን፣ ለነገው ጠንካራ መሠረት መጣል አንችልም። የተሠራውን ያህል ያልተሠራውንም በግልጽ ማየት ያስፈልጋል። የምእመናን ስጦታ፣ ዓሥራትና በኩራት፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ንብረት እንዴት እንደተያዘና እንደለማ በእውነትና በግልጽነት ማሳወቅ የእግዚአብሔርንና የሕዝብን አመኔታ ያተርፋል።
ትክክለኛ መረጃና ሪፖርት ሲኖር ተግባራዊ የሚሆን ዕቅድ ማውጣት ይቻላል፡፡
በመሆኑም በቀረቡት የልማት፣ የበጀት፣ የስበከተ ወንጌል፣ የትምህርትና የማኅበራዊ አገልግሎት ሪፖርቶች ላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ሓላፊነት፣ በእውነተኛነትና በበሰለ መንፈሳዊ እርጋታ እንድናስብ አደራ እላለሁ። ከምንገኝበት ዓለም አቀፍ እውነታ አንጻር ስኬታማ ነን ብለን ያቀረብናቸው ሁሉ ተቆጥረው ተሰፍረው ሊረጋገጡ የሚችሉ መሆናቸው ላይ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በቃል ብቻ የተነገረ ስኬት የነገ አቅጣጫችን ግልጽ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡
በከፍተኛ የሓላፊነት ደረጃ ተይዘው፣ ከቀደሙ ዕቅዶች አንጻር ተመዝነው፣ መከናወናቸው ተረጋግጦ የቀረቡ ሪፖርቶችም አሉ፡፡ ከዚሁ አንጻር በየዘርፉ የተመዘገቡ እድገቶችም አሉ፤ ለእነዚህ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስም ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ለረጅም ዓመታት በዘለቀ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩና በቅርቡ ባገኙት እፎይታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተሠራ ሥራ እጅግ ከተወሳሰበ ችግራቸው ተላቀው ፐርሰንት ገቢ ለማድረግ የበቁ አህጉረ ስብከትም ለቀጣዩ የሥራ ዘመን የሚሆን ትልቅ ተስፋ አሳይተዋልና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
በዚህ ጉባዔያችንን የምናጠቃልልበት ጊዜ ላይ ሆነን የምናሳስበው ነገር ቢኖር የሠራነው በቂ ነው ብለን እንዳናስብ ነው፡፡ ማድረግ የምንችለውና ለቤተ ክርስቲያናችንም የሚገባት ከዚህ በላይ ነው፡፡ ከቀደመው ዘመን የአሁኑ በበርካታ መመዘኛዎች የተሸለ እንደሆነ ሁሉ መጪው ደግሞ የበለጠ እንዲሆን መሥራት ተገቢ ነው፡፡ መዋቅርን መጠበቅ፣ መመሪያንም ማክበር የስፈልጋል፡፡ የተሰጠን አገልግሎት አደራ እንጂ በፍላጎታችን መጠን የምንኖርበት ርስት አይደለም፡፡
ልማታዊ የሆነ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት ጊዜው የሚያስገድደን ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነሕ በጉባዔያችን መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክታቸው እንደተናገሩት፣ ቤተ ክርስቲያን የምትለመን እንጂ የምትለምን መሆን አይገባትም፡፡ ይህን ማሳሰቢያቸውን እንደ መመሪያ ወስደን በልማት እንቅስቃሴያችን፣ ሀብትን በመጠበቅና በማስተዳደር ሓላፊነታችንን፣ ማኅበራዊ አገልግሎትን በማጠናከር አደራችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን የታየውን የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማጠናቀቅ፣ አዲሶችን አቅዶ ተግባራዊ ማድረግና መከታተል ሁላችሁም ልትወስዱት የሚገባ አርአያነት ነው፡፡ በመረጃ ቴክኖሎጂው ዘርፍ የጀመርነውን የሰበካ ጉባዔ፣ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አስተዳደር እና ሌሎችም ዘመናዊ ስልት በሁሉም አህጉረ ስብከት ተግባራዊ እንዲሆን አሳስባለሁ፡፡
በተለይ ደግሞ ከዚህ ዓለም ዐቀፍ ጉባዔ ማጠቃለያ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በትኩረት ልናያቸው ይገባል፡-
1. ስበከተ ወንጌልና የትውልድ ግንባታን በተመለከተ በየሀገረ ስብከቱ የሚኖሩ ወጣቶችንና ሕፃናትን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ለመቅረጽ ዘመኑን የዋጀና ቴክኖሎጂን የተጠቀመ የስበከተ ወንጌል አገልግሎትን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡
2. የሕንፃ ግንባታና የፋይናንስ ሥርዓት ዘመናዊነትን በተመለከተ፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ሀብት በዘመናዊ፣ በግልጽና በታማኝ የፋይናንስ ሥርዓት መምራትና ማስተዳደር ያስፈልጋል።
3. በልማት ራስን ስለመቻል፡ አህጉረ ስብከት በቋሚ ልማት ላይ በማተኮር ራሳቸውን እንዲችሉና ለችግረኞችና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገውን የበጎ አድራጎት ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል።
4. ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም እናት እንደመሆኗ መጠን በሀገራችንና በዓለም ዙሪያ ሰላም፣ ፍቅርና ዕርቅ እንዲወርድ የድርሻዋን እንድትወጣ ማድረግም ይጠበቅብናል።
በመጨረሻም ባለፈው የሥራ ዘመን ላደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረትና በዚህ ጉባዔ ላሳያችሁት ንቁ ተሳትፎ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ይህንን ጉባዔ በሰላም አስጀምሮ፣ ጥበቡንና ማስተዋሉን ሰጥቶ በሰላም እንዳስፈጸመን፣ ለመጪው ሥራ እንዲያተጋንና እንዲያበረታን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።
እግዚአብሔር አምላካችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያንም ጽኑ ሰላም ያድርግልን፡፡
ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
አባ ሳዊሮስ
የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ