መልዕክተ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ቅጽር ጊቢ የተገነባው ዓለም ዓቀፍ ሁለገብ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ምረቃ መርሐግብር ላይ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ያስላለፉት መልእክት እንደሚከተለው ይነበባል።«ወይኄይስ ትርሢቱ ለዝንቱ ቤት ደኃሪ እምቀዳሚ – የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይልቅ ይበልጣል” (ሐጌ 2፡9)፡፡
ክቡር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት፣
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤
ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነሕ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፤
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ክቡር ሙኃዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በሚኒስትር መዓርግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዩች አማካሪ ሚኒስትር፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
ክቡር ረ/ፕ ግርማ ባቱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡራን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች ፤
ክቡር መምህር ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡራንና ክቡራት፤
«ወይኄይስ ትርሢቱ ለዝንቱ ቤት ደኃሪ እምቀዳሚ – የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይልቅ ይበልጣል” (ሐጌ 2፡9)፡፡
በቅድሚያ፡ ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ ይህን ታሪካዊ ስኬት ለማየት ላበቃን እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁን፡፡ ወደዚህ የጽርሐ ተዋሕዶ ምረቃ በዓል እንኳን ደህና መጣችሁ፡፡
ተቋማዊ ዕድገትን ለሚያበሥረውና አዲስ ምዕራፍ ለሚከፈትበት ለዚህ ታላቅ ዕለትና ጽርሐ ተዋሕዶ ብለን ለሰየምነው ለአዲሱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሁለገብ ሕንጻ ምረቃ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ውስጥ በርካታ ታላላቅ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ እነዚያ የቀደሙት ስኬቶች ለዛሬው ተግባር መሠረቶች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ዛሬ የምናስመርቀውን ይህን ግዙፍ ማዕከል ከቁሳዊ ስኬት በላይ ከፍ አድርገን ብንመለከተው፣ የሃይማኖታችን ጽናት፣ የኅብረታችን ፍሬ፣ የጸሎታችን መልስና የእግዚአብሔር ታማኝነት ሕያው ምስክር ሆኖ ይገኛል። ነቢዩ ሐጌ፦ «የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይልቅ ይበልጣል፥ ይላል እግዚአብሔር የሠራዊት አምላክ፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ» (ሐጌ 2፡9) ብሎ እንደተናገረው፣ ይህ ጽርሐ ተዋሕዶ ከቀደሙት ይልቅ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን የአገልግሎት አቅም ወደ ታላቅ ደረጃና ክብር የሚያሸጋግር፣ የወንጌል ሰላምና እውነት ለትውልድ የሚታወጅበት አዲስና ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል ነው።
ቤተ ክርስቲያናችን በረጅም ዘመናት ታሪኳ ውስጥ ታላላቅ በዓላትና መንፈሳዊ ኩነቶችዋ በጊዜው በነበሩ አነስተኛና ዝቅተኛ ደረጃ በነበራቸው መሰብሰቢያዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎች የሚያዘጋጇቸው መርሐ ግብራትም ሌሎች ተቋማትን ደጅ መጥናትና ለከፍተኛ ወጪ መዳረግን የሚያስገድዱ ነበሩ፡፡ ከዚህም በላይ ቤተ ክርስቲያናችን ባሏት ትምህርታዊ ሀብታትና በስመጥር ሊቃውንት ጸጋ ላይ ተመሥርታ ታላላቅ ጉባዔያትን ለማድረግ እንዳትችል በቦታ ውሱንነት ተገድባ ቆይታለች፡፡ ዛሬ የምናስመርቀው ይህ ሕንጻ እነዚህን ሁኔታዎች የመቀየር ታላቅ አቅም አለው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች የሕንጻው መጠናቀቅና ለምረቃ መብቃት እንደ ታሪክ ቀያሪ ክስተት ቢቆጠር ተገቢ ነው፡፡
ይህ ግዙፍ ሕንጻ ዛሬ የተገነባበት ቦታ ላይ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ነበር፡፡ በወቅቱ ቅዱስነታቸው ከአሥር ሺህ በላይ ተሰብሳቢዎችን መያዝ የሚችል ግዙፍና ዘመናዊ ማዕከል እንዲገነባ መመሪያ ሰጥተው እንደነበር ብዙዎቻችን እናስታውሳለን ። በመቀጠል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘመነ ሢመት መጀመሪያ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ዘመን አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ ዲዛይን ተሠርቶና የግንባታ ፈቃድ ወጥቶለት የነበረ ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን የዚህ ታሪካዊ መርሐ ግብር ተሳታፊዎች
የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በቅብብሎሽ የሚከናወን እንደመሆኑ መጠን ብፁዕ አቡነ ያሬድ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በተሾሙ ማግስት ግንባታው እንዲጀመር ከማድረጋቸውም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲፋጠን በማድረግ ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል፡፡
በመቀጠል ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት እንዲመሩ የተሾሙት ብፁዕ አቡነ አብርሃምም ከብፁዕ አቡነ ያሬድ የተረከቡትን የግንባታ ሥራ በማስቀጠል አንዳንድ የዲዛይን ማሻሻያዎችን በማድረግና በሕንጻው ውስጥ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ከአንድ መቶ ሃያ በላይ ብፁዓን አበው ሊቀ ጳጳሳትን የሚያስተናግድ፣ የቅዱስ ሲኖዶስንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚመጥን፣ የተሟላ አዳራሽ ተካቶ እንዲሠራ በማድረግ እንዲሁም የግንባታ ሥራው በተቻለ አቅም እንዲቀላጠፍ በማድረግ የሚያስመሰግን ሥራ አከናውነዋል፡፡
ከብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ዘመን በኋላ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት የጽርሐ ተዋሕዶ ሕንጻ ግንባታ በተቻለ ፍጥነት እንዲከናወንና በዙሪያው ሊሠሩ የሚገባቸው ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች እንዲቀላጠፉ ተደርጓል፡፡ ለሕንጻው መጠናቀቅ የሚረዱ ውሳኔዎችን በመወሰን፣ ውስጣዊ ግብዓቶቹም በተቀላጠፈ መልኩ ከውጭ ገብተው በአስቸኳይ እንዲገጣጠሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ ምክንያት እነሆ የግንባታው ሥራ ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራንና ክቡራት
ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ዐቅዶና ትግበራውን ተከታትሎ ለፍጻሜ ማብቃት ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሮች በታሰቡበት ልክ የማይሄዱበትና ያልታሰቡ ጉዳዮች የሚከሰቱበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡ ይህ ሕንጻ ለመጠናቀቅ ታቅዶለት የነበረው የመጀመሪያ የጊዜ ሰሌዳ አልፎ፣ ለረጅም ጊዜ መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የተጀመሩ ሥራዎችን ተከታትሎ ማስፈጸም በሚለው አንደኛው የተግባራዊ እንቅስቃሴያችን አካል ሊሆን በመቻሉ የተገኙ ለውጦች ለዚህ ሊያበቁት ችለዋል፡፡ የዚህ ሕንጻ ግንባታ መጠናቀቅና ይህን በመሰለ መልኩ ፕሮጀክቱን ተከታትሎ ማስፈጸም መቻል ቤተ ክርስቲያናችን የያዘቻቸውን ቀጣይ የልማት ዕቅዶች መፈጸም ስለመቻሏ የሚፈጥሩት እርግጠኝነት በቀላሉ አይታይም፡፡ አሁንም ቀጣይ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ይህን ቁርጠኝነት እየጠየቁን ስላሉ ይህኛው ስኬታችን ታላቅ የሥነ ልቡና ብርታት ይፈጥርልናል፡፡ ከጽርሐ ተዋሕዶ በቀጣይነት በአሮጌ ቄራ የሚገኘውና 1000 ካሬ ላይ ያረፈው ባለ አሥር ወለል ሕንጻ የጥቅምት 2019 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንደተጠናቀቀ ይመረቃል፡፡ በዚያው አካባቢ የሚገኘውን 480 ካሬ ላይ ያረፈ ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንጻ በቅርቡ ማስመረቃችንም የሚታወስ ነው፡፡ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችም ግንባታቸው ተጀምሮ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንገኛለን፡፡
በሥራችን መጀመሪያ ወቅት ላይ ጽርሐ ተዋሕዶን ለማጠናቀቅ ያቀድነው ዕቅድ እውን የሆነው በዋናነት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድና ረድኤት ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እለሰ ይሴፈውዎ ወይትዔገሥዎ ለእግዚአብሔር ይሔድሱ ኀይሎሙ ወይበቊሉ ክነፊሆሙ፣ ከመ ንስር ይረውጹ፣ ወኢይደክሙ የሐውሩ ወኢይርኅቡ – እግዚአብሔርን የሚታመኑ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንሥር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም» (ኢሳይያስ 40፡31) እንዳለው፣ እኛም በሂደቱ ያጋጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ታምነንና ተስፋችንን በእርሱ ላይ አድርገን አልፈናል።
ይህ ሁለገብ ጽርሐ ተዋሕዶ ሲጀመር የነበረውን ፈታኝ ሁኔታ፣ ያለፈበትን ረጅም መንገድና እስከዚች ሰዓት ድረስ የተከፈለውን ሁለንተናዊ ዋጋ ስናስብ፣ የእግዚአብሔር እጅ በሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዴት አድርጎ ሲሠራ እንደነበር በግልጽ እንረዳለን። በግንባታው ሂደት ውስጥ ያጋጠሙን የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የልዩ ልዩ ፈተና ማዕበላት ቀላል አልነበሩም፤ ነገር ግን የያዝነው ዓላማ የወንጌልን እውነት ከማስፋፋትና ቤተ ክርስቲያንን በሁለንተናዊ መልኩ ከማጠናከር ጋር የተያያዘ አደራ በመሆኑ በጽናት ቀጥለናል።
ዛሬ የምናስመርቀው ይህ ግዙፍ ማዕከል ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ዘመናዊና ሁለገብ የሆነ ታላቅ ተቋማዊ ዐቅም የሚፈጥር ነው። ይህ ስፍራ የቅዱስ ሲኖዶስና የዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ማካሄጃ፣ የታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት መድረክ፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችንን ታላቅነት የሚያንጸባርቁ መንፈሳዊ በዓላት በልዩ ሁኔታ የሚከበሩበት፣ የድምጽ ወምስል ዘመናዊ መሣሪያዎች የተገጠሙለት ማዕከል ነው። በጽርሐ ተዋሕዶ ውስጥ ታላላቅ ስብሰባዎችን የሚያስተናግዱ እና መለስተኛ የሆኑ የተለያዩና ደረጃቸውን የጠበቁ አዳራሾች፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ይህን መሰል ሁለገብ ሕንጻ አጠናቆ ማስመረቅ ያለው ትርጉምና ጠቀሜታ የላቀ በመሆኑ ሁላችሁንም እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡
ይህ ሕንጻ፣ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዚህ እንዲበቃ ከፍተኛ ጥረት ያደረጋችሁ ሁሉ፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እንግዲህ፣ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትናወጡም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ» (1ቆሮ. 15፡58) በማለት ያስተማረው ቃል ዛሬ በእናንተ ትጋት ፍሬ አፍርቶ ይታያል። በዚህ የምረቃ ዕለት፣ ይህ ሕንጻ እውን እንዲሆን የተከፈለውን ዋጋ ስናስብ፣ በየደረጃው አስተዋጽኦ ያደረጋችሁትን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ስም ልናመሰግናችሁ እንወዳለን።
ከሕንጻ ግንባታው ሂደት ጀምሮ በተለይም ባለፉት 16 ወራት ለተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎች ሁሉ በአመራራቸው፣ በቡራኬያቸውና በጸሎታቸው ያልተለዩንን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትን በልዩ ሁኔታ እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡
ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚህና በሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ የሚያስፈልገንን ድጋፍ በማድረግና ለልማት ተነሺ ቦታዎች ምትክ በመስጠት ላደረጉልን ከፍተኛ እገዛ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ከሠላሳ ዓመታት በላይ የዘለቀ የአገልግሎት አንድነታችንን ለመለየት፣ ጸብንና መከፋፈልን ለመፍጠር የተካሄደብንን ከባድ የስም ማጥፋት ዘመቻ ወደ ጎን በመተው በሐሳብና ቅንነት በተመላው ምክር ሳይደክሙና ሳይታክቱ በጽናት ከጎናችን በመቆም ላደረጉልን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
የምናቀርባቸው ሐሳቦችና ጥናቶች ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ባለፉት 16 ወራት የተመዘገቡት ውጤቶች እውን እንዲሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉልን ብፁዓን የቋሚ ሲኖዶስ አባላትና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት በሙሉ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ እናመሰግናችኋለን፣ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ለማለትም እንወዳለን፡፡
መጋቤ ሠናያት ኢንጂነር አያሌው መሸሻ ይህን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሁለ ገብ ሕንጻ በተቋራጭነት በመያዝ ከመጀመሪያው እስከ ፍጻሜው ድረስ በአስቸጋሪ መንገዶች በማለፍ፣ ዓለማችን የምትገኝበትን ፈታኝ ሁኔታ ተቋቁመው ዕቃዎችን ከውጪ በማስገባት፣ ሌት ተቀን በጽናትና በትጋት ለሠሩት ሥራ ከፍ ያለ ልባዊ ምስጋናችንን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናቀርባለን፡፡ መጋቤ ሠናያት ኢንጂነር አያሌው መሸሻ ከዚህ ሕንጻ በተጨማሪ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ሙሉ ወጪውን ሸፍነው ቅጽረ ግቢውን አሁን በሚታየው መልኩ በማጽዳትና በማስዋብ ምቹና ደረጃውን የጠበቀ የአገልግሎት መስጫ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አጠቃላይ አገልግሎት የሚውል ከፍተኛ አቅም ያለውን የከርሠ ምድር ውኃ በራሳቸው ወጪ በማስወጣት አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡ ሌሎችንም የጠየቅናቸውን ሥራዎች ሁሉ በራሳቸው ወጪና ሥራውን በባለቤትነት ይዞ በመሥራት ላሳዩት ቁርጠኛ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት እግዚአብሔር ሥራዎንና ቤተሰቦን ይባርክ፣ ለቀጣይ ፕሮጀክቶች ፍጻሜም ብርታቱንና ጽናቱን ይስጦት እንላለን፡፡ሴይ አማካሪ ድርጅትንም ከመጀመሪያው እስከ ፍጻሜው ድረስ በእኛ ወገን ሆኖ ሥራውን በመከታተል ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም፣ ይህን ጽርሐ ተዋሕዶን እየመረቅን ባለንበት በዚህ ጊዜ ለቀጣይ ሥራዎቻችን የሚያስፈልገው ትጋትና ቁርጠኝነት ከቀድሞው የበለጠ እንዲሆንና የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች እንድናጠናቅቅ አደራ ለማለት እወዳለሁ። የሥራ ተነሣሽነታችን እንዲጨምር፣ ኅብረታችን እንዲጸና እና ቤተ ክርስቲያንን ለሚጠቅም የጋራ ዓላማ በአንድነት እንድንሰለፍም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ይህ ሕንጻ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ ግርማ፣ ለወንጌል ብርሃን መፍለቂያ የሰላም ማዕከል፣ ለአምላካችንም ክብር ምስጋና ማቅረቢያ እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፣ ቀሪ ሥራዎቻችንን ሁሉ ይባርክ፡፡ ሀገራችንን በሰላም በፍቅርና በአንድነት ያጽናልን፡፡
መልካም የምረቃ በዓል!
አባ ሳዊሮስ
የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የሸገር ከተማና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አሄጉረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ