የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ መልዕክት
ወይሔይስ ትርሲቱ ለዝንቱ ቤት ዘደኀሪ እምዘቀዳሚከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል
” ሐጌ 2፡9″
ከሁሉ አስቀድመን የክብር ሁሉ ባለቤትና የዘመናት ጌታ ያለፈውን ዓመት በክብር ሸኝተን ዐዲሱን ዓመት በማይልፍ ሰማያዊ ሀብቱ፣ በማይወሰን ምኅረቱ እንድንቀበል፤ የጀመርነውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ ሁለገብ ሕንፃ አጠናቀን እርሱን በማመስገን እንድንመርቅ ላበቃን ልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁን እያልን ሁላችንንም እንኳን በሰላም አደረሰን እንላለን፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “እመ እግዚአብሔር ኢሐነጸ ቤተ ከንቶ ይጻምው እለ የሐንጹ – እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞቹ በከንቱ ይደክማሉ።” እንዲል የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከልሒቅ እስከ ደቂቅ የሚሰበሰቡበት፣ የሚማሩበት፣ በኅብረት የሚያገለግሉበት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ክብር የሚገለጥበት፣ የወንጌል ቃል የሚታወጅበት፣ ያለፈውን በጋራ ሰምተን የወደፊቱን የምናቅድበት፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤያትን የምናከናውንበትና ሁለገብ አገልግሎትን የምንሰጥበት የዚህ ታላቅ ሕንፃ ግንባታ እግዚአብሔር ባያግዘን በእኛ አቅም የሚቻልና የሚፈጸም አልነበረም፡፡ ስለሆነም ወሀቤ ጸጋ ለሆነው አምላካችን ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን። (መዝሙር 127፥1)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእከቱ “እርስ በርሳችን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እንተያይ፤ መሰብሰባችንንም እንደ አንዳንዶች ልማድ አንተው።” ብሎ እንደጻፈ ይህ አዳራሽ እርስ በርሳችን የምንበረታታበት፣ እምነታችንን የምናጠናክርበት፣ ፍቅርንና ኅብረትን የምንገነባበት፣ ስንቸገር ለመፍትሔ የምንሰባሰብበት፣ አበይተ ቤተ ክርስቲያን ጥበባቸውንና ልምዳቸውን ለቀጣዩ ትውልድ የሚያካፍሉበት፣ ውሉደ አበው ወጣቶች የሚማሩበት ሆኖ በመጠናቀቁ ሁላችንም ደስ ብሎናል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሁለት ወይም ሦስት ሁናችሁ በስሜ በምትሰበሰቡበት እኔ በመካከላቸው እኖራለሁ” ብሎ ቃል ኪዳንን ስለሰጠን ጽርሐ ተዋሕዶ በአንድ አማናዊ ልብ በመሰብሰብ ውይይቶቻችን በአክብሮት፣ ውሳኔዎቻችን በጥበብ፣ ልዩነቶችን በፍቅርና ተልእኮአችንን በታማኝነትና በመፈጸም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ፍሬ የምናቀርብበት ረድኤተ እግዚአብሔር የሚገኝበት ወሳኝ ስፍራ ነው። (ማቴ 18፥20፣ ዕብ 10፥24)
በርግጥ አንድ ሕንፃ ትርጉም የሚኖረው በግድግዳው፣ በጣሪያው ወይም በውበቱ ብቻ ሳይሆን በሚሰጠው አገልግሎት፣ በሚቀርቡ ዕሴቶችና በሚፈጸሙ መልካም ሥራዎች ነው። ነቢዩ ሐጌ 2፥9 ላይ፦ “የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ቤት ክብር ይበልጣል” ሲል ነባሩንና የቀደመውን የወደደና የባረከ አምላክ፤ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ወድጃለሁ በማለት ቃል ኪዳኑ እንዳተቋረጠና ከእኛም እንዳልተለየ አረጋግጦልናል፡፡ በቀደመው ሕንፃ ውስጥ ለብዙ ዐሥርት ዓመታት አያሌ አገልግሎቶችን ከሰበካ ጉባኤ ጀምሮ ስብከተ ወንጌልን፣ የወጣቶች ተሳትፎ፣ የአበውን ዝክርና ክብር፣ የዘመናት ዐውደ ርእይና በርካታ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ያለማቋረጥ ፈጽመንበት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዚያ ላይ ተመሥርተን እግጅ ውብና ሰፊ፣ ጠንካራና ሁሉን አሳታፊ አዲስ ሕንፃ ተሠርቶ ለምረቃ በቅቷል፡፡
ዛሬ የምንመርቀው ሕንፃ ከባለፈው ሕንፃ በሁለንተናው ይበልጣል፡፡ በትልቅነቱ፣ በሚይዘው የሰው አቅም፣ በሚሰጠው የአገልግሎት ስፋት፣ በማራኪነቱና በውበቱ በሁሉ የላቀ ነው፡፡ ይኽንን ሁሉም አይቶ የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ ከቀድሞው በብዙ እጥፍ የበለጠ እንዲሆንም በአዲሱ አዳራሽ የሚቀርበው አገልግሎት ትልቅ ሊሆኑ የሚገባ ሲሆን እነርሱም ፍቅርና እምነት፣ መተባበርና ኅብረት፣ ጥበብና ትጋት፣ አንድነትና የተቃና አገልግሎት የመሳሰሉት ናቸው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እናንተም እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።” ብሎ የሰጠን መመሪያ ለዛሬው የምረቃ በዓል ትልቅ ትርጉም አለው። ጽርሐ ተዋሕዶ ብዙ ሰዎችን በአካልና በአእምሮ እንዲያሰባስብ ተገንብቷል፤ እንደዚሁም ሁሉ የእኛ ማንነት በማይጠፋውና በማያረጀው በክርስቶስ የተገነባ ሕያው ማኅበረሰብ መሆን አለብን። ጽርሐ ተዋሕዶ አሁን ስናየው እጅግ የሚያምር፣ በብዙ ድካምና ጥበብ የተሠራ ምድራዊ ሲሆን በሚያረጀው ሕንፃ ውስጥ የማይፈርሰውንና የማያረጀውን በሁለንተናችን የከበረ እና የደመቀ ማንነት፣ ያማረ አንድነትን የምንሠራበት በመሆኑ ሰማያዊ ክብርን እንድንገነባ ያግዘናል፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 2፥5)
እንደሚታወቀው እግዚአብሔር የሚመሰገንበትና የሚከብርበት ሕንፃ ከምድራዊ ጥሬ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆን በሰዎች እምነትና ቅድስና፣ ፍቅርና ንጽሕና፣ ጥበብና መንፈሳዊነት ይገባል፡፡ እንደ ሕንፃው ሁሉ እኛ እርስ በርሳችን ጠንካራ አንድነት፣ ኅብረትና መከባበር ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ይህን አዳራሽ ስናስመርቅ “እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፣ ይህን ሕንፃ እንደገነባን ልባችንንም ገንባ፤ የዚህ ታላቅ ሕንፃ ግድግዳውን እንዳቆምን ተስፋቸችንንና አንድነታችንንም በጽኑ መሠረት ላይ አጽንተህ አቁምልን፤ በአስደናቂ አፈጻጸም ጣሪያውን እንደከደን ምሕረትህን በላያችን ፍቅርህን በውስጣችን አኑርልን፤ በዚህ ሕንፃ ውስጥ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቀርበው ስብሐት፣ የምናደርገው ምክክርና የምንፈጽመው ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ሁሉ ያማረና የሰመረ አድርግልን” እያልን በአንድነት ልንጸልይ ይገባናል፡፡
ጽርሐ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን በሚመጥን፣ ትውልድን በሚዋጅ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃዋን በሚጠብቅ ለታላቋ ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ቁመና መሠረት የሚጥል፣ ለወደፊቱ ሐዋርያዊ ተልእኮ ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት ለቀጣዩ ትውልድ የሚወረስ ቅርስ ነው፡፡ ቅርስነቱ የሕንፃ ሀብት ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ አገልግሎትና ጠንካራ የእምነት ምስክር፣ ለቤተ ክርስቲያን ዋጋ ለመክፈል ያለንን ቂርጠኝነት ማሳያ ምስክር ነው፡፡
ስለሆነም ሕንፃውን ስንመርቅ አደራ የምንቀበልበትም አደራ የምናወርስበት እለት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በአዳራሽ ውስጥ መሰብሰብ ቀላል ነው፤ በፍቅር አንድ ሆኖ መኖር ግን እውነተኛው ምስክርነት ነው።” እንዳለው እውነተኛ ምስክርነት የምናቀርብበት እንዲሆን ቃል የምንገባበትና ለቀጣዩ ትውልድ መልካም የሆነ የትጋት ምሳሌና ጅምርን የመጨረስ አርአያንና አደራን የምንተውበት የምረቃ ቀን ነው፡፡
ከፊተኛው አዳራሽ ይልቅ ሁለተኛው አዳራሽ እንደሚበልጥ ሁሉ ካለፈው ይልቅ የወደፊቱ ተልእኮአችን የበለጠ የሰመረ፣ ከዘመኑ ጥበብ እጅግ የከበረ፣ የላቀና የታፈረ ያድርግልን እያልን ግንባታው እንዲጠናቀቅ ከቅዱስ ሲኖዶስና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጀምሮ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና የሥራ ኃፊዎች ሁሉ ተገቢውን ጥረት በማድረጋቸው ልናመሰግናቸው ይገባናል፡፡ እንደሚታወቀው የሕንፃው ሥራ የታቀደውና የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) አምስተኛው ፓትርያርክ ዘመን ነበር፡፡
የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ሆኖ እኔና ብፁዕ ወንድሜ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ ሊቀ ጳጳስ በአንድነት አስጀምረን፣ በመካከል ብፁዕ አቡነ ያሬድ ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ሊቀ ጳጳስ በጠቅላይ ሥራ አስከያጅነት የሥራ ዘመናቸው የበኩላቸውን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው አሁንም በታሪክ አጋጣሚ እኛው እንዳስጀመርነው ለማስመረቅ በመብቃታችን አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡
በተለይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተጀምሮ የነበረውን አዳራሽ ከመፈጸም በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ያከናወኗቸው ትውልድ ተሸጋሪ የግንባታና የማስዋብ ሥራዎች፣ አደረጃጀቱን ለመንፈሳዊ፣ ለማኅበራዊና ለአስተዳደር ሥራ ብቁና ደረጃውን የጠበቀ በማድረግ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ጋር በቅርበት በመወያየት ያለአግባብ ተወስዶ የነበረውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ/ ግቢ ይዞታ በአስተዳደራዊ ጥበብ በማስመለስ፣ ክፍት በሆኑ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ላይ ታላላቅ የሕንፃ ግንባታዎችን በማስጀመር፣ ተጀምረው የነበሩት በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በማስቻል፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከአድልኦ የጸዳ መልካም አስተዳደርና ዘመናዊ አሠራር እንደሰፍን ቀን ከሌሊት ያለእረፍት የሚያደርጉት ጥረት አርአያነት ያለው በትውልድ የማይረሳ ታሪካዊና ሐዋርያዊ ተግባር በመሆኑ ከፍ ያለ የተለየ ክብርና ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሥራችንን ለበረከት ያድርግን አገልግሎታችን ይቀበልልን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን እና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አባ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ
መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ/ም፡ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ